ከአዲስ አበባ በደቡብ ምሥራቅ በኦሮሚያ ክልል 403 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች የባሌ ዞን ሰፊውን መሬት ይዟል፡፡ ዞኑ በዓመት ከፍተኛ የዝናብ መጠን መኖሩን ተከትሎ ግብርና የበርካቶች መተዳደሪያ ነው፡፡ በተለይ በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ በከፍተኛ የስንዴ ምርት ይታወቃል፡፡
የዞኑ መልክዓ ምድር ለም፣ የባሌ ተራሮች ደግሞ በቱሪስት መስህቦች የታደሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም በርካታ ቱሪስቶች ሲያስተናግድ ይውላል፡፡ በዞኑ ከተሞች የመኸር ወቅትን ጠብቀው ወደ እርሻ የሚሰማሩ በጭቃ የቦኩና መንገድ ጥግ ይዘው የቆሙ ትራክተሮችን ማየት የተለመደ ነው፡፡
ባሌ ሮቤ ከተማን ለቀው በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 577 ኪሎ ሜትር ሲርቁ፣ በባሌ ዞን ከሚታየውና ከሚነገረው የእህል አምራችነት ዜና የተቃረነ ሁኔታ ይመለከታሉ፡፡
ከደሎ መና ከተማ 56 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው በከሌ ጎልባ ቀበሌ በረሃማ ሥፍራ ላይ እዚህም፣ እዚያም በጭራሮ ከተሸፈኑ ዳሶች ውስጥ የመኪና ኮቴን የሰሙ ሕፃናት ብቅ ብቅ አሉ፡፡
ከታች በቀይ አፈር ከላይ ከበረሃ ጭራሮ በተሸፈነው ሥፍራ ላይ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሊበረከትላቸው የተሰናዳውን መሠረታዊ ቁሳቁስ ለመረከብ በረድፍ ተሰባስበው የተቀመጡ አባ ወራዎችና እማ ወራዎች ይታያሉ፡፡ በሥፍራው ላይ ከሚገኙት ጎልማሶች በቁጥር የማይተናነሱ ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ 12 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት እዚያም እዚህም ቆመው የሚሆነውን ይታዘባሉ፡፡
ወደ ደሳሳዎች ገባ ሲሉ በጭራሮ ርብራብ በተሠራ ላይ የተኙና ከሕመማቸው ጋር ትግል የገጠሙ አዛውንቶችና ነፍሰ ጡር እናቶች ይታያሉ፡፡ ዜጎቹ ከወር በፊት የኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ ክልል ጋር ከሚዋሰንባቸው ስድስት ወረዳዎች በአንዱ የሞቀ ኑሮ ነበራቸው፡፡
ወ/ሮ ሐመቱ ሀጂበከር 32 ዓመታቸው ሲሆን፣ የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ሁለቱ ክልሎች ከሚዋሰኑበት በጉራ ዳሞሌ ቀበሌ ከባለቤታቸው ጋር ሆነው በከብት ዕርባታና በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይኖሩ ነበር፡፡ በአዋሳኝ ድንበሩ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ከተፈናቀሉበት ቀበሌ አሁን ወደ ተጠለሉበት ከሌ ጎልባ ቀበሌ ለመድረስ ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ሁለት ቀናት እንደፈጀባቸው ያስረዳሉ፡፡ ልጆቻቸውን ይዘው ለመሸሸም ከሰዎች አህያ ትብብር ጠይቀው እንደነበር ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በአዋሳኝ ድንበሩ ላይ የታጠቁ ኃይሎች መኖራቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ሐመቱ፣ ቀበሌያቸው ለሦስት ወራት በታጣቂዎች ከበባ ሥር ወድቃ፣ የሚላክላቸውን የምግብ ዕርዳታ እንዳያገኙና ገበያ ወጥተው የሚፈልጉትን እንዳይሸምቱ መደረጋቸውን ያነሳሉ፡፡
በደሎ መና ወረዳ ከጉራ ዳሞሌ ቀበሌ ተፈናቅለው፣ በከሌ ጎልባ ቀበሌ የሠፈሩት 8,759 ዜጎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 1,040 አባ ወራዎች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ሕፃናትም ከአዛውንቶቹ ጋር ያልተናነሰ ቁጥር አላቸው፡፡
በጉዞ ወቅት ልጆቻቸው በሕመም ምክንያት ሲሰቃዩባቸው እንደነበረ የሚያስታውሱት ወ/ሮ ሐመቱ፣ አሁን ባረፉበት ቦታ ከደረሱ በኋላ የሩዝና የዱቄት ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት ረዥም መንገድ እንደሚጓዙና ለዚህም የሚጠቀሙባቸው አህዮች በረሃብ ምክንያት እየሞቱባቸው በመሆኑ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ያስረዳሉ፡፡
ወ/ሮ ሐመቱ መንግሥት ብድር አመቻችቶላቸውና ንግድ ጀምረው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚፈልጉ አክለዋል፡፡
