ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሥልጣን በተነሱት የቀድሞ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ምትክ ለአምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) የኮሚሽነርነት ሥልጣን ሰጡ፡፡
የኮሚሽኑ ምንጮች ሪፖርተር እንዳረጋገጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ኮሚሽኑ የላከው ደብዳቤ አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) ከሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ኮሚሽነር ሆነው እንደተሾሙ አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትርና ትምህርት ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደርና እንዲሁም የሌሴቶና ናሚቢያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