ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሚቴ (አይአርሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ድንገተኛ ችግሮች ሲከሰቱ አፋጣኝ መሠረታዊ ሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ይታወቃል፡፡ በተለይ የዜጎች መፈናቀል፣ የጎርፍ አደጋ፣ የመጠጥ ውኃ እጥረት፣ ድርቅ እንዲሁም ጤና ላይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይሰጣል፡፡ በኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው ክልሎች አንዱ ደግሞ ኦሮሚያ ነው፡፡ በኦሮሚያ በበሽታ፣ በጎርፍ፣ በረሃብ፣ በመጠጥ ውኃ ዕጦት እንዲሁም የመፈናቀል ችግር ለገጠማቸው ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ በክልሉ ከ3.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከ150 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መሠረታዊ ድጋፎች እየለገሰ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የመጀርያውን ድጋፍ ማድረስ ችሏል፡፡አቶ አብዲሳ መሐመድ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ክፍል ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ዳዊት ቶሎሳ ድርጅቱ በክልሉ እያደረገ ስላለው ድጋፍ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሰብዓዊ ድጋፉን በምን ዓይነት መንገድ እያደረጋችሁ ነው?
አቶ አብዲሳ፡- ዋና ቢሮውን በአዳማ ያደረገው አይአርሲ ችግሩ በተፈጠረበት ቦታ ላይ በ72 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ድጋፉ በተለያዩ መንገዶች የሚደረግ ሲሆን ከድርቅ፣ ከጤና፣ ከንፁህ የመጠጥ ውኃ ዕጦት እንዲሁም ከዜጎች መፈናቀል ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ችግሮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በዚህም የውኃ ችግርን ከመፍታት አንፃር የገንዘብ ዕርዳታና አደጋን የመከላከል መሠረታዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለሦስት ወይም ለስድስት ወራት ወይም ለዓመት የሚዘልቅ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ድንገተኛ ችግር ሲያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ የት አካባቢዎች ላይ ነው ድጋፍ እያደረጋችሁ የምትገኙት?
አቶ አብዲሳ፡- ድርጅቱ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአዳማ የሚገኘው ዋና ቅርንጫፍ ግን በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ላይ ችግሮች ሲከሰቱ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡ በኦሮሚያ ባሌ፣ ሐረርጌ፣ አርሲና ምሥራቅ ሸዋ እንዲሁም ምዕራብ ክፍሉ ላይ እንሠራለን፡፡ አይአርሲ በዋነኛነት የሚሠራው በተለይ አብዛኞቹ የኦሮሚያ ቆላማ ሥፍራዎች ውኃ አጠር በመሆናቸው በይበልጥ ውኃ ማቅረብ ላይ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ በአካባቢያቸው ውኃ ካለ ወጥቶ በአግባቡ እንዲጠቀሙ እናደርጋለን፡፡ በአካባቢው ውኃ ከሌለ ደግሞ በቦቴ እየመጣ እንዲዳረስ እናደርጋለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሕይወታቸው አሥጊ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙት የገንዘብ ድጋፍ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ምን ዓይነት ድጋፍ ታደርጋላችሁ?
አቶ አብዲሳ፡- ለተፈናቀሉ ወይም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉ ተረጂዎች ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ድጋፎችን እንደግፋለን፡፡ ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ቤታቸው የተመለሱ ካሉ ቤታቸውን ዳግም እንዲገነቡ መኖሪያቸውን የሚሠሩበት ቁሳቁስ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ቆርቆሮ፣ ሚስማር እንዲሁም ተመሳሳይ የቤት መሥሪያ ቁሳቁሶች እንደ ሁኔታውና አካባቢው ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ሌላው ተፈናቃዮች ባሉበት ሥፍራ ላይ በተለይ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን የሥነ ልቦና ጉዳት ለመቀነስ እንሠራለን፡፡ በከተማ ላይ በማኅበር በማደራጅት ኢኮኖሚያቸውን የሚያጠናክሩበት ሥራዎችን እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት፣ በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ ተፈናቅለው ለተጠለሉ ዜጎች ድጋፍ አድርጋችኋል፡፡ ስለሁኔታው ቢያስረዱን?
