Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ15 በላይ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሥራት ጥያቄ አቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው ለማልማት፣ ከ15 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በአገሪቱ በተከሰተው የፀጥታ ችግርና በኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ቀዝቅዞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየተሻሻለ መምጣቱን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ በተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ለማልማት የተለያዩ አገሮችና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመነጋገር የቢዝነስ ፕሮፖዛል ማስገባታቸውን ገልጸው፣ እነዚሁ አልሚዎቹ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም ጋር በንግግር ላይ መሆናቸውን አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ15 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሽፈራው፣ ባለሀብቶቹ የቢዝነስ ፕሮፖዛላቸው እየተገመገመ እንደሚገኝና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 49 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት መነሻ ካፒታል ያስመዘገቡ ዘጠኝ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ሥራ መጀመራቸው ኮርፖሬሽኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ሐዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ቂሊንጦ፣ አዳማ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ባለሀብቶቹ የገቡባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

አቶ ሽፈራው በተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ የቆየው የኢንቨስትመንት ፍሰት በዚህ ወቅት ወደነበረበት እየተመለሰ ነው ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑም አገር በቀል አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው ማምረት እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ማድረጉን አክለዋል፡፡

ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አኳያ ባለፉት ዓመታት ተጠቃሽ ሥራ ተሠርቷል የሚሉት አቶ ሽፈራው፣ ሆኖም ይህንን ከኢኮኖሚ ጥቅሙና ካለው አዋጭነት አንፃር እየተመዘነ ወደ ሙሉ አቅምና ውጤታማነት ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 ከዚህ ቀደም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ፓርኮች አንዱ በሆነው፣ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኙ 15 ሼዶች ብዙዎቹ በባለሀብቶች አለመያዛቸው ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ለወደብ ካለው ቅርበት አንፃር ከተገነባበት ጊዜ አንፃር ኢንቨስተሮች ለምን ወደ ፓርኩ ሊገቡ አልቻሉም ለሚለው ጥያቄ ዋነኛው እንቅፋት የነበረው፣ ፓርኩ እንደተመረቀ የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰቱን በምክንያትነት ያቀረቡት አቶ ሽፈራው፣ ባለሀብቶች የገዥዎቻቸው የመግዛት አቅም በመዳከሙ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመግባት ፍላጎታቸውን የሚቀንስ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኮቪድ ተፅዕኖ ተቋቁሞ ውጤታማ ለማድረግ የተደረገው እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በአገሪቱ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከመልካ ጀብዱ እስከ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ድረስ የሚደርሰው መንገድ በሚገነባበት ወቅት ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ የነበረው ጉዳይ በፍጥነት አለመጠናቀቁ ሌላው ቸግር እንደነበረና ምንም እንኳን በዚህ ወቅት የተፈታ ቢሆንም፣ የውኃ አቅርቦት ችግር እንዲሁ ባለሀብቶች ቶሎ በፓርኩ ውስጥ እንዳይገቡ ካደረጓቸው ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ካለው የወደብ ቅርበትና መልክዓ ምድር ጋር ተያይዞ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለሎጂስቲክስና ለንግድ በጣም ወሳኝ የሆነ ቦታ ላይ የሚገኝ  ስለሆነ ወደፊት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ዕምነት እንዳለ ተገልጿል፡፡

ብዙዎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በማኑፋክቸሪንግና በተተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በዚህ ወቅት ደግሞ ለሎጂስቲክስ፣ ለሥልጠና፣ እንዲሁም ለመጋዘን ክምችት የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በ13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ120 በላይ ባለሀብቶች ገብተው እየሠሩ እንደሚገኙ ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ግዙፍ የኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች