Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእናት ጡት ወተት የመጀመርያው የሕይወት ክትባት

የእናት ጡት ወተት የመጀመርያው የሕይወት ክትባት

ቀን:

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን አስከትሏል፡፡ ከዚህ አኳያ የዜጎችን የመኖር ዕድል፣ ጤናና ደኅንነት መጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በተለይ ጡት ማጥባት ጥሩ የሕይወት ጅማሬን ከማቀዳጀቱ ባሻገር፣ ለረዥም ጊዜ ጤናን ለማጎናፀፍ፣ ለተስተካከለ ሥርዓተ ምግብና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ አለው፡፡

ጡት ማጥባት ለሰው ልጆች የተሰጠ ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብት በመሆኑ ሊከበር፣ ሊደገፍና ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና ማሳወቅ፣ ጡት ማጥባትን መደገፍንና ከሥርዓተ ምግብ፣ ከምግብ ዋስትናና እኩልነትን ከማረጋገጥ ጋር ማያያዝ ግድ ይላል፡፡

በመጀመርያዎቹ 1,000 ቀናት ጡት ማጥባትን ለመደገፍ ከግለሰቦችና ከተቋማት ጋር በጋራ መሥራትና የባለድርሻ አካላትንና የአሠራር ሥርዓቱን አቅም በመገንባት እመርታዊ ለውጥ እንዲኖር ለማድረግ የሁሉም የጋራ ኃላፊነት ነው፡፡

የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የሕፃናት ጤና እና የሥርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) እንደለገጹትም፣ ጨቅላ ሕፃናት እንደተወለዱ ወዲያውኑ የእናት ጡት ወተት  መጥባት አለባቸው፡፡ ይህም እስከ ስድስት ወራት ድረስ ሊዘልቅ ይገባል፡፡ በ2012 ዓ.ም. የተካሄደው መለስተኛ የሕዝብ ዳሰሳ ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው፣ ለስድስት ወራት የእናት ጡት ወተት ብቻ ያጠቡ እናቶች 59 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡

ጡት ማጥባት እንደ ባህል በሚታይበት ኢትዮጵያ የሚያጠቡ እናቶች ቁጥር 59 በመቶ ብቻ መሆኑ በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ የቁጥሩን መጠን ወደ መቶ በመቶ ከፍ ለማድረግ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ለልጅ የሚሰጥ ትልቁ ስጦታ የእናት ጡት ወተት ነው የሚል እምነት አለኝ፤›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ይህ ስጦታ የመጀመርያው የሕይወት ክትባት መሆኑን፣ ክትባቱም ሕፃናቱ ይህንን ዓለም ሲቀላቀሉ በበሽታ እንዳይጠቁ፣ እንዳይጎዱና እንዳይሞቱም የሚያስችል የተፈጥሮ ንጥረ ነገር የተሟላለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

‹‹ምቹ ሁኔታ ለሚያጠቡ እናቶች እናስተምር፣ እንደግፍ!›› በሚል መሪ ቃል ለአንድ ሳምንት የተካሄደውን የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት አስመልክቶ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ መሠረት (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ሕፃኑ ለዕድገቱ የሚያስፈልገውን ምግብና ውኃ ከእናት ጡት ብቻ ማግኘት አለበት፡፡

በጤና ባለሙያ ካልታዘዘ በስተቀር ከጡት ወተት ሌላ ምንም ዓይነት ነገር ማለትም የተለያዩ የእንስሳትና የፋብሪካ ምግቦችን፣ ፈሳሾችንና ውኃን የመሳሰሉትን መስጠት ፈጽሞ እንደማይመከር ተናግረዋል፡፡

ከስድስት ወራት በኋላ በቀጣይ ለሁለት ዓመታት ከእናት ጡት ወተት በተጨማሪ ምግብ መስጠት ማስፈለጉን፣ ሴቶችም ለማጥባት እንዲያስችላቸው መንግሥት በፊት የነበረውን የወሊድ ፈቃድ ወደ አራት ወራት ከፍ ማድረጉንና ሥራ ላይ ያሉ እናቶች ጡታቸውን ማጥባት መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት የዱቄት ወተት በገበያ ሲሸጡ፣ ማስታወቂያዎቻቸውም ሲሠራጩ እንደሚስተዋሉና ሲነገሩም እንደሚሰማ አክለው፣ ማስታወቂያዎቹ ለዚህ ሲባል የወጣውን መመርያና ሕግ በጠበቀና በተከተለ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው፣ ሲተዋወቁም የእናት ጡት ወተትን በልጠው መሆን እንደሌለበት አመልክተዋል፡፡

