Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የራያ ሕዝብ በሕወሓት ብቻ ሳይሆን በሰርጎ ገቦች ጭምር እየተሰቃየ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የወሎ ራያ አማራ ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ፣ ሕዝቡ የሚሰቃየው በሕወሓት ሴራ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ በተሸጎጡ ሴራ ጠንሳሾች ጭምር እንደሆነ አስታወቀ፡፡ የራያ ሕዝብ ብሔር ተኮር ጥቃትን በየአካባቢው ተሸጉጠው ሴራ የሚጠነስሱ ሰርጎ ገቦችን ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኮሚቴው ጥሪውን ያቀረበው እሑድ ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በደሴ ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ የወሎና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ እንደገለጹት፣ የራያ ሕዝብ ላለፉት 30 ዓመታት የተለያዩ ሥቃዮችና መከራዎች ደርሰውበታል፡፡ ራሱን ‹‹የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር›› ወይም ‹‹የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር›› የሚለው ሕወሓት፣ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ መንቀሳቀስ መጀመሩንና ከዚያን ጊዜ አንስቶ የራያ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር ሲያደረግ እንደቆየ አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፡፡

የራያ ሕዝብ አንድነት ለማምጣትና ብሔር ተኮር ጥቃትን ለማስወገድ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. ኮሚቴ ማዋቀሩን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ኮሚቴውም ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ አደረጃጀት በመፍጠር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተለያዩ ጎራ የተሠለፉትን የራያ ማኅበረሰብ አካላት ወደ አንድ ለማምጣት ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ከአራት ጊዜ በላይ መድረክ በማዘጋጀት፣ ነፃና ግልጽ የሆነ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ከዓላማጣና ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ከመጡ ወገኖች ጋር በቆቦ ከተማ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ የራያ ሕዝብ ለእንግልት የበቃው በሽብርተኝነት በተፈረጀው የሕወሓት ሴራ ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ ጉያ ውስጥ ሆነ መረጃ በሚያቀብሉ ሰርጎ ገቦች ጭምር መሆኑን ለማረጋገጥ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ ቦታዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለችግር የተጋለጡ የራያ ወገኖችን ለመደገፍ ኮሚቴው እንደሚሠራና በየትኛውም ሁኔታ ከሕዝቡ ጎን እንደሚቆም አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ሕወሓት ክልሎችን የማደራጀት አዋጅ አውጥቶ ሲሠራ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃይሉ፣ አዋጁ የራያ ሕዝብን በራሱ እንዳይቆምና ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ እንዳይጠቀም አድርጎታል ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የራያ ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን ሰቆቃ ለመከላከል አንድነት ትልቅ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የራያ ተወላጆች እርስ በርስ የመጋጨትና የመከፋፈል ሐሳቦችን በማስወገድ፣ የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ነፃነት በማስቀደም ችግሮችን መጋፈጥ እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

በተደጋጋሚ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሲነሳ የነበረውን የነፃነት ጥያቄ ለመመለስ መደራጀትና አንድ መሆን ያስፈልጋል ያሉት በለጠ (ዶ/ር)፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ዋጋ መክፈል የግድ ይላል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገላጸ፣ የነፃነት ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ የራያ ሕዝብ ያለውን የተፈጠሮ ሀብት በመጠቀምና የግብርናና የኢንዱስትሪው ልማትን በማሳደግ ሰፊ ሥራ ማከናወን ይኖርበታል፡፡

የራያ ሕዝብ አንድ ላይ በመቀናጀትና በመተሳሰብ ራሱን ከብሔር ተኮር ጥቃት መታደግ እንዳለበት ከከተማዋ የተውጣጡ ሽማግሌዎች፣ እሑድ ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የራሱን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ አገር ይቅደም የሚል ሐሳብ እንዳለ፣ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማኅበረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭቆና መቅረት እንዳለበት ወጣቶች አሳስበዋል።

በሌላ በኩል አገርን ለመጠበቅ በተለያዩ ቦታዎች ተሠማርተው የሚገኙ የራያ ሚሊሻዎችና የልዩ ኃይል አባላት በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለራያ ሕዝብ  ትኩረት እየሰጠ ባለመሆኑ ችግሩን ውስብስብና ከባድ እንዳደረገው ሳይገልጹ አላለፉም።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች