Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሙርሌ ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ገድለው ሁለት ሕፃናትን ወሰዱ

የሙርሌ ታጣቂዎች ሁለት ሰዎችን ገድለው ሁለት ሕፃናትን ወሰዱ

ቀን:

የጋምቤላ ክልልን ከምታዋስነው ጎረቤት አገር ደቡብ ሱዳን የሚመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፣ በክልሉ አኝዋ ዞን ዲማ ወረዳ የስደተኞች ካምፕ ላይ ጥቃት ከፍተው ሁለት ሰዎችን ገድለው ሁለት ሕፃናትን አግተው መውሰዳቸው ተገለጸ፡፡

ድንበር ተሻግረው የመጡት ታጣቂዎች በዲፕ ቀበሌ በሚገኘው ኡኩጉ ካምፕ የሚገኙ ስደተኞችና ተፈናቃዎች ላይ ጥቃት የፈጸሙት ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሆኑን የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሕይወታቸው ካለፉት ሁለት ሰዎች ባሻገር አንድ ሰው ከፍተኛ ቁስለት ደርሶበት በሕክምና ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከጥቃቱ መድረስ በኋላ የክልሉ ልዩ ኃይልና የፌዴራል ፖሊስ አካባቢ ላይ መሰማራታቸውን የተናገሩት አቶ ኡጌቱ፣ ታጣቂዎቹን ግን ማግኘትና መያዝ እንዳልቻሉ ገልጸዋው ‹‹አሁን በሚሊሻዎች ዱካቸውን እየተከተልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የዲማ ወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡጁሉ አከኔ በበኩላቸው፣ ጥቃት ከተፈጸመበት ኡኩጉ ካምፕ የሚገኙ ታጣቂዎች በተፈጠረባቸው ሥጋት ሳቢያ ከካምፑ እየወጡ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ማኅበረሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበት ሁኔታ አለ›› ሲሉም ካምፑ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ወደ ሌሎች መኖሪያ መንደሮች መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ቅርበት ስላላቸው እንደፈለጉ ይሻገራሉ፡፡ በየቀበሌው በተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽማሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ጥቃት ከፍተው ሰው ይገላሉ፣ ሕፃናት ይወስዳሉ›› ያሉት አቶ ኡጁሉ፣ ታጣቂዎቹ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በከፈቱት ጥቃት አንድ ስደተኛ ሲገደል አንዲት ሴት መቁሰሏን ተናግረዋል፡፡

በየዓመቱ በጋምቤላ ክልል በኩል የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ጥቃት የሚፈጽሙት የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፣ ከ2008 ዓ.ም. አንስቶ እስካሁን ከ740 በላይ ሰዎችን መግደላቸውን የክልሉ መንግሥት መረጃ ያስረዳል፡፡ ታጣቂዎቹ 2014 ዓ.ም. ከገባ ወዲህ እስከ መጋቢት ወር ብቻ 18 ሰዎችን ገድለው ስምንት ሕፃናትን ወስደዋል፡፡ ከ300 በላይ ከብቶችን ዘርፈዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታጣቂዎቹ በከፈቱት ጥቃት ሳቢያ 20 ሺሕ የክልሉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው ተገልጾ ነበር፡፡

የሙርሌ ታጣቂዎች ከሰባት ወር በፊት ጥር ወር 2014 ዓ.ም. በኑዌር ዞን አኮቦ ወረዳ ካንካን ቀበሌ በጉዞ ላይ የነበረ አምቡላንስ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ስምንት ሰዎችን ገድለው፣ በአምስት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት አድርሰው ነበር፡፡ ጥቃቱ ከመፈጸሙ ከቀናት በፊትም ከ70 በላይ የቀንድ ከብቶችን ከዘረፉ በኋላ፣ ዘረፋውን ለመከላከል የሞከረ አንድ የፖሊስ ባልደረባ ገድለው ሄደዋል፡፡

በጥር ወር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢጋድ አገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውልና በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲን ያካተተ ልዑክ ወደ ደቡብ ሱዳን አቅንቶ ነበር፡፡ ልዑኩ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዳት ጋር በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን አዋሳኝ አካባቢ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ተወያይቶ የነበረ ሲሆን፣ የሙርሌ ታጣቂዎች በኢትዮጵያ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጾ ነበር፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የተደረሰው መግባባት ‹‹ውጤቱ መታየት የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለም›› ያሉት የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ፣ ‹‹ቀጣይነት ያለው ጥቃት ስላለ ውይይቱ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሙርሌ ታጣቂዎች በብዛት መጥተው የሚፈጽሙትን ጥቃት ማስቀረት ቢቻልም ‹‹በየወሩ አንድና ሁለት ሰው እየገደሉ›› መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል›› ያሉት አቶ ኡጌቱ፣ የክልሉ መንግሥት ከደቡብ ሱዳን አጎራባች ክልሎች ጋር በቅርቡ ውይይት ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...