Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መራራ ትግል!

ሰላም! ሰላም! ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የሰላምና የነፃነት ጉዳይ የሚያንገበግበው ከእጃችን ሲወጣ ነው…›› እያለ በአለፍ ገደም የሚነግረኝን ሳስታውስ ሰላም መባባል ተራ ሰላምታ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ለሰላም ሲባል በሚከፈል መስዋዕትነት ነፃነት እንደሚገኝ ሳስብም፣ ይህንን የመሰለ ዕንቁ ነገር የመንከባከብ ኃላፊነት የእኔም ሆነ የእናንተ ኃላፊነት እንደሆነም እገነዘባለሁ፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን ከከበሩ ጌጣ ጌጦችና ከተለያዩ ንብረቶች በላይ ለመጠበቅ መትጋት ያለብን፡፡ መቼስ አንዳንዴ ዓለም ምን መልካም ብትመስል ሰው ሐሳብና ቢጤ ሲያጣ ውስጡ ይታወካል። ውስጣችን ሲታወክ ደግሞ ድባቴ ይይዘናል፡፡ ከዚህ ይሰውራችሁ ነው የሚባለው። እንደምታውቁት ድባቴ ሲኖርብን አዕምሮአችን ስለሚነካ የምናደርገውን አናውቅም። ጊዜው ደግሞ እንደምታውቁት በአይጥ መርዝ ድመት የማሰናበት አባዜ ተጣብቶታል። አንዱ ለራሱ የአይጥ መርዝ ሊገዛ ሱቅ ደፍ ላይ ደረሰ አሉ። ‹‹ባለሱቅ የአይጥ መርዝ አለህ?›› ይላል። ባለሱቅ ደግሞ፣ ‹‹የአይጥ ወጥመድ ብቻ ነው ያለኝ…›› ሲለው በገዛ ፈቃዱ በገዛ ገንዘቡ ሊሰናበት የተሰናዳው ሰውዬ በሳቅ ፈረሰ። እንግዲህ እዚህ ላይ ሰንብች ያላት ነፍስ ለካ በሞላ ገበያ ብቻ ሳይሆን በጎደለም ትሰነብታለች፡፡ የጎደሉብን ነገሮች እንዲሟሉ ፀሎት ማቅረብ የእኛ ፋንታ ነው። ፀሎታችን ሲሰማ ደግሞ ለላይኛው ጌታ ምሥጋና ማድረስ ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ከዘወትር ፀሎታችን ጎን ለጎን ምሥጋና ማቅረብ የዘወትር ተግባራቸው የሆኑ አማኞች ብፁዓን ናቸው…›› የሚሉት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። እሳቸው እህ ከተባሉ ብዙ ይላሉ!

ብቻ እኔ የፀሎትና የምሥጋናን ጉዳይ ያነሳሁት አንዳንዴ ባላሰብነው መንገድ፣ ለበጎ የሚለወጡልንን ሁኔታዎች በማሰብ ተጠምጄ ስለሰነበትኩ ነው። ታዲያ ሲያቀብጠኝ በቀደም ለባሻዬ ልጅ በጎደሉብን ነገሮች ምትክ የምናገኛቸውን በጎ ነገሮች ላመሳክር ባነሳበት ከአፌ ነጥቆ፣ ‹‹በል እስኪ በያዘ አፍህ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን እንደ ምሳሌ አድርገህ ለበጎ የሆነበትን መንገድ አስረዳኝ…›› ሲለኝ አፌ ተሳሰረ። ወዲያው ግን ከየት እንዳመጣሁት አላውቅም፣ ‹‹ለምሳሌ ከሥራ ወጥተህ ሊፍት ውስጥ ገብተህ ከአሥረኛ ፎቅ ወርደህ ጨርሰህ አስፋልት ለመሻገር በምትደርስበት የአፍታ ያህል ደቂቃ ውስጥ፣ አንድ ፍሬን የበጠሰ መኪና ሊደፈጥጥህ እየተቅለበለበ እየመጣልህ ይሆናል። ነገር ግን ስድስተኛ ፎቅ ላይ ስትደርስ ኤሌክትሪክ ጠፋ። አሳንሰሩ ለጥቂት ደቂቃ ቆመ። በተዓምር ተረፍክ ማለት አይደል?›› ስለው በሳቅ አሽካክቶብኝ ሲያበቃ፣ ‹‹ይህች ቲቪ ላይ ያየሃት ድራማ ናት…›› ብሎኝ አረፈው። ገሃዱና ምናቡ እየተምታታ ለምሳሌ የማይመች ጊዜ ላይ ደርሰን ቸገረን እኮ እናንተ፡፡ ለማንኛውም ወደ ፈጣሪ ፀሎት ማድረስም ሆነ ምሥጋና ማቅረብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም፣ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ማመሥገን መልካም ነው፡፡ ፈጣሪያችንን ስናስታውስ ከተቃጣብን አደጋ እንደምንተርፍ ያለፍንባቸውን ክፉ ዓመታት ዞር ብሎ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ አይደለም እንዴ!

በቀደም አንዱ ሲክለፈለፍ የደላሎች ድድ ማስጫ መጥቶ ዳታው ተጭበረበረ ስለተባለው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ጉዳይ፣ ‹‹ሰበር ዜና አለኝ…›› ሲል አንድ አንጋፋ አራዳ ደላላ፣ ‹‹ወገብ ዛላህ ይሰበርና የምን ሰበር ነው? ይህንን የለዘዘ ወሬህን ትተህ ዋናው ሰው የት እንዳሉ ለምን አትነግረንም…›› ብሎ ቆሌውን ገፈፈው፡፡ አጅሬው አያርመውምና፣ ‹‹እንዴ እሳቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አናውቅም እንዳትሉ ብቻ…›› ብሎ የነገር ድሩን ሲዘረጋ፣ ‹‹አንተ ወሽካታ የሲኤንኤንና የአልጄዚራ ርዝራዥ የአልቃይዳው አለቃ አይማን አልዘዋህሪን አሜሪካ እንዴት ደርሳበት እንደገደለችው ለምን አትዘግብልንም…›› ብሎ ሲያፋጥጠው፣ ‹‹አሜሪካማ ልትገድለው የቻለችው…›› እያለ ወሬውን ሊለቀው ሲል ዶፍ ዝናብ መጥቶ ገላገለን፡፡ እኔ በዚህ መሀል የገረመኝ ግን የእኛዎቹ አክቲቪስቶችም እንደዚህ ማይም ደላላ ወሬውን ከደረት ወይም ከኋላ ኪሳቸው መዥረጥ እያደረጉ የሚተነትኑ ነው የሚመስለኝ፡፡ አንድ ጊዜ የአንዱን ታዋቁ ተብዬ አክቲቪስት የዩቲዩብ ትንተና ስሰማ ብቻዬን ነበር እንደ ዕብድ የሳቅኩት፡፡ ሰውየው ከእሱ በስተቀር አዋቂ የሌለ እስከሚመስል ድረስ፣ ‹‹በወቅቱ ልብ አላላችሁም እንጂ ሩሲያና ዩክሬን በቅርቡ ጦርነት ጀምረው ዓለም የነዳጅና የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥመው ከማንም በፊት የተናገርኩት እኔ ነበርኩ…›› እያለ ሲተረተር አንዱ በአስተያየት መስጫው፣ ‹‹እውነትህን ነው ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊትም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ማርያም እንደሚወለድ አንተ ነበርክ ትንቢት የተናገርከው…›› ያለውን አንብቤ እንዴት አንጀቴ እንደ ራሰ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

አሁንማ ትንቢት ተናጋሪ ነን የሚሉ ሐሰተኛ ነቢያትና አደናጋሪ አክቲቪስት ተብዬዎች እንደ ልባቸው በሚፈነጩባት ኢትዮጵያ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ እንደ መንጋ ሲነዱ ሳስተውል ከመገረም አልፌ እበሳጫለሁ፡፡ ድሮ የአራዳ ልጆች ሲሰርቁም ሆነ ሲዋሹ ከተነቃባቸው፣ ‹‹በቃ እንዳላየህ ሆነህ እለፍ…›› ይሉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ከአራድነት ጋር የማይተዋወቁ ከተሜ አይሏቸው