አቶ መሐመድ አደም ሮባ የ62 ዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ አዛውንቱ በጉራ ዳሞሌ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ሆክልቱ ቀበሌ ነዋሪ ነበሩ፡፡ ከሁለት እማወራዎች 12 ልጆች አፍርተዋል፡፡ በዋነኛነት በከብት ዕርባታ የሚተዳደሩት አቶ መሐመድ አካባቢው የዝናብ እጥረት ሲያጋጥመው ከብቶቻቸውን እየሸጡ ቀለብ ሸምተው ቤተሰባቸውን እንደሚመግቡ ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ መሐመድ አስተያየት፣ በወረዳቸው የሚገኘው የግጦሽ መሬት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወረረና እየተስፋፋ ከ30 ዓመታት በላይ የግጭት ቀጣና ሆኖ መክረሙን ያስታውሳሉ፡፡
‹‹በሰላሙ ጊዜ በወረዳችን የሚገኘው መሬት ለግብርና እንዲሁም ለግጦሽ እየተጠቀምን ስንኖር ነበር፡፡ ምንም እንኳን የድንበር ግጭቱ እየጠፋ፣ እየበራ ለሦስት አሠርት ዓመታት የተሻገረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቀጣናው የተኩስ ድምፅ ሳይሰማ የማይታደርበት ሆኖ ሰንብቷል፤» በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ፡፡
በተለይ ዋብረ ጉና በሚባለው አካባቢ መስጊድና መኖሪያ መቃጠሉንና በርካታ ከብቶች እንደወደመባቸው አቶ መሐመድ ይናገራሉ፡፡
«ከሁለት ቀናት በላይ በወሰደብን ጉዞ መንገድ ላይ የሞቱብንን እየቀበርን፣ የታመሙብንን እያስታመምን አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈን ነው የደረስነው፤» ሲሉ አቶ መሐመድ ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡
እንደ አቶ መሐመድ አስተያየት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በደሎ መና ከሌ ጎልባ ሲደርሱ አራት ሰዎች እንደሞቱባቸው አልሽሸጉም፡፡
በከሌ ጎልባ ያረፉት ተፈናቃዮቹ ሕፃናትና አዛውንቶች ከፍተኛ ጉንፋን በሽታ መግባቱንና ነፍሰ ጡር እናቶች በመኖራቸው በቂ መድኃኒትና ሕክምና እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በአካባቢው የመፀዳጃ ቦታን ለመሥራት ቁሳቁስ በማጣታቸው ለከፋ ችግር እየተጋለጡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዕድሜያቸው ከሰባት ወራት በታች የሆኑ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብና መድኃኒት በማጣታቸው እየተጎዱባቸው እንደሆነና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሱ አቶ መሐመድ ሥጋታቸውን አክለዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች ግጭት ምክንያት ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በዞኑ አምስት ቀበሌዎች ላይ የሠፈሩ ሲሆን፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መሠረታዊ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መቆየታቸው ታውቋል፡፡
ከወር በፊት በባሌ ዞን በደሎ መና ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ183 ሺሕ ዩሮ በላይ ከአውሮፓ ኅብረትና ከአይሪሽ ኤድ በተገኘ ድጋፍ፣ የዓለም አቀፍ ሪስኪዩ ኮሚቴ አማካይነት መሠረታዊ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
በዚህም ለ1,040 አባዎራዎች ለመጠለያ የሚሆን ሸራ፣ 17 ዓይነት የቤት ቁሳቁሶች እንዲሁም የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ድጋፍ በቀዳሚነት ማድረስ መቻሉን ሆኖም የጤና፣ የውኃና የተጨማሪ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮቹ አሳስበዋል፡፡
ለጊዜውም ቢሆን የተፈናቃዮቹ በሕይወት የመኖር ዕጣ ፈንታ በዕርዳታ ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም፣ የእነ አቶ መሐመድና ሐመቱን ህልም ግን ከተረጂነት ወጥተው ወደ ሥራ መመለስ ነው፡፡
«ለጊዜው የሰዎችን ዕርዳታን እየተጠባበቅን ለመኖር ብንገደድም ተረጂ ሆነን መቀጠል አንፈልግም፡፡ የእርሻ መሬት ተዘጋጅቶልን በግብርና፣ በከብት ዕርባታና በንግድ ላይ ተሰማርተን ከተረጂነት መውጣት እንፈልጋለን፤» ሲሉ አቶ መሐመድ ፍላጎታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በሚፈጠር ግጭት ሳቢያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ሸሽተው በመጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን ችግር ለመፍታት በርካታ መድረኮች ተሰናድተው ምክክር ቢደረግም መፍትሔ ግን ሊበጅለት አልቻለም፡፡