Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው

በኢትዮጵያ ካሉ 1,200 በላይ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ 33 በመቶ የሚሆኑት የቴሌ ብር ሒሳብ የከፈቱ ቢሆኑም ሥራ አለመጀመራቸውን ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ጭራሽ አካውንት ባለመክፈታቸው እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በቴሌ ብር አገልግሎት እንዲጀምሩ፣ የማይጀምሩ ከሆነ ግን ‹‹ምንም ዓይነት ነዳጅ እንዳይቀርብላቸው›› ሲል የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮኖስ ወርቁ ተፈርሞ በዝርዝር ለጠቀሳቸው የነዳጅ ኩባንያዎች ተጽፎ የተሠራጨው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ማደያዎቹ ግዴለሽነት የታየባቸው ኩባንያዎቹ በሥራቸው ያሉትን ማደያዎች አካውንት ከፍተው ሥራ መጀመራቸውን ክትትል ባለማድረጋቸው እንደሆነ ነው፡፡

ማደያዎቹ ነዳጅ በቴሌ ብር መሸጥን በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው ያለመሥራታቸው ደብዳቤውን ለመጻፍ መገደዱን ባለሥልጣኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹም ይህንን ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ከኢትዮ ቴሌኮሙ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ማካሄጃ ቴሌ ብርን ብቻ እንዲጠቀም የወሰነ ሲሆን፣ የነዳጅ ማደያዎቹ በዚህ ተግባራዊነት የነጋዴና ወኪል አካውንት ከፍተው ድጎማ ተጠቃሚዎችን እንዲያስተናግዱ ታዘው ነበር፡፡

ይህን የግብይት ሥርዓት በቴሌ ብር ብቻ እንዲሆን ውል አድርጎ የነበረው የትራንስፖርትና የሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ በሌላ በኩልም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ፣ በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ እየመከረ እንደሚኝ ሚኒስቴሩ በሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሳውቋል፡፡ ይህም የቴሌ ብርን ብቸኛ የድጎማ ነዳጅ ክፍያ ማስፈጸሚያነት የሚጋራ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ምክክር፣ እንደ ሲቢኢ ብርን ጨምሮ ሌሎች የክፍያ አማራጮችን በመጠቀም የድጎማው ሥርዓት ላይ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም መግለጻቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ወደ 40 የሚጠጉ የነዳጅ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን፣ በሥራቸው 1,273 የሚሆኑ ማደያዎች አሉ፡፡ የኩባንያዎቹ የገበያ ድርሻን ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (NOC) በ33 በመቶ ሲመራ፣ ኦይል ሊቢያ 18 በመቶና ቶታል ኢነርጂስ በ14 በመቶ ይከተላል፡፡

መንግሥት ወደ 134 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ በኩል ለነዳጅ ድጎማ በማውጣቱና ድጎማውም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እየጎዳ በመምጣቱ ለማንሳት የተገደደ ሲሆን፣ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ድጎማ ግን በትራንስፖርት ላይ በተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ላይ የታለመለትን ድጎማ ማድረግ ከጀመረ አንድ ወር አልፎታል፡፡

እስካሁን ድረስም 141,000 የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በዚህ ሥርዓት ላይ ተመዝግበው አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ ትራንስፖር ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሁሉም ማደያዎች ግን በቴሌ ብር አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው የድጎማው ግብይት በሁሉም ማደያዎች እየተከናወነ አይደለም፡፡        

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች