Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

የማስተማር ሙያ ሥልጠና ባልወሰዱ መምህራን ላይ አስገዳጅ ውሳኔ ተላለፈ

ቀን:

  • ለአሥር ዓመት ሥልጠናውን ያልወሰዱ መምህራን ከመምህርነት ሙያ ይወጣሉ
  • የግል ትምህርት ቤቶች በራሳቸው ወጪ መምህራኖቻቸው እንዲያሠለጥኑ ይደርጋሉ

በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ የሚገኙና የማስተማር ሙያ ሥልጠና (Post Graduate Diploma in Teaching – PGDT) ያልወሰዱ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቅ መምህራንን በሚመለከት ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

ከውሳኔዎቹ መካከልም ከአሥር ዓመታት በላይ ሥልጠና ሳይወስዱ እያስተማሩ የሚገኙ መምህራንን ከሙያ የሚያስወጣ፣ የግል ትምህርት ቤቶችም በራሳቸው ወጪ  መምህራኖቻቸውን እንዲያሠለጥኑ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከተለያዩ የክልልና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ጋር በተደጋጋሚ በመምከር ስምምነት ላይ የተደረሰበት ውሳኔ፣ በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ፊርማ ወጪ ከተደረገ ደብዳቤ ጋር አባሪ ተድርጎ ለአሥር ክልሎችና ለሁለት ከተማ አስተዳደሮች (ትግራይን ሳይጨምር) የትምህርት ቢሮዎች በተላከው መሠረት፣ የውሳኔው ተግባራዊነት ከነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይሆናል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የትምህርት ቢሮዎቹና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የመምህራን ደረጃ፣ ዕድገትና የትምህርት ደረጃ መሻሻልን እንደ ዋነኛ ምክንያት በማድረግ፣ የተወያዩበትና ውሳኔዎቹን ያሳለፉባቸው አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሀል አንደኛው በቅጥር ውል ፈርመው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስተማሩ የሚገኙ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቃንን በሚመለከት ሲሆን፣ ከሦስት ዓመታት በታች አገልግሎት የሰጡ ጀማሪ መምህራን የመምህርነት ሙያ ቢያሟሉም ከተፈቀደው እርከን አንድ ደረጃ ዝቅ ያለ መነሻ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡

በተያያዘም ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስተማሩ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቅ መምህራን፣ የማስተማር ሙያ ሥልጠናን ሳይመቻችላቸው የቀሩ ሆነው የመምህራን ሙያ ሥልጠና ያልወሰዱት፣ ለጀማሪ መምህር መደብ የተዘጋጀውን መነሻ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሆነው ነገር ግን ከስድስት እስከ ስምንት ዓመታት ያገለገሉ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቅ መምህራን፣ ለመለስተኛ መምህር የተመደበ ደመወዝ ያገኛሉ፡፡ አገልግሎታቸው ከአምስት ዓመታት በላይ ሆኖ፣ ነገር ግን መንግሥት ያመቻቸላቸውን ሥልጠና በግላቸው ምክንያት ሳይወስዱ የቀሩ መምህራን፣ አገልግሎታቸው ስምንት ዓመት እስኪሞላ ድረስ በግላቸው ወይም መንግሥት በሚያመቻቸው ሥልጠና አጠናቀው እስኪገኙ ድረስ ለጀማሪ መምህር የተፈቀደውን መነሻ ደመወዝ ብቻ ያገኛሉ፡፡

በግል ትምህርት ተቋማት ለሚያስተምሩ የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂዎች፣ ነገር ግን የማስተማር ሙያ ሥልጠና ሳይወስዱ ለቀሩ መምህራን የትምህርት ተቋማቱ ባለቤቶች ሙሉ ወጪያቸውን ችለው እንዲያሠለጥኗቸው፣ ይህም በትምህርት ሚኒስቴር መዋቅር ቁጥጥር እንዲደረግበትም ተወስኗል፡፡ መምህራኖቹም የሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ከተመረቁበት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዲኖረው ሲል ውሳኔው ይገልጻል፡፡

የማስተማር ሙያ ሥልጠና (PGDT) የሚሰጠው በተመረጡ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሆኖ፣ ሥልጠናውን የሚወስደውም ከትምህርት ሚኒስቴር የተፈቀደለት መምህር ይሆናል፡፡ ከአሥር ዓመታት በላይ ሥልጠናውን ሳይወስዱ የሚያስተምሩ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቃንም፣ ከመምህርነት ሙያ ወጥተው ድጋፍ ሰጪ ብቻ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ተወስኗል፡፡

የትምህርት ቢሮዎች በሥራቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቃንን መቅጠር ከፈለጉ፣ ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን መልምለው የአንድ ዓመት (10 ወራት) የማስተማር ሙያ (PGDT) በአሠልጣኝ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሠለጥኑ በማድረግ መቅጠር ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የመምህራን አጥረት ቢገጥማቸው ምሩቃኑን ከጀማሪ መምህራን አንድ ዕርከን ዝቅ አድርገው መቅጠር ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ለዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፣ በምን ደረጀ ላይ ሆነው ምን ምን ያሟሉ መምህር መሆን እንደሚችሉ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣  ‹‹ማንኛውንም የትምህርት መሥፈርት የሚያሟሉ፣ ብቃት ያላቸውና አስፈላጊውን ሥልጠና ወስደው በመምህርነት እየሠሩ የሚገኙ አባል መሆን ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡ አስተማሪ የሆኑና የማስተማር ሙያ ሥልጠና (PGDT) ባይሠለጥኑም እንደ አሠሪና ሠራተኛ በመደራጀት ማኅበር አባል የሆኑ አሉ ብለው፣ ማንኛውም መምህርን ይህንን ሥልጠና መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹የአስተማሪ እጥረት ሲከሰት የግል ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችም ያልሠለጠኑ ምሩቃንን ሲቀጥሩ ነበር፤›› ሲሉ ዮሐንስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከበፊትም ጀምሮ የነበረ ሕግ መሆኑንና ከሰሞኑ በተደረጉ ማኅበሩም በተሳተፈባቸው ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ይህ ውሳኔ ሊተላለፍ ችሏል፡፡ ለመመህራን የሙያ ሥልጠና መስጠት ያለባቸው የተወሰኑ የመንግሥት አሠልጣኝ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን በትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የተፈረመው የውሳኔ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...