አቶ አብዲሳ፡- በባሌ ዞን በደሎ መና ወረዳ በከሌ ጎልባ ቀበሌ ላይ ነው ተፈናቃዮቹ የሚገኙት፡፡ በዚህ ቀበሌ ላይ ከወር በፊት በተከሰተ የድንበር ግጭት ምክንያት ከስምንት ሺሕ በላይ ዜጎች ከአጎራባች ቀበሌ ተፈናቅለዋል፡፡ እኛ መፈናቀላቸውን የሰማነው መፈናቅሉ ከተከሰተ ሁለት ሳምንት በኋላ ነበር፡፡ በዚያ ጥያቄ መሠረት ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጥናት አደረግን፡፡ በጥናታችን መሠረት ዜጎቹ አፋጣኝ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸውና ቶሎ መድረስ ስለሚገባን ከአውሮፓ ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፍና ከአይሪሽ ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ባገኘነው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ መርዳት ችለናል፡፡ በዚህም በሁለት ቀበሌዎች ከ2,000 በላይ አባ ወራዎችን በ72 ሰዓት ውስጥ 17 ዓይነት መሠረታዊ ድጋፎችን ልናደርስ ችለናል፡፡
ሪፖርተር፡- በአብዛኛው የሚቀርብላችሁ የዕርዳታ ጥያቄ የትኛው ነው?
አቶ አብዲሳ፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚቀርብልን የዕርዳታ ጥያቄ ከድርቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የዜጎች መፈናቀል ነው፡፡ አሁን ግን እኛ አብዛኛው እየሠራንባቸው ያለነው በድርቅ ላይ ነው፡፡ በተለይ የባሌ ቆላማ ቦታዎች፣ ሐረርጌና አርሲ አካባቢዎች በውኃ ዕጦት ምክንያት ለድርቅ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሌላው የኮሌራ በሽታ በባሌ ተከስቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ችለናል፡፡ በሐረርጌም የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በቅርቡ ምላሽ የሰጠንበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በዕርዳታ ወቅት እንደ ችግር የሚጠቀስ ጉዳይ አለ?
አቶ አብዲሳ፡- ድርጅታችን ችግሩ በተከሰተበት ሥፍራ ላይ ችግርን ተቋቁሞ መድረስ የሚችል ቡድን አለው፡፡ ሁሉም የዕርዳታ ጥሪ የራሱ የሆነ ፈተናዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ የእኛ ቡድን በተቻለው መጠን ችግሩን ተጋፍጦ፣ ዕርዳታውን ማድረሱ የማይቀር ነው፡፡ ሆኖም በተፈለገው መጠን መድረስ አለመቻል፣ የአካባቢው ምድራዊ አቀማመጥ አመቺ አለመሆንና የአየሩ ሁኔታ ፈታኝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ድጋፍ ከማቅረብ ባሻገር ማኅበረሰቡ ዘለቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ያለው ሚና ምን ይመስላል?
አቶ አብዲሳ፡- ማኅበረሰቡ ጋር ካለው ፍላጎት አንፃር እኛ ሙሉ በሙሉ አሟልተናል ማለት አይቻልም፡፡ ብዙ የተጓደሉ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በአንፃሩ እኛ በምንሰጣቸው ድጋፎች ላይ ቀጣይነት እንዲኖረውና የአካባቢው ኅብረተሰብ ኃላፊነት ወስዶ በባለቤትነት እንዲያስቀጥለው የሥራው አካል እንዲሆን እናደርጋለን፡፡ በእርግጥ አፋጣኝ ድጋፍ አድርገን የምንወጣባቸው አካባቢዎችን አያካትትም፡፡ ለምሳሌ የውኃ ከሆነ እኛ ከወጣን በኃላ ከማኅበረሰብ ውስጥ ኮሚቴዎችን መርጠን እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ ከዚያም በዘለለ ወረዳው ድረስ ቡድን በማዋቀርና በቅርበት እንዲከታተል አስረክበን እንወጣለን፡፡ ለእንዳንዱ ሥራችን የመውጫ ስትራቴጂ አለን፡፡