Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ክለሳ አይደረግበትም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ትግበራ ላይ የሚገኘው የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ክለሳ እንደማይደረግበት ተገለጸ፡፡

‹‹ፍኖተ ብልጽግና›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የአሥር ዓመት ዕቅድ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም የንግድ ሥርዓት ላይ የፈጠረው ቀውስና በኢትዮጵያ ተከስተው በነበሩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችና የተለያዩ ጫናዎች በልማት ዕቅዱ ትግበራ ላይ ጫና አስከትለዋል ተብሎ በሚኒስትር ደኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) ተገልጾ ነበር።

በዚህም መንግሥት በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥጋቶችን ተቋቁሞ ግቡን ለማሳካት እንዲረዳው፣ የዕቅድ ክለሳ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለው ነበር።

በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እንደተገለጸው ግን የዕቅድ ክለሳ ሐሳብ የለም፡፡ የአሥር ዓመቱን ዕቅድ ማስፈጸሚያ የያዘ የሦስት ዓመት የፕሮግራምና ፕሮጀክቶች ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡

‹‹የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ክለሳ አይደረግበትም፣ ለዕቅዱ ማስፈጸሚያ የሦስት ዓመት ዕቅድ እየተዘጋጀ በመሆኑ ፓርላማ ባፀደቀው ሕግ ላይ ክለሳ አይደረግም፤›› ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሥር ከ2016 ዓ.ም. እስከ 2018 ዓ.ም. የሚተገበር የሦስት ዓመት መካከለኛ ዘመን ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ ዕቅዱ ከየካቲት እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ድረስ ሊጠናቀቅ ይችላል ሲሉ ፍፁም (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር የምርምርና የፖሊሲ ጥናት ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱን ክለሳ ለማድረግ ከተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየትና ግብዓት ወስዷል ይላሉ፡፡

‹‹የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ የታሰበውን ያህል መጓዝ ባለመቻሉ ክለሳ ሊደረግበት መሆኑን፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ የሦስት ዓመት ዕቅድ በዝግጅት ሒደት ላይ ነው፤›› ሲሉ ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የነበረችበትን ሁኔታ በመመልከት ለወደፊት ረዥም ዓመታት ዕቅዶች ይሠራሉ፡፡ እንደ ዓለም ባንክና የአፍሪካ ኅብረት ያሉ አካላት የረዥም ዓመት ልማታዊ ዕቅድ ሲያወጡ ትልልቅ ግቦችን ያስቀምጣሉ ብለዋል፡፡

‹‹በአገራችን የወጣው ዕቅድ ኢትዮጵያ እየተጓዘች ባለችበት ሁኔታ የታቀደውን ነገር ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ነው፤›› የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፣ በኢኮኖሚ መርህ የረዥም ዓመት የዕቅድ ትግበራን በተመለከተ ሁለት የተለያዩ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡

የመጀመሪያው የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ለዕቅዱ ተገዥ በመሆን ሐሳብን አለመለዋወጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው የዕቅድ ዓይነት ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ክለሳ የሚደረግበት ነው ብለዋል፡፡

‹‹የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ለዕቅዱ ተገዥ መሆን ሐሳብን አለመለዋወጥ ማለት፣ ዕቅድ በተለዋወጠ ቁጥር በኢኮኖሚ ላይ መተማመን ያሳጣል፡፡ ማኅረበሰቡም መንግሥት መጪውን ጊዜ በማሰብ ማቀድ አይችልም የሚል ሐሳብ ይፈጠርበታል፤›› በማለት አቶ ዋሲሁን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁለተኛው መርህ ዕቅድ ከታቀደ በኋላ ነባራዊ ሁኔታን በመመልከት ክለሳ የሚደረግበት ሲሆን፣ ይህም ማለት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ ዕቅዱ ከመፅደቁ በፊት ለበርካታ ባለድርሻ አካላት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ውይይት ሲደረግ የጊዜና የገንዘብ ወጪ አለው፡፡ ስለዚሀ አንዳንድ ጊዜ ወጪው ከፍተኛ ስለሚሆን ክለሳ ማድረግ ጉዳት እንዳለው የሚገልጽ መርህ፤›› ሲሉ አቶ ዋሲሁን አውስተዋል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም. ባሉት አሥር ዓመታት በአማካይ አሥር በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ዕቅድ እንደተያዘ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች