Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል የናፈቃቸው አዲስ አበቤዎች

ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል የናፈቃቸው አዲስ አበቤዎች

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገጥሙ በርካታ ችግሮች መካከል የንፁህ ውኃ እጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ጋር የሚስተካከል የውኃ አቅርቦት አለመኖር ብዙዎችን ለእንግልት ዳርጓል፡፡ በተለይም ውኃ በፈረቃ የሚያገኙ አዲስ አበቤዎች ቅሬታቸውን ማሰማት ከጀመሩ ዓመታት ቢቆጠርም ከጊዜያዊ መፍትሔ የዘለለ ምላሽ አላገኙም፡፡

ችግሩን ለመፍታት መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ቢናገርም፣ የውኃ እጥረትና ፍትሐዊ ክፍፍልን ማስፈን መፍትሔ አልባ ሆኗል፡፡ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ታቦት ማደሪያ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በአካባቢው በሳምንት አንድ ጊዜ ውኃ የሚያገኙበት ፈረቃ ቢኖራቸውም፣ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሁለትና ሦስት ሳምንታት ድረስ ውኃ እንደማያገኙ ይገልጻሉ፡፡ በፈረቃው በሚመጣበት ወቅት ውኃ ቢለቀቅም ኃይል የሌለው በመሆኑ ከአንድ ባልዲ በላይ ላያገኙ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡ የፈረቃ ቀን ማዘልና ሰው በማይጠብቅበት ቀን መልቀቅ፣ ውኃ በቀን ላይ መልቀቅ ሲገባ ከምሽቱ 4 ሰዓትና ከዚያ በኋላ በመለቅ ቀን ሥራ የዋለ ቤተሰብን ማንገላታት ለአካባቢያቸው የተለመደ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡

የሚለቀቀው ውኃ ኃይል ስለሌለውና እየተቆራረጠ ስለሚመጣ አንድ ባልዲ ውኃ ለመሙላት ደቂቃዎችን እንደሚወስድ የአካባቢው ነዋሪ በተወሰኑ ጀሪካኖች በርሜሉች ለመሙላት እሮብ ንጋት ድረስ ሲቀዳ እንደሚያድርም ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እዚያው አካባብ ሆኖ የተወሰኑ አካባቢዎች ኃይል ያለው ውኃ ሲያገኙ፣ ሌሎች እንደማያገኙ ይህም ከአሠራር ኢትፍሐዊነት እንደሚመነጭ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ሁልጊዜ ውኃ ይሰጠን›› የሚል ማንሳት ለአካባቢው ቅንጦት መሆኑን፣ ይህ ጊዜ እስኪመጣ ግን መንግሥት ሊያቀርባቸው ከሚገደድባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ዋና የሆነውን ንፁህ የመጠጥ ውኃ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሳይስተጓጎል እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው ተዘዋውረን ነዋሪዎችን እንዳነጋገርነው አካባቢው ላይ በተለይ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በፈረቃ የሚለቀቀው ውኃ በቀኑ እየለቀቀ አይደለም፡፡ ይህንን ቅሬታ ይዘው የአካባቢውን የውኃ ሥርጭት የሚመለከተው አካል ጋር ሲሄዱ ችግሩ እንደሚፈታ፣ ነገር ግን ከተወሰነ ዙር በኋላ መልሶ እዚያው እንደሚገባ ነግረውናል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ የውኃ አቅርቦት ችግር እንዳለ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ትልቁ ችግር ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል ነው፤›› ያሉን የአካባቢው ነዋሪ፣ ፈረቃቸው በደረሰ ጊዜ ውኃ አለማግታቸው ችግር እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡

በዋነኛነት የችግሩ ተጠያቂ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና የአካባቢው የውኃ ሥርጭት ክፍል ሠራተኞች እንደሆኑ፣ የአንድን አካባቢ ተራ ለሌሎች ቦታዎች አሳልፈው የሚለቁ ሠራተኞች መኖራቸውን፣ በአካባቢው ውኃ አልተለቀቀም እንዳይባል ኃይሉን ወይም መጠኑን በመቀነስ ለሌሎች አካባቢዎች ተራውን አሳልፈው እንደሚሰጡም ይገልጻሉ፡፡

በወረዳ አምስት አብዛኛው ማኅበረሰብ ውኃ በፈረቃቸውም ስለማያገኙ ለብዙ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን፣ ውኃ ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች አቅም የሌለው በጀሪካን አቅም ያለው ደግሞ እስከ 5000 ሊትር ውኃ እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከችግሩ የተነሳ የልብስና የዕቃ ማጠቢያ በድጋሚ ለአገልግሎት ለማዋል መገደዳቸውንም አክለዋል፡፡

ውኃ በጠፋ ቁጥር የሚያወጣው ወጪዎች ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት ነዋሪዎቹ መንግሥት የውኃ ታሪፍ ከፍ አድርጎ የሥርጭት መጠኑን ማሳደግ መቻል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎች ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ለመንግሥት የሚገባውን ገቢ ለሳምንታት የውኃ ግዥ እንደሚያውሉት፣ በዚሁ አካባቢ አንዳንድ ነዋሪዎች የውኃ መጠኑን ወይም ኃይል ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የውኃ ፓምፕ ገዝተው እየሳቡ የሚጠቀሙ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የውኃ እጥረትና የሥራ ዕድል

የውኃ እጥረት ችግር ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሠረታዊ ችግር ቢሆንም፣ ለአንዳንዶች ደግሞ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ምክንያት ሆኗል፡፡

ውኃ በቦቴ፣ በመኪና በተጫኑ አንድ ሺሕ ሊትር ውኃ በሚይዙ ማጠራቀሚያዎች እያመላለሱ ለነዋሪዎችና ለንግድ ቤቶች የሚያቀርቡት አቶ ቀፀላ ተወንድህ ለሦስት ዓመታት በዚሁ ሥራ ዘልቀዋል፡፡ ውኃ የሚቀዱት መስቀል ፍላወር፣ ብሔረ ጽጌ፣ ጎፋ፣ ጀሞና ለቡ አካባቢዎች ላይ ውኃ ተገዝቶ ለኅብረተሰቡ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡

የእሳቸው ሥራ ውኃ መሸጥ ሳይሆን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መሆኑን፣ በአይሱዚ መኪና ጭነው የሚንቀሳቀሱ ባለአንድ ሺሕ ሊትር አምስት የውኃ ማጠራቀሚያ እንዳሉዋቸው፣ የክፍያ መጠኑም በሚሄዱበት ቦታ ርቀት እንደሚወሰን፣ ከብሔረ ጽጌ የተቀዱትን ውኃ ለቦሌ አካባቢ አገልግሎት ቢሰጡ፣ እስከ 1,200 ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል፡፡

ውኃ የሚገዙዋቸው ደግሞ ሆቴሎች፣ መኖሪያ ቤትቶችና ሌሎች ተቋማት ሲሆኑ፣ ለተገልጋዮች እፎይታ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ውኃ ከጠፋ በቀን ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ ግለሰቦች እንደሚያቀርቡና ሳይሠሩ ውለው እንደማያድሩ አክለዋል፡፡

እንግዳ ማረፊያዎች፣ ግንባታ ሠራተኞችና ለአንዳንድ ባለሀብቶች ለመኖሪያ ቤታቸው አገልግሎት ፈልገው እንደሚደውሉላቸው ተናግረዋል፡፡ በአገልግሎታቸው ዝቅተኛው ክፍያ 1,200 ብር ሲሆን፣ ከለቡ የተቀዳ ውኃ ለሐያትና አካባቢው ሲቀርብ ከ1,500 ብር እስከ 1,800 ብር እንደሚጠየቁ አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ከ1,500 ብር እስከ 1,800 ብር ዋጋው ከፍ ማለቱን፣ ከዚህ ቀደም ግን ረዥም ኪሎ ሜትር ተጉዘው 1,200 ብር ብቻ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል፡፡