ገጠሬዎች ግን ለዘመኑ የማይመጥኑ ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው ይኩራራሉ፡፡ አንድ ቀን የአሰላሳዮችን የፌስቡክ ገጾች ሳስስ አንዱ የአራዳ ልጅ ስለአራድነት የከተበውን አነበብኩ፡፡ እስቲ እናንተም አጣጥሙት፡፡ ‹‹”አራዳ” ማለት ምን ማለት ነው? ነገሮችን ቀለል አድርጎ ለማየት የማይከብደው፣ ለማናገር፣ ለመጠየቅ፣ ለማዘዝ የማይከብድ፣ ቀላል ሰው፣ ስለምንም ነገር ብታወራው የማያካብድ ነፃ ሰው፣ ከሴራና ከአጉል ነገሮች የፀዳ ምርጥ ሰው፣ አዛኝና ትሁት (ትዕቢተኛም ሆኖ ደግ) ሰው ነው፡፡ ሰውን ማስከፋት የማይወድ፣ የተሰማውን የሚያሳይ፣ ልቡ ጫካ ያልሆነ፣ ለራሱ ተመችቶት መኖርን፣ ለሌላውም ደግሞ ተመችቶት እንዲኖር የሚመኝ፣ የቻለውን የሚያደርግ፣ ምርጥ ትሁት ቀላል ሰው፣ ለእኔ የአራዳ መጨረሻ ነው፤›› ነበር የሚለው፡፡ ጎበዝ የገዛ ወገኑን እንደ በግ አጋድሞ ለማረድ ከሚፈልግ ወፈፌ ጀምሮ፣ አዳራሽ ሙሉ ሰው ሰብስበው ከፈጣሪ በላይ የሆኑ ያህል በፈውስና በተዓምር ስም ከሚያጭበረብሩ የዘመኑ ይሁዳዎች ከተሜው አራዳ በስንት ጣዕሙ ያሰኛል፡፡ አይደለም እንዴ!

እስቲ ደግሞ ወደ ሌላ ጉዳይ እናምራ። ሲያቀብጠኝ ያለ ዕውቀቴ ስለፍልስፍና የሚወራበት ውይይት ላይ ዘው ብዬ ገባሁ፡፡ እኔ መቼም ሲፈጥረኝ ከአቋራጭ ሀብት ይልቅ ዕውቀት ስለሚናፍቀኝ እዚህ የተገኘሁት በዚያ ስሜት መሆኑን ተረዱኝ፡፡ የፍልስፍናው ውይይታችሁ እንዴት ነው ብዬ የባሻዬን ልጅ ማብራሪያ ስጠይቀው፣ ‹‹እንዴት ብሎ ነገር ምንድነው? ሰው እኮ በእህልና በውኃ ብቻ አይኖርም። መንፈሱን የሚያድስበት፣ የሚናፈስበት፣ የሚዝናናበት ሥፍራና ክንዋኔ በገፍ የሚያስፈልገው ፍጡር ነው። እነ ሮም፣ እነ አቴና፣ እነ ባበቢሎን ለልዩ ልዩ ጨዋታዎችና መዝናኛዎች የከለሉዋቸውን ሥፍራዎችና የገነቧቸውን አስደናቂ ስታዲዮሞች አስታውስ። እኛ ግን ሐሳባችን ሁሉ ከእጅ አይሻል ዶማ ሆኖ ይኼው የብሔርና የሃይማኖት ልዩነት ይሰበክልሃል፡፡ የልዩነት ስብከቱን ተከትሎ ደግሞ ደም የጠማቸው አውሬዎች ወገኖቻችንን ይፈጃሉ፡፡ በሐዘን አንገትህን አቀርቅረህ ከዕንባህ ጋር ስትታገል የመጠጥና የዳንኪራ መሰናዶ ማስታወቂያ ያዋክብሃል። እንዴት ማለት ምንድነው?›› ሲለኝ ነቃሁ። ለካ እኔ ዞሮብኝ ጥልቅ የፍልስፍና ውይይት መሰለኝ እንጂ፣ እነሱ የያዙት ወግ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ከወደፊት ተስፋችን ጋር ያቆራኘውን ሰቆቃችንን ነው፡፡ ወይ የደላላ ጭንቅላት፣ አንዳንዴ እኮ እንደ ተነፈሰ ጎማ ነው የሚያደርገኝ፡፡ ንቃ አትሉኝም!  

