Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመጻሕፍት ቡፌ

የመጻሕፍት ቡፌ

ቀን:

 ሕፃናትና ወጣቶች የትምህርት ዕረፍታቸውን ከትምህርት አጋዥ በተጨማሪ ልብ ወለድ፣ ታሪክ፣ የሥነ ልቦና መጻሕፍትን በማንበብ ክረምቱን ይዘልቃሉ፡፡  

 ተማሪዎችና አስተማሪዎች ከትምህርቱ ገበታ የሚለዩበትና የሚያርፉበት በመሆኑ ከሌላው ወቅት በተለየ መጻሕፍትን ከማንበብ ጋር ይገናኙበታል፡፡ 

አንባብያን፣ ደራስያን፣ ጸሐፊያን፣ ተርጓሚያን፣ ከአሳታሚዎች ጋር በማገናኘት ረገድ፣ ለንባብ ባህል መዳበር ቁልፍ ሆነው የሚታዩት የመጻሕፍት መደብሮችና ዓውደ ርዕዮች ናቸው፡፡

ሕፃናቱ የወላጆቻቸውን እጅ ይዘው የመጽሐፍት መረጣቸውን ተያይዘውታል፡፡ አንዳንዶች መጽሐፍት ሲገዛላቸው የመጀመርያቸው ሲሆን፣ አብዛኞቹ ግን ከወላጆቻቸው ጋር የተረት መጻሕፍትን አብሮ የመግዛት ልምድ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

አምስተኛው የንባብ ለሕይወት የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ በርካታዎች የተሳተፉበት ነው፡፡ እናቴ ‹‹ይኼኛው ይሻላል››፤ አባቴ ‹‹እኔ የምፈለገው በቢጫ ቀለም ያማረውን መጽሐፍ ነው›› እያሉ የመጽሐፍት ምርጫቸውን ለወላጆቻቸው በተኮላተፈ አንደበታቸው የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

እግረ መንገዳቸውንም ‹‹በአምስተኛው የንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ›› ላይ በድንገት የተከሰቱና መጻሕፍት ገበያውም ያስደመማቸውም አይታጡም፡፡

በዓውደ ርዕዩ ሥራዎቻቸውን ይዘው ከቀረቡ ገጣሚያን መካከል ገጣሚ ታገል ሰይፉ ይገኝበታል፡፡

ላለፉት 26 ዓመታት ሲጽፋቸው የቆዩ፣ 2012 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ታትመው ለንባብ ያልበቁ አራት መጻሕፍት በዓውደ ርዕዩ አቅርቧል፡፡

ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር፣ የሕፃናቱ የተዘጋጀ የእንቅልፍ ዳር ወጎች፣ የልቤ ክረምቱና ስለግጥም ምንነት መግቢያና ተልባና ጥጥ የተሰኙ መጽሐፍትን ለገበያ አቅርቧል፡፡

ዓውደ ርዕዩ ላይ በርካታ ዜጎች እንደተገኙና አቀባበላቸውም ጥሩ እንደነበር ገጣሚ ታገል ተናግሯል፡፡

የተለያዩ ይዘት ያላቸውን አሥራ አንድ መጻሕፍት የጻፈው ገጣሚ ታገል የጎብኚዎች ፍላጎትና ደስታ እንዳስገረመው ተናግሯል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ከተሳተፉ ጎብኚዎች የተሰጠው አስተያየት ለወደፊቱ ትልቅ የቤት ሥራ እንደተሰጠው ገልጿል፡፡

የአብዛኛው የጎብኚ አስተያየት የመጻሕፍት ዓውደ ርዕዩ በየሦስትና አራት ወራት መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

የዓውደ ርዕይ ገበያ

ሁሉም እንደ አቅሙ የሚገበያይበት መሆኑን፣ በተለያዩ የገበያ ማዕከላት እየጮሁ እንደሚሸጡት ሁሉ ከ25 ብር ጀምሮ መጻሕፍት ተሸጧል፡፡

ደራሲውና አሳታሚው ከገዥ ጋር በቀጥታ የተገናኘበት በመሆኑ ዋጋው ቅናሽና ብዙዎች እንዲገዙ ዕድል የከፈተ ነው ተብሏል፡፡ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የልብ ወለድ፣ የእውነተኛ ታሪክና የሕፃናት መጻሕፍትን ጨምሮ በዓውደ ርዕዩ ቀርበዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጥንት መጻሕፍት፣ የእስልምና ሃይማኖት መጻሕፍትና ሌሎችም ዓይነቶች እንደቀረቡ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ቃኝቷል፡፡

