ከተቋቋሙ በኋላ ካፒታላቸውን ለማሳደግ አዲስ አክሲዮኖችን የሚሸጡ ኩባንያዎች፣ በአክሲዮን ሽያጭ የሚያገኙት ገቢ ላይ የተጣለባቸው የገቢ ግብር ተነሳ፡፡ ከአክሲዮን ሽያጭ ላይ የተነሳው ግብር ድርጅቶች ከዚህ ገቢ ላይ የሚከፍሉትን 30 በመቶ ግብር የሚያስቀር ነው፡፡
ይህ ውሳኔ የተላለፈው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የአክሲዮን ሽያጭን ከገቢ ግብር ነፃ የሚያደርግ ረቂቅ ደንብ በማፅደቁ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ያሳለፋቸውን ውሳኔ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ በካፒታል እጥረት ምክንያት የሥራ እንቅስቃሴያቸው የተዳከሙ ድርጅቶች ተጨማሪ ካፒታል ለማሰባሰብ ከሚሸጡት አዲስ አክሲዮን የሚገኝ ገቢን ከግብር ነፃ ማድረግ የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ደንቡን እንዳፀደቀ አስታውቋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መነሻ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን ደንብ ያዘጋጀው በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባያዎች የካፒታል እጥረት ተግዳሮት ሆኖባቸው ስለሚታይ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ይህ ታክስ ኢንቨስትሮችን ወደ አገር ወስጥ ለመሳብ አመቺ እንዳልሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ታክስ ታደርጋለች የሚል ሐሳብ ፈጥሯል፡፡ እንዲህ ዓይነት ታክስ ኢንቨስትመንትን አያሳድግም፡፡ ያቀጭጫል፡፡ የሚል አቤቱታ ቅሬታ ይቀርባል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኩባንያዎች ሥራቸውን ለማስፋት በሚል ለተጨማሪ ካፒታል ከሚሸጡት አክሲዮን ላይ አንድ ሦስተኛ ገደማውን ለመንግሥት ስለሚከፍሉ፣ በሚፈልጉት መጠን ካፒታላቸውን ለመሸጥ እንደሚቸገሩ አክለዋል፡፡
ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የተለያዩ የመንግሥት አካላት ይህ የግብር ገቢ እንዲነሳ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም. የወጣው የገቢ ግብር አዋጅ በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆነ ኩባንያ አክሲዮን በመሸጥ ወይም በመለወጥ የሚገኝ ገቢ እንደ ገቢ ምንጭ ተቆጥሮ ግብር እንደሚጣልበት ደንግጓል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ሽያጭ የሚገኘው ገቢም በ‹‹ምድብ ለ ግብር›› ውስጥ ተካቶ ሰላሳ በመቶ ተጥሎበታል፡፡
ኩባንያዎች ካፒታላቸውን ለማሳደግ አዲስ አክስዮን የሚሸጡት ኩባንያው ሲመሠረት፣ የአንድ አክስዮን ዋጋ ተብሎ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ላይ ወቅታዊ የገበያ ዋጋን በመጨመር ነው፡፡ አክሲዮን ሸጠው ከሚያገኙት ገቢ ላይ የሚከፍሉት 30 በመቶ ግብር የሚታሰበውም በመመሥረቻ ጽሑፋቸው ላይ ያስቀመጡት የአንድ አክሲዮን ዋጋ አሁን ከሸጡበት ዋጋ ላይ ተቀናሽ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር በገቢ ግብር አዋጁ ላይ የተቀመጠው ይህ ግብር እንዲነሳ የሚያደርግ ደንብ ለሚኒስቴሮች ምክር ቤት ያቀረበው ኢኮኖሚያዊ አስተዳደራዊ ወይም ማኅበራዊ ምክንያቶች መኖራቸው ሲታመን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት አንድን ገቢ ከግብር ነፃ ሊያደርግ እንደሚችል በተደነገገው መሠረት መሆኑ ተገልጿል፡፡
እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ህንድ ያሉ አገሮች ካፒታልን ለማሳደግ ከሚደረግ የአክሲዮን ሽያጭ ላይ ግብር እንደሚሰበስቡ የገለጹት የሕግ ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ፣ ‹‹ያለው ልምድ የሚያሳየው ኢንቨስትመንት ስለሆነ ከታክስ ውጪ እንደሚሆን ነው፤›› በማለት ደንቡ የተዘጋጀበትን መነሻ ሐሳብ አስረድተዋል፡፡
ከኩባንያዎቹ በአክሲዮን ሽያጭ ገቢ ግብር ከመሰብሰብ ይልቅ ካፒታላቸውን አሳድገው በሚሠሩት ሥራ የሚገኘው የሥራ ዕድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ይበልጥ ጥቅም እንደሚያስገኝም አክለዋል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ግብሩን ለማንሳት ኢንቨስትመንት ማበረታታትን በምክንያትነት ቢያስቀምጥም በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ የሚታሰበው የካፒታል ገበያም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ባለሙያው ሰውአለ አባተ (ዶ/ር)፣ የካፒታል ገበያን ለማስጀመር የሚደረጉ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸው አስታውሰው ገበያው ሲጀመር ግን አክሲዮን አውጥተው የሚሸጡ ድርጅቶች በሚፈለገው መጠን ላይኖሩ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ሥጋት ለመቅረፍ እንደ መፍትሔ ዕርምጃ ተሚጠቆሙ ተግባራት ውስጥም ካፒታል ለማግኘት ከሚደረግ ሽያጭ ላይ ግብርን ማንሳት እንዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹ፒኤልሲ የነበሩ ኩብንያዎች አክስዮን ኩባንያ ለመሆን ሲያስቡ ታክስ የሚከፍሉ ከሆነ አክሲዮናቸውን ወደ ገበያ የማውጣት ፍላጎታቸውን ይገድበዋል፤›› ያሉት ሰውአለ (ዶ/ር)፣ ይህም ከገቢ ግብሩ ከፍተኛነት ጋር እንደሚያያዝ ገልጸዋል፡፡
ይህ ውሳኔ ኩባንያዎች አክሲዮን ገበያን እንዲቀላቀሉ የሚደረግ ማበረታቻ እንደሆነ ተናግረው፣ ‹‹ኩባንያዎች አክሲዮን በመሸጥ ካፒታላቸውን የማሳደግ ፍላጎታቸውን ስለሚጨምር በበጎ የሚታይ ውሳኔ ነው፤›› ሲሉም የምክር ቤቱን ውሳኔ ደግፈዋል፡፡