እንግዲህ ከዚህ በመለስ ያለው የጎጆ ጣጣችን ይሆናል። አንዱን በዓል ስንሸኘው ሌላው ከተፍ ሲል ትንፋሽ ሳይሰጥ ሆኗል። ቀን ምን አለበት? አወይ ጊዜ እንዲህ እልም እልም ሲል፣ እሱም ለአንድ ቀን ሰው ሆኖ ባየው ያስብላል። እውነቴን እኮ ነው። ያስለመድነው ደግሞ አይረሳም። ዜማና ኑሯችን የተቃኘው በትዝታ ቅኝት ነዋ። ማንጠግቦሽ የፍልሰታ ፆም ገና ከመጀመሩ ለአዲሱ ዓመት ከወዲሁ ማሰብ ጀምራለች፡፡ ‹‹አሮጌ ዓመት አልፎ አዲሱ ሲተካ በሁላችንም ልብ ውስጥ ተስፋ ይኖራል፡፡ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ከአንድ ወር በላይ ቢቀርም የዘንድሮ የኑሮ ውድነት አያላውስምና ተፍ ተፍ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ድሮ ሙክት ጥለን፣ የበሬ ቅርጫ አክለንበት፣ ዶሮ ተጨምሮበት፣ ጠላው፣ ጠጁ፣ ቢራውና ከተገኘም ውስኪ ደማምረንበት የምናከብረው በዓል ትዝታው አይጣል ነው…›› የሚለኝ አንድ ደላላ ወዳጅ አለኝ፡፡ ‹‹ዘንድሮ እንደዚህ በቅንጦት የምናከብረው በዓል ባይኖርም፣ ካለችን ላይ ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉ በሥውር ለሚራቡ ሰዎቻችን ሳይቀር መተባበር አለብን…›› የሚለኝ ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ አዛውንቱ አባቱ ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹ደስታ የሚገኘው ብቻችን በመብላትና በመጠጣት ሳይሆን በማካፈል ውስጥ ነው…›› ይሉኛል፡፡ ይህንን የሰማችው ውድ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹አንበርብር ለበዓሉ ከወዲሁ እንዘጋጅበት ያልኩህ እኮ ለእኛ ደስታና ፈንጠዚያ ሳይሆን ለወገኖቻችን ለመትረፍ ጭምር ነው…›› እያለች የደግነትን ጥግ ስታመላክተኝ ውስጤ በደስታ ይጥለቀለቃል፡፡ ይብላኝ ሀብት ቢያግዙ ለማይጠረቁና በሰቀቀን ለሚኖሩ ሀብታም ተብዬ ስስታሞች እንጂ፣ የእኛ ሰው እኮ ማንም ወገኑ እንዲራብበትም ሆነ እንዳይጠማበት እንደማይፈልግ ለመረዳት ወጣ ብሎ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!

እንሰነባበት መሰል። በዚህ ዘመን ጥቂቶች ቢከፉም ብዙኃን ልብ ውስጥ ክፋት ከሌለ የማይታለፍ ችግርም ሆነ መሰናክል የለም፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር፣ ኢትዮጵያ የምትባል ታሪካዊት አገር በፈጣሪ ቸርነት እስካሁን በዓለም ደምቃ የምትኖረው ስንቱን መከራና ችግር ተሻግራ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ክፉዎች ድሮም ነበሩ፣ ዛሬም ይኖራሉ፣ ነገም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ደጎች ስለሚበልጧቸው ልክ እንደ ጥላ እነሱም ውልብ ብለው ያልፋሉ፡፡ ታሪክም እዚህ ግባ የሚባል ቦታ ስለማይሰጣቸው ተወላጆቻቸው በኃፍረት ሲሳቀቁ ይኖራሉ…›› እያሉ ሲያስረዱኝ፣ ክፋት የሚባለው ነገር ምናልባት ጊዜያዊ ተድላ ይዞ ይመጣ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ አለመሆኑን እያሰብኩ መብሰልሰል ጀመርኩ፡፡ በታላቁ የዓድዋ ጦርነት በጀግንነት ለአገራቸው የተዋደቁ ጀግኖችና ታሪክ በክብር ሲዘክራቸው ተወላጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በየዘመኑ የነበረው ትውልድ እንዴት እንደሚያከብራቸው ሳስብ ክፋት ከንቱ ነገር እንደሆነ ነው የገባኝ፡፡ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ ሲፈጽም በጀግንነት አገራቸውን ያኮሩ ጀግኖች አርበኞችን በኩራት ሳስታውስ፣ ለፋሽስቶች በባንዳነት አድረው የነበሩ ግለሰቦች እንዴት በኃፍረት ይሸማቀቁ እንደነበሩ አይዘነጋኝም፡፡ ለአገር ደግ መዋል ማለት ወገንን ማክበርና መደገፍ ማለት ነው፡፡ ይህንን ሳይገነዘቡ ክፋት ውስጥ መዳከር ትርፉ ውርደት ነው፡፡ ወገንን መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማሳደድ፣ መዝረፍ፣ ማስራብ፣ በዋጋ ጭማሪ ማጎሳቀል፣ ከመጠን በላይ በማትረፍ መበልፀግ፣ ምርት መደበቅ፣ አገልግሎት መንፈግ፣ ፍትሕ መንፈግና አድልኦ መፍጠር አሳፋሪ ክፋቶች ናቸው፡፡ በቃ ይባሉ! 

የአገር ጉዳይ ሲነሳ ብዙ የሚያነጋግር በመሆኑ ለማሳረጊያ የሚሆን ጉዳይ ላንሳ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ዘንድሮ በሕዝብ ስም እየቆመረ በማያውቁት አገር ቁርበት የሚያስነጥፍ አስመሳይ ቁጥሩ እየጨመረ ነው… የአገር መሠረቱ ቤተሰብ ሆኖ ሳለ፣ አወቅን ባዩ ሁሉ ነገር ዓለሙን በፖሊሲ ለውጥና በፖለቲካ አቋም ብቻ ካላጠራሁ ሲል ነው እኮ የሚገርምህ… ራሱ ነፃነት ሳይኖረው ለቤተሰቡ፣ ለትዳር አጋሩ ነፃነት የሚነፍገው ሁሉ ደርሶ ስለነፃነት ሲቀባጥር ማየት ይታክተኛል… የቤት ሠራተኛውን በሰብዓዊ ክብር ዓይቶም ይዞም የማያውቅ፣ ደርሶ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲቀባጥር ይተናነቀኛል… በሠፈራችን፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየመዝናኛውና በደረስክበት ቦታ ሁሉ የራሱን ጉድፍ ሳያጠራ የሰው እንከን የሚታየው መብዛቱ ያሳቅቀኛል… ሰው እንዴት ለሥራ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ሳይነሳ የሚሠራ ይተቻል… ዲግሪውን ከተቀበለ በኋላ የረባ መጽሐፍ አንብቦ የማያውቅ ወይም አንዲት አንቀጽ ያልጻፈ እንዴት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተንታኝ ይሆናል… እንኳን በአገር ጉዳይ ለመተቸት የገዛ ኩሽናውን የማያውቅ ደፋር ያለ እኔ ማን አለ ማለት ይችላል… ትናንት ለአምባገነኖች አጎብድዶ ወይም አንገቱን ደፍቶ ይኖር የነበረ ፈሪ በምን መመዘኛ ነው ዛሬ የጀግንነት ሜዳሊያ ካልተሰጠኝ ብሎ የሚንጎማለለው… ለሰላም ቅንጣት አስተዋፅኦ ሳይኖረው የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት ይገባኛል ከሚል ወሮበላ ዓይነት ጋር እኮ ነው መራራ ትግል የገጠምነው…›› እያለኝ ብዙ አወጋኝ። እውነቱን ነው ትግላችን መራር ነው! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት