Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የአፈጻጸም ጉድለት የታየበትና 33 በመቶ የደረሰው የዋጋ ግሽበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሁሉም የማክሮ አመላካቾች እመርታ ብታስመዘግብም፣ የአፈጻጸም ጉድለት ታይቶበታል የተባለው የዋጋ ግሽበት በአማካይ 33 በመቶ መድረሱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱን ይፋ ያደረገው የሐምሌ ወር የሸማቾች ኢንዴክስ እንደሚያሳየው፣ በአገሪቱ ከሐምሌ 2013 እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. በነበረው ወቅት ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33.7 ከመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገበው አማካይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 40.2 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የነበራቸው የዋጋ ግሽበትም 25 ከመቶ እንደነበር አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ለችርቻሮ ዋጋ ጥናት የሚያግዙ 119 የተመረጡ የገበያ ቦታዎች መሠረት ተደርጎ የሚቀርበው የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ የሐምሌ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱም ሆነ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆነው የግሽበት ሁኔታ አሁንም በ30ዎቹ ውስጥ ይገኛል፡፡

የዋጋ ግሽበት በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባደጉ አገሮች ጭምር ፈተና እየሆነ መምጣቱን ያስታወቀው የስታትስቲክስ አገልግሎት፣ ‹‹ካለው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የኢኮኖሚ ሁኔታና ሌሎች ፈታኝ ሁኔታዎች አንፃር በሐምሌ 2014 ዓ.ም. የታየው የዋጋ ግሽበት መልካም የሚባል ነው፤›› በማለት ገልጾታል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ፈተና ውስጥ ተሆኖ፣ በማክሮ ኢንዲኬተርስ ከዋጋ ንረት በስተቀር የተገኘው እመርታ ይበል የሚያስብል መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በሐምሌ ወር የምግብ የኢንዴክስ ክፍሎች መጠነኛ መረጋጋት ማሳየታቸውን የሚሳየው የአገልግሎቱ ሪፖርት፣ በአንፃሩ ምግብ ያልሆኑ የኢንዴክስ ክፍሎች ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ አሁንም እያሻቀበ እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳ ቁሶች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉትና ዋና ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ በአልኮልና በትምባሆ፣ በልብስና ጫማ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች ተብለው በሚመደቡት የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ኪዳን ቆርቆሮ፣ የቤት ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ሕክምናና ጌጣ ጌጦች የተመዘገበው የዋጋ ንረት ይጠቀሳል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ በመደረጉ ከውጪ በየብስ ትራንስፖርት ተጓጉዞ የሚመጡ የውጭ ምርቶች ለማስገባት የዋጋ መጨመር ከመኖሩ ባሻገር፣ የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ በሚፈጠሩት የዋጋ ትርምሶች ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ስለሚጎዳ፣ የመሠረታዊ ቁሳ ቁሶች አቅርቦትን መንግሥት በተጠናከረ ሁኔታ መምራት እንዳለበት በኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚሰነዘር አስተያየት ነው።

ነዳጅን ሰበብ አድርገው የሚፈጠሩ አዳዲስ ዋጋዎች መደበኛ ዋጋ መሆን ስለሚጀምሩ፣ ቅድሚያ የመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሥርዓት በማበጀት የዋጋ ጭማሪ እንዳይለመድ መደረግ እንዳለበት ይገለጻል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተጠናቀቀው ዓመት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ማብራሪያ ያቀረቡት የፕላንና የልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ የዋጋ ግሽበት በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ፣ ዓለም አቀፋዊ ይዘት በመያዙና የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትም ከዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ጋር ቁርኝነት ያለው በመሆኑ ተፅዕኖው በግልጽ የሚታይ ሆኗል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሠረታዊ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ክስተቶች ግን የዋጋ ንረቱን በሚፈለገው ልክ እንዲረጋጋ እንዳላደረጉ አስረድተው ነበር፡፡

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትም የነዳጅ፣ የምግብና የሌሎች የሸቀጣ ሸቀጦች ዓለም አቀፋዊ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲንር በማድረጉም፣ አገሪቱ በምታስገባቸው ሸቀጦች ላይ ከ1.52 እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ለሚደርስ ለተጨማሪ ወጪ እንደምትዳረግ በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተንከባላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ አዳዲስ ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተጨመሩበት ክፍተቱ ሰፊ በሆነበት ሁኔታ ከሰሞኑ በማክሮ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅት የተጠቀሱት ውጤቶች ተመዝግበው ከሆነ መጥፎ የሚባል አይደለም የሚል አስተያየታቸው ይደመጣል።

በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በሚሰጡት የኢኮኖሚ ትንታኔ የሚታወቁት አቶ ዋሲሁን በላይ ጉዳዩን አስመልክቶ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ እንዳሠፈሩት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ቁጥር ሲገለጽ ሕዝብ ማረጋገጥ የሚሞክርበት መንገድ ገበያውን በመመልከት በመሆኑ፣ የዋጋ ንረት በተሻለ ቁጥር መቀነስ፣ ከምርት ሥርዓት የወጡ አምራቾችና አርሶ አደሮችን መደገፍ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ኢፍትሐዊነትን መቀነስ፣ ምክንያታዊ የድጎማ ሥርዓት መዘርጋትንና ሌሎችም የግድ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

የማክሮ ቁጥሮች በጣም አታላይ የሚሆኑት የተገኙ ውጤቶች ከረዥምና ከዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ ይልቅ ጊዚያዊ (Nominal) ውጤታቸው እየጎላ የሚቀጥል ከሆነ ነው በማለት ሐሳባቸውን ያሠፈሩት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ለአብነትም በውስን አካባቢዎችና ዘርፎች ላይ በሚኖር ርብርብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በተገኘ ማግሥት በፀጥታ ምክንያት የተፈጠሩትን ችግሮች በጊዚያዊነት (በሰብዓዊ ድጋፍ) ለመደገፍ እንዲውል የሚደረግ ከሆነ ዘላቂ ያለመሆን አደጋ አያጣውም የሚል ሐሳብ አንስተዋል። ስለሆነም የማክሮ ቁጥሮች ከማኅበራዊና ከቤተሰባዊ የኢኮኖሚ ውጤት መለኪያዎች ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ተገቢ ነው ባይ ናቸው።

በጠቅላላው የሐምሌ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠን 33.5 በመቶ የምግብ ዋጋ ግሽበት 35.1 በመቶ፣ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 30.4 ሆነው መመዝገባቸውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች