Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዓይን ግርዶሽን በእንጭጩ የማስቀረት ትልም

የዓይን ግርዶሽን በእንጭጩ የማስቀረት ትልም

ቀን:

ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ወልቂጤ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በግብርና ሕይወትና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአብዛኛው የትራኮማ (የዓይን ማዝ) ተጠቂ መሆናቸውን ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡

ድርጅቱ በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በመሄድ፣ የዓይን ሕክምና ማዕከል በማቋቋምና ግብዓቶችን በማቅረብ የዓይን ሕሙማን የሆኑ ወገኖችን እየረዳ ይገኛል፡፡

ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ እናቶችና አባቶች ተደርድረው ቁጭ ብለዋል፡፡ ከተደረደሩት እናትና አባቶች መካከል ወ/ሮ ቀመሪያ መሐመድ ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ቀመሪያ የዓይን ሞራ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሞራው እየጋረዳቸው መምጣቱን የሚናገሩት ወ/ሮ ቀመሪያ፣ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ ባለማግኘታቸውና የችግሩን አሳሳቢነት ባለማወቃቸው ሁለቱም ዓይናቸው እክል እንደገጠመው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ ብቻ ዓይናቸውን ለመታየት አካባቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ማቅናታቸውን፣ ነገር ግን በቂ ሕክምና ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ሕመም መጋለጣቸውን አስታውሰዋል፡፡ ወ/ሮ ቀመሪያ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጉሊት ላይ እንደሚነግዱና በአዋራና በመሰል ችግሮች ምክንያት የበሽታው ተጠቂ ሊሆኑ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር መለያየታቸውን የሚያስረዱት ወ/ሮ ቀመሪያ፣ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች ተደማምሮባቸው ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደከበዳቸው ገልጸዋል፡፡ የሚኖሩበት አካባቢ ገጠራማ በመሆኑ፣ ጤና ጣቢያ ወይም የሕክምና ተቋም አለመኖሩን፣ የመጀመርያ ሕክምናቸውን ያገኙት ረዥም ርቀት ተጉዘው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በጊዜ ሒደት ግን ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሚባል ድርጅት ቤት ለቤት የዓይን ሕክምና መስጠት መጀመሩን በሰሙ ወቅት ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደቻሉ አስታውሰዋል፡፡

ወደ ጤና ተቋሙ በሚሄዱበት ወቅት ፍራቻ እንዳደረባቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ቀመሪያ፣ በጓደኞቻቸው ግፊት ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ፣ አገልግሎቱን ማግኘት መቻላቸውን ያስረዳሉ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሄዱ ወዲያውኑ አገልግሎቱን አለማግኘታቸውንና ወረፋ ተይዞላቸው አሁን ላይ ሁለቱንም ዓይናቸውን ሊታከሙ መቻላቸውን ሪፖርተር በቦታው ሆኖ ሊመለከት ችሏል፡፡

ሕክምናውን ከማግኘታቸው በፊት ሽፋሽፍቶቻቸው እየተነቀሉ ሁለቱንም ዓይኖቻቸውን ሊጋርደው እንደቻለ፣ በጤና ባለሙያዎችና በጓደኞች ምክንያት ሕክምናውን ሊያገኙ በመቻላቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ዓይኖቻቸውን መታከማቸውንና በቀጣይም ፍራቻቸውን አስወግደው በየጊዜው ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በግብርና ሕይወት የተሰማሩት ዕድሜያቸውን 72 ዓመት የሚገምቱት አቶ ቶማስ ወልደ ትንሳዔ፣ የዓይን የሞራ ግርዶሽ በሽታ ሰለባ ሆነዋል፡፡

አቶ ቶማስ ቀድሞ ግራ ዓይናቸውን መታመማቸውንና በኋላ ሙሉ ለሙሉ ማየት እንደከበዳቸው ተናግረዋል፡፡ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ሁለቱም ዓይኖቻቸው በበቂ ሁኔታ ማየት እንደማይችሉና ችግሩ መባባሱን አስረድተዋል፡፡

የቀኝ ዓይናቸው በሞራ መጋረድ ከጀመራቸው አራት ወራት ማስቆጠሩን፣ ከዚህ በፊትም የግራ ዓይናቸውን አካባቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ በነፃ መታከማቸውን ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ድርጅት ባመቻቸላቸው የሕክምና አገልግሎት ሁለቱም ዓይኖቻቸው ማየት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ቶማስ ከባለቤታቸው ስምንት ልጆችን ማፍራታቸውን፣ ልጆቻቸውም በተለያዩ ነገሮች እየደገፏቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸውን ሆነ የአካባቢውን ሰው በድምፅ እንጂ በዕይታ እንደማይለዩዋቸው የሚናገሩት አቶ ቶማስ፣ በዚህም የተነሳ በመጠኑም ቢሆን ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው አስታውሰዋል፡፡

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዓለማየሁ ሲሳይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በጉራጌ ዞን ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሕፃናት የትራኮማ (የዓይን ማዝ) በሽታ ተጠቂ ናቸው፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጥናት ማድረጉን የገለጹት የካንትሪ ዳይሬክተሩ፣ በጉራጌ ዞን ከፍተኛ ችግር በመኖሩ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ዘልቆ በመግባት እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በምዕራብ ጉራጌ እ.ኤ.አ. ከ1999 ጀምሮ ‹‹የዓይን ጤና እንክብካቤ›› ላይ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ዓለማየሁ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት አጠናክሮ በመቀጠል ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ መንግሥታዊ የሆኑ የጤና ተቋሞች ላይ በመሄድ የዓይን ሕክምና ችግር ያለባቸውን ወገኖች በመርዳት ሰፊ ሥራ መሥራቱን፣ በተለይም ደግሞ በጉራጌ ዞን ላይ ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ የሕክምና አገልግሎቶችን በተለያዩ የጤና ጣቢያዎች ላይ በመጓዝ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በጉራጌ ዞን ባለፉት 20 ዓመታት ድርጅቱ የዓይን በሽታን በተመለከተ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጉን ያስታወሱት ካንትሪ ዳይሬክተሩ፣ የወልቂጤ ሁለተኛ ደረጃ የዓይን ሕክምና ማዕከል ውስጥ የማስፋፋት ሥራ መሥራቱን፣ የማዕከሉን የማስፋፊያ ግንባታ ለመፈጸም ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ ከጉራጌ ዞን ጤና መምርያ ቢሮ፣ ከአካባቢው የማኅበረሰብ ክፍሎችና ከማዕከሉ ሠራተኞች ጋር በመቀናጀት ግንባታውን ተግባራዊ ሊያደርግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በጉራጌ ዞን የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ተንሠራፍቶ የነበረው የዓይን ጤና ችግር (ትራኮማ) ለመከላከልና ሕክምናውን በአግባቡ በመስጠት በኩል የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ድርጅት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያሉት የጉራጌ ዞን ጤና መመርያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን ናቸው፡፡

ድርጅቱ የመንግሥት መዋቅርን ተከትሎ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ በዞኑ ሥር ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

ለትራኮማ (የዓይን ማዝ) በሽታ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዞኑ ፕሮጀክት ነድፎ እየሠራ እንደሚገኝ፣ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በስምንት የገጠር ወረዳዎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በየዓመቱ የዚትሮ ማክስ መድኃኒት ማከፋፈል መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በዞኑም በአምስት ወረዳዎች ማለትም እዣ፣ ምሁር፣ አክሊል፣ እንደጋኝ፣ ገደባኖ፣ ጉታዘር፣ ወለኔና አበሽጌ ላይ የእንጭጭ ትራኮማ ሥርጭት እንዲቀንስ የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በዞኑ የጤና ሥርዓቱን ከማጠናከር አንፃር ሰፊ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን፣ በተለይም በመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ ከ24 በላይ የመጀመርያ ደረጃ የዓይን ሕክምና መስጫ ክፍሎችን በመሣሪያ በማደራጀትና መድኃኒቶችን እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ከትምህርት ዘርፉ ጋር በተያያዘም በፕሮጀክት ውስጥ በማስገባት በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች በትምህርት ቤቶች የዓይን ጤና ክበብ በማቋቋምና ሥልጠናዎችን በመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱም በወልቂጤ ጤና ጣቢያ ውስጥ የመነጽር ማምረቻ ወርክሾፕ በመክፈትና ባለሙያዎችን በማሠልጠን እንዲሁም ዘመናዊ የመነፅር ማምረቻ መሣሪያዎችን በማደራጀት ማኅበረሰቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የመነፅር አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2020 ላይ ‹‹ትራኮማን እናጠፋለን›› የሚል አቅጣጫ ማስቀመጡን፣ ተግባሩን በ2030 ተፈጻሚ እንዲሆን አቅጣጫ መቀመጡንና ተፈጻሚ እንዲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ አገሮች የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው አቅጣጫ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደሆነ፣ የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ሲኒየር ፕሮግራም ማናጀር አቶ ተዘራ ደስታ ተናግረዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል አምስት በመቶውን መፈጸም ከተቻለ ችግሩ ሊወርድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዞኑ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል የዓይን በሽታ ተጠቂ እንዳይሆን የተለያዩ ግንዛቤዎች እንደሚሰጣቸው የገለጹት አቶ ተዘራ፣ ዕድሜያቸው ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተጠቂ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በጉራጌ ዞን አካባቢ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በየዓመቱ የዚትሮ ማክስ መድኃኒት በማሠራጨት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የኦርቢስ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ዶሪስ (ዶ/ር) የዓይን ሕክምና ማዕከሎች ጉብኝት ሲያደርጉ እንደገለጹት፣ ለዓይን በሽታ ተጠቂ የሆኑ ወገኖችን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የዓይን ማዕከሎች ውስጥ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ድርጅቱ የሚሠራ መሆኑን፣ በወቅቱ ላደረጉላቸው አቀባበል ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...