እናት በተለያየ ምክንያት ማጥባት ባትችል፣ ብትታመም ወይም በሕይወት ባትኖር ሌላ አማራጭ መውሰድ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ በዚህ ወቅት አሳዳጊዎች አማራጭ የዱቄት ወተት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹እናቶች በሚመችም በማይመችም ሁኔታ ውስጥ ጡት እንዲያጠቡ መደገፍና ማበረታታት ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም አንዳንድ ተፈናቃይ እናቶች በመጠለያ ውስጥ ሆነው ሲወልዱ የጠቀምናቸው መስሎን ዱቄት ወተት መስጠት የለብንም፡፡ ከዚህ ሁሉ ጡቷን እንድታጠባ ማበረታታትና መደገፍ ይገባል፡፡ ከዚህ በዘለለ ደግሞ በገንዘብና በቁሳቁስ መደገፍ፣ የሥነ ልቦናና የአዕምሮ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ሕፃናትን በመንከባከብና በማሳደግ ሴቶች ሰፊውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ሥራ ጫና የሚያመጣና ለሥራ ተሳትፎ ያላቸውን ጊዜ የሚቀንስ ነው፡፡ የልጃቸውን ጤናና ዕድገት ለመጠበቅ ሁለቱም ቤተሰቦች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ጡት ማጥባት ለእናቶች ብቻ የሚተው ሳይሆን የትዳር አጋሮች፣ ቤተሰብና ማኅበረሰብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በተለይም የጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍና ዕገዛ ሊያበረክቱ በአጠቃላይ በየጤና ተቋማቱ ለሕፃናት ምቹ ‹‹ቤቢ ፍሬንድሊ›› የተባለው መርህ በአግባቡ ሊተገበር ይገባል፡፡

ሕፃኑ እንደተወለደ ከእናቱ ጡት የሚወጣው ‹‹እንገር›› ሁለት ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ጠቀሜታ በሽታን ይከላከላል፡፡ ሁለተኛው ጠቀሜታ ደግሞ የጡት ወተትን የማመንጨት አቅም ያጎለብታል ያሉት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ ሥርዓተ ምግብ ቡድን መሪ ወ/ሮ ሕይወት ዳርሰኔ ናቸው፡፡

እንደ ቡድን መሪዋ፣ እናቲቱ ሕፃኑን ቀንና ሌሊት የተቻላትን ያህል ጊዜ ብታጠባ ጡቶቿ በቂ ወተት እንዲያመነጩ ከመርዳቱ በተጨማሪ፣ ጡቶቿ በጣም አግተው ሕመም እንዳያስከትልባት ይከላከላል፡፡

የሚያጠቡ እናቶች ወትሮ ከሚመገቡት ምግብ ሁለት ተጨማሪ ምግቦች እንዲመገቡ፣ በቂ ዕረፍት እንዲያደርጉ፣ ጭንቀት ወይም ሥነ ልቦና ጫና ከሚያሳድሩ ነገሮች በተቻለና አቅም በፈቀደ መጠን እንዲርቁና እንዲላቀቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ድጋፎችን ማግኘት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡

በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ሳቢያ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ እናቶች የንፁህ መጠጥ ውኃና የምግብ አቅርቦት ከተሟላላቸው፣ ከጭንቀትና ከድባቴ ከተላቀቁና በእናቶችና በሕፃናቱ መካከል ያለው ተፈጥሯዊ ግንኙነት ከሰመረ ሕፃኑ የጡት ወተት የማግኘት ዕድሉ የሰፋ ነው፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት በሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ፣ ዕገዛና ትብብር በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ከቡድን መሪዋ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ጥምረት አስተባባሪ ወ/ሮ እስራኤል ኃይሉ ከፍተኛ የሆነውን የሥርዓተ ምግብ መዛባት ችግር ለመቀነስና የምግብ ምርታማነትና ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸው፣ ጥምረቱ በዚህ ዙሪያ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችል እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ፣ በዓለም ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ከሐምሌ 25 ቀን እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የተከናወነው ‹‹የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት›› ዓላማዎች፣ ጡት ማጥባትን ለመደገፍ ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና ማሳወቅ፣ ጡት ማጥባት መደገፍን ከሥርዓተ ምግብ፣ ከምግብ ዋስትናና እኩልነትን ከማረጋገጥ ጋር ማያያዝ፣ ጡት ማጥባትን ለመደገፍ ከግለሰቦችና ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት፣ የባለድርሻ አካላትንና የአሠራር ሥርዓቱን አቅም በመገንባት እመርታዊ ለውጥ እንዲኖር ማድረግ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...