Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጉራጌ ዞን በርካታ አካባቢዎች የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

በጉራጌ ዞን በርካታ አካባቢዎች የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

ቀን:

የክልሉ ፖሊስ በኢ-መደበኛ ኃይሎች የተጠራ አድማ ነው ብሎታል

በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ዞኖች ውስጥ አንዱ የሆነው የጉራጌ ዞን በርካታ ከተሞች ከ‹‹ክልል እንሁን›› ጥያቄ ጋር በተገናኘ ላቀረቡት ጥያቄ መንግሥት በቂ ምላሽ አልሰጠንም በማለት ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የሥራ ማቆም አደረጉ፡፡ የተጠራው አድማ በኢ-መደበኛ ኃይሎች የተጠራ መሆኑ፣ የክልሉ ፖሊስ ተናግሯል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በበራሪ ወረቀትና በተለያዩ መዋቅሮች በተደረገ ጥሪ በዞኑ ከተሞችና ወረዳዎች በተለይ በወልቂጤ፣ ጉንቸሬ፣ ምሁር አክሊል፣ እነሞርና ኢነር ወረዳ፣ እዥ፣ ጉመር የተባሉ አካባቢዎች አድማን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ መዋላቸውንና ሱቆች፣ ባንኮች፣ መሥሪያ ቤቶች፣ የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ከሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ማወቅ ተችሏል፡፡

በቀጣይ ቀናትም መንግሥት ምላሽ ካልሰጠ አድማው እንደሚቀጥል የተናገሩትና አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የእዣ ወራዳ ክልል ምክር ቤት ተዋካይ አቶ ታረቀኝ ደግፌ ሲሆኑ፣ በቀጣይም መልስ ካላገኙ የተያዘውን ሰላማዊ ትግል በተደራጁ ወጣቶች አማካይነት እንደሚቀጥሉበትና አሁን ከሚታየው አድማ በተለየ መልኩ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያሰፉበት ተናግረዋል፡፡  

ምንም እንኳ የጉራጌ የክልል እንሁን ጥያቄ የቆየ ቢሆንም፣ መንግሥት ከሌሎች ዞኖች ጋር በማሰባጠር አዋቅረዋለሁ ያለው አዲስ ክልል፣ ጉራጌ በቋንቋ፣ በባህል በሥነ ልቦና ከሚቀራረበው ማኅበረሰብ ጋር መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡

የጉራጌ ዞን አመራር ሠራተኛ እንዲሁም የአካባቢው የአገር ሽማግሌ በዚህ አቋሙ በፀናበት በዚህ ወቅት ዞኑ በኮማንድ ፖስት ሥር  ከመሆኑም በላይ መንግሥት በግድ ሕዝቡን ውይይት ላይ እንዲሳተፍ በማድረግና ውሳኔውን እንዲቀበል እያደረገ መሆኑን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

‹‹ራሴን ላስተዳድር፣ ልልማ፣ ቋንቋዬን ላሳድግ ብሎ፣ የብሔር ፌደራሊዝሙ እስካልጠፋ ድረስ መብቴ ይጠበቅልኝ በሚል በሰላማዊ መንገድ መብቱን እየጠየቀ  መሆኑንና አድማው በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን፤›› አስረድተዋል፡፡

 በደቡብ ክልል በርካታ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ተከትሎ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ለሁለት ተከፍለው፣ በሁለት አዲስ ክልሎች ለመደራጀት በየምክርቤቶቻቸው ወስነው ውሳኔውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የሕዝቡን የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ፣ ‹‹እኛ ሕዝቡ የሥራ ማቆም አድማ እንዲመታ አልፈቀድንም፣ ሱቆችና ባንኮች ሌሎችም የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ ተሽከርካሪዎች ሥራ አቁመዋል፡፡ እኛ ወደ ሥራ ተመለሱ፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ አድርጉ እንላለን፣ ነገር ግን ይህንን ጥሪ እምቢ ያለ አካል በመነጋገር እንዲፈታ ከማድረግ ባለፈ የተለየ ውሳኔ ልንወስን አንችልም፤››  ብለዋል፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ የሚፈጸመው ነገር ትክክል እንዳልሆነና ሕገወጥ መሆኑን የማስረዳት ሥራ እየሠሩ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ሰዎች ሳይፈልጉ በኢ-መደበኛ ቡድኖች ተፅዕኖ ሥራቸውን እንዳይሠሩ እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ‹‹ጥያቄ ካልተመለሰ የሚባል ነገር የለም፣ መንግሥትና ፓርቲው አደረጃጀትን በተመለከተ ያለውን ጥያቄ መልሷል፣ ስለዚህ ማንኛውም አካል ዝምብሎ መምራት አይችልም፣ ይህ ማለት አገር በምን መልኩ መመራት እንዳለበትና የሚቀርብ ጥያቄ በምን መልኩ መመለስ አለበት የሚለውን ለመፍታት በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል፤›› ብለዋል፡፡

ኢ-መደበኛ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚያወሩትን ነገር በምንም ዓይነት መልኩ አሁን ያለውን የመንግሥትና የሕዝብን ሐሳብ የሚያስቀይሩ አይደሉም ያሉት የፖሊስ ኮሚሽነሩ፣ በጉዳዩ ላይ በየደረጃው ያለው ሕዝብ ተወያይቶበትና አምኖበት አብሮ የመኖርን ሐሳብ ደግፏል ብለዋል፡፡

አክለውም በደቡብ ክልል ያሉ 11 ዞኖች ክልል ቢጠይቁም ለሁሉም ክልል መስጠት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ጥያቄውን በሁለት ክልሎች ለማደራጀት የመንግሥት ውሳኔ የተደረሰበት በመሆኑና አሁን የሚነሳው ጉዳይ የሚጠቅም አለመሆኑን ሁሉም የክልሉ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ያመኑበት በመሆኑ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረገው ቅስቀሳ ውሳኔውን የሚያደናቅፍ አይደለም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...