ትልልቅ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ በየሦስት ወራት መዘጋጀት አለበት በሚል አስተያየት የሰጡን ደግሞ፣ በዓመት አንዴ መሆኑ መንግሥትና ባለሀብት ትኩረት ያለመስጠታቸው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማይረብሽ፣ ሕንፃ የማያቃጥልና ድንጋይ የማይወረውር ትውልድን ለመፍጠር የሚያነብ ትውልድ መገንባትና ለዚህ ደግሞ መጽሐፍት በቅናሽ የሚያገኙበት ዕድል ማመቻቸት እንደሚገባ ገጣሚ ታገል አስረድቷል፡፡

የሙዚቃ ኮንሰርትን በስፖንሰርነት የሚደግፉ ብዙ ድርጅቶች መኖራቸውን፣ የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይን በመደገፍ ንብረቶችን የማያቃጥልና የማያወድም ትውልድን ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሥነ ጽሐፉ ዘርፍ ውስጥ እንደሚሠሩ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል አደል መጻሕፍት ከሸመቱት መካከል ይገኙበታል፡፡ በዓውደ ርዕዩ መጻሕፍት በዓይነትና በብዛት መቅረቡን፣ ነገር ግን ከአንባብያን ጋር ለማድረስ የሚያግዝ ድልድይ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ይህም ንባብና ሙያዊ ሒስ መሆኑን አቶ ሳሙኤል አስረድተው፣ በዓውደ ርዕዩ የመጻሕፍት ዳሰሳ መደረጉን አድንቀዋል፡፡

ማንበብ በዙሪያው ያለውን ዓለም የማወቅና የመረዳት ችሎታን የሚያሻሽል ተከታታይ ችሎታዎችን እንዲያዳብር ያግዛል ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ትምህርታዊ ድርሰት፣ መረጃ ሰጪና አልፎ አልፎ የመዝናኛ ወይም ልብ ወለድ ጽሑፎችን (ሥነ ጽሑፍ) በማንበብ በእውነተኛ ሕይወት ውስጥ የሚታዩትን ምክንያትና ውጤት ትርጉምን ለመረዳት ያግዛል ብለዋል፡፡

ንባብ  የማመዛዘን ችሎታን የሚያጎለብትና ሒሳዊ አስተሳሰብን  የሚያነቃቃ በመሆኑ፣ ሰዎች  በአካባቢያቸው ያሉትን ክስተቶች የበለጠ እንዲያውቁ፣ የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማቸውና ወጥ የሆነ የግል ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በርካታ ነጋዴዎች፣ ደራስያንና ተቋማት የተሰባሰቡበት ዝግጅት  መሆኑን፣  ገበያው  ከ25 ብር እስከ 3,000 ብር ለአንድ መጸሐፍ ብር መሸጡን ገልጸዋል፡፡ 

ሕፃናት የቦረቁበትና ከመጸሐፍ ጋር የተገናኙበት መሆኑን አቶ ሳሙኤል አስረድተው፣ ትውልድን ለመፍጠር ማንበብ ጠቀሜታ እንዳለው አክለዋል፡፡

የመጽሐፍት ዓውደ ርዕዮች በመንግሥት፣ በግል ተቋማትና በባለሀብቶች በመታገዝ ትውልዱ ላይ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጻሕፍት አሳታሚዎች፣ ደራሲያንና የምርምር ማዕከላት የተሳተፉ ሲሆን ከ50 በላይ መጻሕፍት ተመርቀዋል፡፡

አዳዲስ መጻሕፍት በቅናሽ የሚገኝበት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢቡክ በነፃ የተዘጋጀበትም ነበር፡፡ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በተደረገው የንባብ ለሕይወት ዓውደ ርዕይ፣ የልጆች መማሪያዎችና የተረት ተረት ሌሎችም መጻሕፍት በብዛት ለገበያ ቀርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ከንባብ ለሕይወት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሚሰናዳው ዓውደ ርዕይ፣ በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...