Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2፣ ‹‹በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፤›› ይላል፡፡ ይህ በሕግ የተደገፈ መብት በሕጉ መሠረት ይከናወን፡፡ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ምክንያት የደረሰው ዕልቂትና ውደመት አይዘነጋም፡፡ አሁንም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡ በሕጉ መሠረት እንደሚስተናገዱ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል ግን ጥያቄያችን ተቀባይነት አላገኘም በማለት በጉራጌ ዞን ተቃውሞ እየተሰማ ነው፡፡ ጥያቄ ያነሳውም ሆነ ጥያቄውን የሚቀበለው አካል በሕጉ መሠረት ተነጋግረው ችግሩን በፍጥነት መፍታት አለባቸው፡፡ የክልልነት ጥያቄም ሆነ ሌሎች ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ያለባቸው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን፣ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ያላሰለሰ ጥረት ያድርጉ፡፡ አንፃራዊውን ሰላም ማደፍረስ አይገባም፡፡

በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት አራት ዓመታት የገባችበት መጠነ ሰፊ ቀውስ መንስዔው፣ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ መልክ አስይዞ በሚያቃርኑ ጉዳዮች ላይ በቂ ውይይትና ድርድር ለማድረግ አለመቻል ወይም ፈቃደኝነት ማጣት ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ከማጋጠማቸው በተጨማሪ፣ ንፁኃንን ማንነታቸውን መነሻ በማድረግ በተፈጸሙ ጥቃቶች አሰቃቂ ዕልቂቶችና ውድመቶች ደርሰዋል፡፡ በጦርነቱም ወቅት ሆነ ከዚያም በኋላ በንፁኃን ላይ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎችና ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እንደተገለጸው የፌዴራል መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ሕወሓት ጋር ካደረገው ፍልሚያ በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌና በሌሎች ሥፍራዎች ከተለያዩ አደረጃጀቶችና ከአልሸባብ ጋር ጭምር ባደረጋቸው ኦፕሬሽኖች በሕገወጦች ላይ አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ዕርምጃ ጎን ለጎን ሌሎች መወሰድ ያለባቸው ጉዳዮች ደግሞ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መስኮች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡

ሰሞኑን በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ያወጣው የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በአመራር፣ በፀጥታ አካላትና በሕዝቡ ቁርጠኝነትና መስዋዕትነት ሊተገበሩ ካላቸው መካከል አሸባሪና ሕገወጥ ታጣቂዎችን ሥጋት ከማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ፣ ሕዝብን በማወያየት፣ የታጠቁ አካላትን በማግባባት፣ ወጣቶችን በሰላም ተግባራት ላይ በማሳተፍ፣ ዘላቂ ሰላም የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በመሥራት፣ የፍትሕ አካላትን በማጥራትና በማጠናከር ለአገራዊ ሰላምና ደኅንነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ በማድረግ፣ ሕዝቡን በሚያማርሩ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሙስና፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ወዘተ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ሕዝቡ ዕፎይ እንዲል ማድረግ፣ በየደረጃው ያለውን አመራር በማጥራትና ተጠያቂነትን በማስፈን በየደረጃው ብቁ፣ ንቁና ሁሌም ዝግጁ የሆነ አመራር መፍጠር፣ ሕዝባዊና የሃይማኖት በዓላትን፣ የብሔርና የአስተዳደር እርከን ጥያቄዎችን ጠላት የዓላማው ማስፈጸሚያና የሕዝቡን ሰላም ማወኪያ እንዳያደርጋቸው ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት መሥራትና የመሳሰሉትን ሐሳቦች አውስቷል፡፡ ይህ የፀጥታ ጉዳይን የተመለከተ ውሳኔ እንዳለ ሆኖ፣ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ደግሞ ሰላም ሰፍኖ ሥጋት እንዲወገድ፣ የበኩሉን ኃላፊነት በሕጋዊና በፖለቲካዊ መስመር ፈር ማስያዝ ይጠበቅበታል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በቅርቡ በኬንያ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ከሕወሓት ጋር ለድርድር እንደሚቀመጥ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ ድርድር በባህሪው የተለያዩ ዓላማዎችና ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች ቅድመ ሁኔታዎችን የሚደረድሩበት ቢሆንም፣ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች ድርድሩ የተሟላ ሰላም እንዲያስገኝ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ከዚህ ቀደም የፈሰሰው የንፁኃን ደምና የወደመው የአገር ሀብት ታሳቢ ተደርጎ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዳትገባ የሚያግዙ የመፍትሔ ሐሳቦች መሰንዘር አለባቸው፡፡ ይህ ድርድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ እንዲያስገኝ  ከተፈለገ፣ ከምንም ነገር በላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖች ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ድርድሩን የግለሰቦች፣ የቡድኖችና የጥቂት ተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል በቅድመ ሁኔታዎች ከማጠርና እንቅፋት ከመፍጠር መቆጠብ ተገቢ ነው፡፡ በሕዝብ ስም በተለመደው ቁማርተኝነት የጥቂቶችን የበላይነትና ማናለብኝነት ለማስፈን ሳይሆን፣ በሰላም ዕጦት ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖችን ለመታደግ ድርድሩ ይካሄድ፡፡ ሰላም የሚሰፍነውና ሕዝብና አገር ዕፎይ የሚሉት ለእውነተኛ ድርድር መቅረብ ሲቻል ነው፡፡

በሌሎች አካባቢዎችም ለሁከትና ለውድመት የሚያነሳሱ ሕገወጥ ድርጊቶች የሚከሽፉት፣ ጥያቄ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ የተደራጁ ወገኖች በሕጋዊ መንገድ እንዲስተናገዱ ዕድሉ ሲመቻችላቸው ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የግለሰቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር፣ ለእኩልነትና ለፍትሐዊነት ፀር የሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶችን መግታት፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎችን አለመቀላቀል፣ ለሌብነትና ለዝርፊያ የሚመቹ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ተቋማትን በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች ማጠናከር፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ሰላማዊና ሕጋዊ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎች ላይ ማተኮርና ለሕግ የበላይነት መስፈን ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ሒደት የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማኅበራት አመራሮች፣ የሙያና የጥቅም ማኅበራት ወኪሎች፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ እንዲሁም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎችን በማሳተፍ ሰላማዊ ድባብ እንዲፈጠር ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ግለሰቦች ወይም ስብስቦች ሲያኮርፉ ‹‹የራሳችሁ ጉዳይ›› ከማለት ይልቅ፣ ችግራቸውን በውል ተገንዝቦ ለመፍትሔ በጋራ መትጋት ለሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶችም ሆኑ ጥቃቶች ገጽታቸውን እየቀያየሩ በአገርና በሕዝብ ላይ ጉዳት እየደረሰ መቀጠል አይቻልም፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ ተርፋ ለዓለም ሰላም መከበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሥር በበርካታ አገሮች ግልጋሎት ሰጥታለች፡፡ ለምሳሌም በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ሥር በሶማሊያ ተሰማርታ አርዓያነት ያለው አኩሪ ተግባር የፈጸመች ታላቅ አገር ናት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ያለባቸው ችግሮች ለአላስፈላጊ ደም መፋሰስና ውድመት ዳርገዋት፣ በዚህ ዘመን በውጭ አሸማጋዮች አማካይነት ለድርድር እየተዘጋጀች ነው፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የመፍታት አኩሪ ባህሎች ባሏት ኢትዮጵያ፣ እጅግ አስደማሚ የሆኑ የግጭት አፈታቶችና የሽምግልና ሥርዓቶችን በሁሉም ሥፍራዎች ማግኘት ብርቅ አይደለም፡፡ በዳይ ተበዳይን ይቅርታ የሚጠይቅበት፣ የሚክስበትና እንደገና ወዳጅነት የሚጀምርባቸው አኩሪ ባህላዊ እሴቶች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ በዚህ ዘመን የገዛ ወገናቸውን አሰቃይተውና ገድለው የሚፎክሩትን በቃችሁ ማለት የሚቻለው ኢትዮጵያውያን በቁጭት ሲነሱ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ሰላሟ እየተቃወሰ አትሰቃይ፡፡ የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...