የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ማኅበራዊ ልማት የተባለ አዲስ ቀረጥ የሚጥል ረቂቅ ደንብ አፀደቀ፡፡ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሦስት በመቶ ምጣኔ ያለው ሲሆን፣ ከመሠረታዊ የሕክምና ግብዓቶች ውጪ በተጨማሪ ቀረጥ (ሱር ታክስ) ውስጥ ያልተካተቱ ምርቶች በሙሉ ይህንን ቀረጥ ይከፍላሉ፡፡
ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አሥረኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥን የተመለከተ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ውሳኔዎቹን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ይህንን አዲስ ቀረጥ በመጣል በሚገኘው ገቢ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማስፋፋት፣ ለመጠገንና ለማሻሻል መታሰቡን አስታውቋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መነሻ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹የዚህ ቀረጥ ዓላማ ከፍተኛ ወጪ ውስጥ የሚገኘውን የመንግሥት ወጪ መጋራት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ያለበትን የወጪ ጫና ለመደጎም ይህንን ዓይነት ቀረጥ መጣል አስፈላጊ በመሆኑ ነው፤›› ብለው፣ ከዚህ ቀረጥ የሚገኘው ገቢ እንደ ጤናና ትምህርት ላሉ መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ የሚውል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ ቀረጥ የተጣለው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፣ ነገር ግን በሱር ታክስ ውስጥ ተካተው አሥር በመቶ ታክስ የሚከፈልባቸው ምርቶች ከማኅበራዊ ልማት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይህ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አብዛኞቹ ምርቶችን ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የሚያደርግም ቢሆንም፣ በዚህ ቀረጥ ውስጥ የሚካተቱ ምርቶች ከዚህ ቀደም ነፃ ተደርገው የቆዩ ናቸው፡፡
ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው የሱር ታክስ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ነበር፡፡ ደንቡ ከቀረጥ ነፃ ብሎ ካስቀመጣቸው የተወሰኑ ምርቶች ውጪ በሁሉም ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ሱር ታክስ እንደሚጣል ደንግጓል፡፡
ከተጨማሪ ቀረጡ ነፃ የሚሆኑት በደንቡ ላይ የተዘረዘሩ ዕቃዎችና በሕግ ወይም መንግሥት ባደረገው ስምምነት፣ ከጉምሩክ ነፃ የተደረጉ ሰዎችና ድርጅቶች የሚያመጧቸው ዕቃዎች ናቸው፡፡
በደንቡ ላይ ሱር ታክስ እንደማይመለከታቸው ከተዘረዘሩት ዕቃዎች መካከል የካፒታል (ኢንቨስትመንት) ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም አውሮፕላንና ክፍሎቹ ይገኙበታል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የተዋወቀው አዲሱ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ከሱር ታክስ ነፃ የተባሉትን እነዚህን ምርቶች እንደሚመለከት የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የቀረጥ ነፃ መብት ያለው በኢንቨስትመንት ዕቃ ሲያስገባም ሦስት በመቶ ይከፍላል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀው ደንብ መሠረት ለሽያጭ የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት ወይም አገልግሎት ለመስጠት ጥቅም ላይ የሚውሉ ማሽነሪዎችና መሰል ንብረቶች (ካፒታል ዕቃዎች) በሙሉ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ይከፍላሉ፡፡
ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የፀደቀው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ፣ ለአዲስ ኢንቨስትመንትና ለነባር ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ከውጪ የሚገቡ የካፒታልና የግንባታ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንደሚገቡ ደንግጓል፡፡ ለኢንቨስትመንት ዓላማ የሚውሉ ተሽከርካሪዎችም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ተደርገዋል፡፡
እነዚህ ሁሉ አሁን ሦስት በመቶ ቀረጥ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ከሱር ታክስ ነፃ ተደርገው የነበሩት አውሮፕላን፣ የአየር መንኮራኩር፣ የጠፈር መንኮራኩርና ክፍሎቻቸው በማኅበራዊ ልማት ታክስ ይካተታሉ፡፡ ይህም እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ የአቪዬሽን ተቋማት አውሮፕላኖች ገዝተው ሲያስገቡ ሦስት በመቶ ታክስ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡
በማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ደንብ ላይ በዓለም አቀፍ ስምምነት፣ በተለይም በቬና ኮንቬንሽን ከማንኛውም ታክስ ነፃ የተደረጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ከዚህ ቀረጥ ነፃ እንዳደረገ አቶ ሀብታሙ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ በሚያወጣው መመርያ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ስንዴና ዘይት የመሳሰሉት ላይ መጣል የዋጋ ንረትን ሊያባብስ ስለሚችል እነዚህ ላይ ይጣላል ተብሎ አይታሰብም፤›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፣ ሦስት በመቶ የሆነው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚጣልበት የሥሌት መሠረት ከጉምሩክ ቀረጥ ማስከፈያ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ሦስት በመቶ የሚጣለው የዕቃው ዋጋ፣ የመድን ዓረቦንና የማስጫኛ ወጪ (Cost, Insurance and Freight (CIF) ብቻ ታሳቢ ተደርገው ነው፡፡ እንደ ሱር፣ ቫትና ኤክሳይስ ታክስ ያሉ ታክሶች የሥሌት መሠረት አይሆኑም፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት 156 ቢሊዮን ብር ለሚደርስ ለተጨማሪ የወጪ ፍላጎት እንደተዳረገ የገለጸው የፌዴራል መንግሥት፣ ግብርና ቀረጥ የሚገኝባቸውን መሠረቶች በማስፋት ገቢውን ለመጨመር እንዳቀደ አስታውቋል፡፡
ለዚህም የተጨማሪ እሴት ታክስና የኤክሳይስ ታክስ ሕጎችን ማሻሻል ጨምሮ፣ አዲስ ሕግ በማውጣት የንብረት ታክስን እንደሚያስተዋውቅ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት 336.7 ቢሊዮን ብር ግብር ሰብስቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት አንፃር የ57.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ቢኖረውም ካቀደው በ23 ቢሊዮን ብር ያነሰ ነው፡፡