ከትልልቅ ሕንፃዎች ሥር የሚወጣውን ውኃ ከ150 ብር እስከ 200 ብር እንደሚገዙ፣ የዋጋው ልዩነት እንደ አካባቢው የመንገድ ሁኔታ እንደሚወሰን ጠቁመዋል፡፡

ውኃ በቦቴ መሸጥ ከጀመሩ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠሩት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ አባት፣ በዚህ ሥራቸው ለበርካቶች እፎይታ እንዳስገኙላቸው ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ውኃ የማይጠፋበት ቦታ እንደሌለ የሚገልጹት የቦቴ ውኃ አቅራቢ፣ የከተማው ነዋሪዎች በችግር ውስጥ መሆናቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የሚያቀርቡት ክፍያ እንደ ቦታው ርቀት እንደሚለያይ፣ ድርጅቶች፣ ፋብሪካዎች፣ ሆቴሎችና ለግል መኖሪያ ቤቶቻቸው የሚያስቀዱ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የከተማው ኅብረተሰብ ንፁህ፣ በቂና ዘላቂ የውኃ አቅርቦት በቀን ከ40 ሊትር እስከ 100 ሊትር ለማድረስ ዕቅድ ቢያዝም፣ በቀን አሥር ሊትር ውኃ አጥተው የሚንገላቱ ነዋሪዎች በከተማዋ ቁጥራቸው ከፍ ይላል።

በንጹህ የመጠጥ ውኃ እጥረት ችግር ተደጋጋሚ ወቀሳ የምታስተናግደው የአዲስ አበባ ከተማ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከስድስት ወራት ለሚበልጥ ጊዜ ንጹህ የመጠጥ ውኃ በቧንቧዎቿ እንደማይፈስ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

  የታሸገ ውኃ መግዛት የማይችል ሰው 20 ሊትር ጀሪካን አንጠልጥሎ ማየትም የተለመደ ሆኗል፡፡ እንደ ጀሪካን ያሉ የውኃ ማጠራቀሚያና መቅጃዎች በማይገባቸው ዋጋ እንደሚሸጡ፣ 20 ሊትር ባዶ ጀሪካን ከ180 እስከ ከ250 ብር እንደሚሸጡ በተለያዩ ገበያዎች ለማየት ተችሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የመካኒሳ ቅርንጫፍ የውኃ ስምሪትና መስመር ዝርጋታ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ አሳምነው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ታቦት ማደሪያ አከባቢ ያሉ ነዋሪዎች ውኃ የሚገኙት ከአጉስታና ከቃሊቲ ነው፡፡

በአካባቢው ውኃ ከሐሙስ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ፈረቃቸው መሆኑን፣ በመብራት መቋረጥና በሌሎች ምክንያቶች ካልተስተጓጎለ በስተቀር በፈረቃቸው እንደሚደርሳቸው አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡

አንዳንዴ የውኃ ኃይል መቆራረጥ ካጋጠመ የማሸጋሸግ ሥራ እንደሚሠሩ፣ ብዙ ጊዜ ቅሬታ የሚያቀርቡት ከፍተኛ ቦታዎች (አቀበት) ላይ የሚኖሩ መሆናቸውንና በቂ ውኃ ላያገኙ እንደሚችሉ፣ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች በበቂ ሁኔታ ውኃ ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ስልክ እንደሚደውሉ ሳምንታዊ ፈረቃ ላይ ሁለትና ሦስት ሳምንታት ውኃ ላላገኙ ቦታዎች የማሸጋሸግ ሥራዎች እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡

የወረዳ አምስት ነዋሪዎች የከርሰ ምድር ውኃ እንደሚያገኙ፣ ከአጉስታ ከቃሊቲና ከጦር ኃይሎች ከተቆፈሩ ጉድጓዶች እንደሚሠራጭ የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ በተለይ የከተማ መውጫ አካባቢ መደበኛ ያልሆኑ (ሕገወጥ) ቤቶች መኖራቸው፣ ነገር ግን ውኃ ማግኘት ሰብዓዊ መብታቸው በመሆኑ፣ በቦቴና በሮቶ እንደሚያደርሱላቸው ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የመካኒሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ሸዋንዳኝ እንደተናገሩት፣ ቅርንጫፍ አራት ክፍለ ከተሞች ያሉት ሲሆን፣ በ21 ወረዳዎች ላይ እየሠራ ነው፡፡

ለውኃ እጥረት በይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ተብለው በተመረጡ ቦታዎች 12 የከርሰ ምድር ውኃ መቆፈሩን፣ ዘጠኙ ኮልፌ፣ የተቀረው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እንደሚገኝ አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

የውኃ ሥርጭት የማይደርስባቸው ላይ ሦስት ቦቴ እንደሚያሰማሩ፣ ቦታዎቹም የውኃ አቅርቦትና ፍላጎት ያልተመጣጠኑ፣ ከፍታማ ቦታዎች (ኮልፌ ወረዳ 3) እነኚህ ላይ የውኃ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸዋል፡፡

አራት ክፍላተ ከተሞችን 21 ወረዳዎች ላይ በዋናነት ቅርንጫፉ የሚሠራባቸው ሲሆን፣ ከ92,000 በላይ ደንበኞች እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡

ከ360 የሚበልጡ ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ አባላት መኖራቸውን፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በስልክና በአካል በመገናኘት በጋራ መፍትሔ እንደሚበጅ ተናግረዋል፡፡

ከማኅበረሰቡ ከተወከሉት ጋር በየ15 ቀናት፣ በወር የዓመታዊ የሥራ ሒደት ግምገማ ጭምር እንደሚቀርቡላቸው አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰርካለም ጌታቸው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባለሥልጣኑ ለነዋሪዎች ሁለት የውኃ አማራጮችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

ከገፀ ምድርና ከከርሰ ምድር የተገኘ ውኃ ለከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚያደርሱ፣ ረዥም ጊዜ ያስቆጠሩ የለገዳዲና የገፈርሳ ግድቦች ዋነኞቹ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከገፈርሳ 30 ሺሕ ከለገዳዲ 180,000 ሜትር ኪዩብ የከርሰ ምድር ውኃን ጨምሮ፣ 644,000 ሜትር ኪውብ የማምረት አቅም ተፈጥሯል፡፡

በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ ወራት ላይ የከርሰ ምድር ውኃ በማስቆፈር በ86,000 ሜትር ኪውብ የውኃ አቅርቦቱን ቁጥር ከፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ፍትሐዊ የውኃ ስምሪት አለመኖር

ከተማዋ በእጅጉ እየተለጠጠች መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሰርካለም፣ ኢንቨስትመንት፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አንዳንድ ፋብሪካዎች ውኃን ለግብዓትነት የሚጠቀሙ ናቸው፣ የፍትሐዊነት ችግሩ የመጣውም የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቁጥርና የውኃ ምርቱ ሲሰላ፣ 1.2 ሚሊዮን ሜትር ኪውብ ውኃ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የሚያመርተው ደግሞ በቀን 644,000 ሜትር ኪውብ መሆኑን አስታውሰው፣ ችግሩ የመጣው ከፍተኛ የውኃ ፍላጎት መጨመርና የሚመረተው ውኃ አነስተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ውኃን በፍትሐዊ መንገድ ለማዳረስ በፈረቃ እየተሠራጨ መሆኑን ምክንያቱ ደግሞ አንዱ አካባቢ አግኝቶ ሌላው እንዳያጣ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ውኃን በፍትሐዊነት ለማድረስ የተደረገው ጥረትም፣ ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች በከተማው የተወሰኑ 220 የውኃ ጉድጓዶች በመቆፈር እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የውኃ ምንጮች እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች ውኃን በእኩል ለነዋሪዎች ለማድረስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ወ/ሮ ሰርካለም አስረድተዋል፡፡

በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያገኙ አሥራ አራት ወረዳዎች፣ በሳምንት ከሁለት ቀን እስከ ሦስት ቀናት የሚገኙ ደግሞ 88 ወረዳዎች እንዲሁም በሳምንት ከአራት እስከ አምስት ቀናት የሚያገኙ ስምንት ወረዳዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ሰርካለም እንደተናገሩት፣ በሳምንት ውኃ የሚያገኙባቸው ቀናት ከፍ ያሉባቸው ቦታዎች የውኃ አማራጮች በአቅራቢያቸው የሚገኙና ውኃ ካጡ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ እንደ ሆስፒታሎች፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድና መሰል ድርጅቶች ናቸው፡፡

ከ1000 በላይ ፈረቃ መኖሩን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ስምሪቱ በትክክል ለመፈጸም በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በሳምንት አንዴ የሚያገኙ አካባቢዎች በኤሌክትሪክ መቋረጥና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ፈረቃቸው እንደሚያልፋቸው የሌላውን ፈረቃ ለእነሱ ማድረግ ደግሞ ሥርዓቱን እንደሚያዛባ አክለዋል፡፡

በተለየ ሁኔታ ውኃ የማይመጣላቸው ቦታዎች የጨረቃ ቤቶች አካባቢዎች መሆናቸውን፣ በከተማ ጫፍ ዳርቻ ላይ ባለሥልጣኑ የውኃ ሥርጭት ጣቢያ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

ውኃ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች በባለሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡ እንደሚገመገሙ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ለውኃ ሥርጭት ኤሌክትሪክ ወሳኝ መሆኑን፣ ትልቁ ችግር የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የመስመር ስብራት፣ የፓምፕ መበላሸትና በሌሎች ምክንያቶች የፈረቃ ውኃ ሥርጭትን ከሚያስተጓጎሉ ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በፈረቃ ሥርጭት ሠራተኞች የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው በወሬ ደረጃ እንደሚሰማ፣ ሆኖም የውኃ የሥርጭት ሥርዓቱ ለአንድ ተሰጥቶ ለሌላው መከልከል የሚቻል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ከማኅበረሰቡ ጋር በነበረው ብዙ ስብሰባዎች የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ጠቁሙ ሲባሉ ምላሽ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን በወሬ የሚናፈሱ የሥነ ምግበር ጥሰቶችን እንደሚሰሙ ጠቁመዋል፡፡

በውኃ ሥርጭት ላይና በሠራተኞች የሥነ ምግባር ጉዳይ አስተያየትና ቅሬታ ያለው ‹‹906›› የነፃ መስመር ላይ በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ፣ ባለሥልጣኑም አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡

የውኃ እጥረትን ለመቅረፍ

የአዲስ አበባ ውኃ አቅርቦትን ለማስተካከል ለገዳዲ ክፍል ሁለት ውኃ ፕሮጀክት ከ16 ጥልቅ ጉድጓዶች 86,000 ሜትር ኪውቢክ የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለገዳዲ ክፍል ሁለት 10 ማሠራጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ከ2000 እስከ 5000 ሜትር ኪውቢክ ውኃ የሚይዙ፣ 186 ኪሎ ሜትር የውኃ መስመር ዝርጋታ እንዳለው ገልጸወል፡፡

ፕሮጀክቱ ከየካ ክፍለ ከተማ እስከ ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚኖሩ ዜጎችን የውኃ ችግር የሚቀርፍ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሪክ ያልገባ በመሆኑ ሁሉም ዜጎች እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡

ሌሎችም ትልልቅ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን፣ የገንዘብ ማፈላለግ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ፣ መገርቢ ግድብ የገንዘብ እገዛ ተገኝቶ በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑን በተለይ በግድቡ ምክንያት ለሚፈናቀሉ ዜጎች የካሳ ክፍያ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...