በአክሊሉ ወንድአፈረው
በብልፅግና የሚመራው በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መሀል ለሚደረገው ድርድር እስካሁን ሒደቱን ሲመራ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሕወሓት ሰዎች ድርድሩን ይመሩ የነበርቱት ኦባሳንጆን ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ያዘነበሉ ወገንተኛ ብቻ ሳይሆኑ ዘገምተኛም ናቸው በማለት፣ እሳቸው ከአደራዳሪነት እንዲነሱና በምትካቸውም የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪ እንዲሆኑ በቃል አቀባያቸውና በተለያዩ መግለጫዎቻቸው በኩል አሳውቀዋል፡፡
ይህ የሕወሓት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ያደራድሩን የሚለው አቋም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በቀጥታ አይሆንም የሚል መልስ ባይሰጥበትም፣ ደግሞ ደጋግሞ ድርድሩ መካሄድ ያለበት በአፍሪካ አንድነት ሥር ነው የሚለውን አቋሙን ግን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ለረዥም ጊዜ ሲነግሩን የነበረው፣ እነሱ የሚደግፉት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል መሆን እንደሚገባው የሚያመላከት ነበር፡፡ ያም ሆኖ የፕሬዚዳንት ኡሁሩን ወደ አደራዳሪነት መምጣት ሲቃወሙ አልተሰማም፡፡
ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ መቀሌ ተጉዞ የነበረው የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምሥራቅ የአፍሪካ ልዩ ልዑካን ይህን የአደራዳሪነት ሚና በተመለከት፣ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል መሆን እንደሚገባው እንደሚያምኑ አሳውቀው ነበር፡፡
ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. (August 6, 2022) በሪፖርተር ጋዜጣ የእንግሊዝኛ ዕትም እንደተዘገበው፣ በአዲስ አበባና በመቀሌ ተገኝተው የነበሩት እነዚህ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑካንንና የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ኮሚቴ በአዲስ አበባ ባደረጉት ስብሰባ የድርድሩ ሒደት በቀጣይነት በአፍሪካ ኅብረቱ ተወካይ በኦባሳንጆ ስብሳቢነት እንዲካሄድ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ በአደራዳሪው ቡድን ወስጥ እንዲካተቱ የሚል ወሳኔ እንዳስተላለፉ ይፋ ሆኗል፡፡
ይህ አዲስ ክስተት በአጠቃላይ ፍትሐዊና ውጤታማ የድርድር ሒደት አንፃር ሲመረመር የሚኖረው ጠቀሜታና ጉዳት በአጠቃላይም አንድምታው ምን ሊሆን ይችላል? ምንስ ያስከትላል? ብሎ መመርመር እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጽሑፍም ይህንኑ ይቃኛል፡፡ በማስከተልም የተሻለ ውጤት ለማስገኘት የሚያግዙ ምክረ ሐሳቦችንም ያቀርባል፡፡
አሽማጋዮች ወይም አደራዳሪዎች ከወገንተኘነት የራቁ ራሳቸውንም ያወቁ የመሆን አስፈላጊነት
የቅራኔ አፈታት አዋቂዎች በተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት አሸማጋዩ ወይም አደራዳሪዎች ውጤታማ ለመሆን ከሚይስፈልጓቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ቁልፉ ጉዳይ ራስን ማወቅ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ አሸማጋዮች ተፃራሪ ተደራዳሪዎችን የማቴርያል፣ የዲፕሎማሲ፣ ወዘተ ድጋፍ በመስጠት፣ ለድርድር የሚሆን ወጪን በመሸፈን፣ ስለድርድር አካሄድ ዕውቀትን በማካፈል፣ ወዘተ ሊያበረክቱት የሚችሉበት ብዙ ጉዳይ እንዳለ ሁሉ፣ አደራዳሪዎች የሚወክሏቸው መንግሥታትና ድርጅቶች የቀደመ ወገንተኛነት መኖር በድርድሩ ሒደት ነፃነትና ተቀባይነት ላይ ታላቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
በመሠረቱ አሽማጋይ ወይም አደራዳሪነት በተለይም በዓለም አቀፍ ቅራኔ አፈታት ውስጥ በከፊል የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን በግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታት ወይም ድርጅቶች በድርድር ሒደት በአሸማጋይነት ሲሠለፉ የራሳቸውን የውጭ ጉዳይ ጥቅም በግንዛቤ ውስጥ አስገብተው እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንዳንዱ አሸማጋይነት ውጤታማና ዘላቂ ሰላምን ለማስገኘትም ታላቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሁሉ፣ አንዳንዱ ደግሞ በተፋላሚዎች መሀል የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ሁኔታውን አወሳስቦ እጅግ አስቸጋሪ ምስቅልቅል በመፍጠር የበለጠ ጥፋት ሊጋብዝ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኃያላኑ በአደራዳሪነት የሚሠለፉት ለችግሩ ቋሚ መፍትሔ ለማስገኘት ሳይሆን፣ የሚታየው ግጭት ከሚገኝበት ደረጃ አልፎ ሰፋ ያለ ጥፋትን ሳያስከትል ባለበት ደረጃ እንዳለ እንዲቆይ ለማድረግም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌም በኮሶቮና በቦስንያ በ1990ዎቹ መጨረሻ የኃያላኑ ዓላማ በከፊል ይህ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2012 ይፋ ባደረገው ዶክመንት በቅራኔ አፈታት ውስጥ የአሸማጋይነት ሚናን ውጤታማ ለማድረግ ሊሟሉ የሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው ብሎ ካቀረባቸው ስምንት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ የአሸማጋዮች ገለልተኛነት (Impartiality)፣ በተደራዳሪ ወገኖች በኩል የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማግኘት (Consent)፣ የሽምግልናው ሒደት አገር በቀል በሆነ ባለቤትነት መመራቱ (National Ownership) የሚሉት ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ በአገራችን የሰሜን ክፍል የተፈጠረውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት በአዲስ መልክ በአደራዳሪነት የተጨመሩት የአሜሪካ መንግሥት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቋም ምን ይመስላል? ለመሆኑ በዚህ ግጭት ውስጥ እነዚህ ክፍሎች ገለልተኛ ናቸው? ድርድሩን በገለልተኛነት መምራትና ተዓማኒ ሊሆኑስ ይችላሉ? ለድርድር በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ ሊያስፈጽሙት የሚፈልጉት አቋም አላቸው? ይህንን የአደራዳሪነት መድረክ ተጠቅመው የእነሱን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያደርጉት አካሄድስ ከአገራችን ፍላጎት ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል? ለመሆኑ የምዕራባውያኑ የአደራዳሪነት መታከል የሁሉንም ተቀባይነት አግኝቷል? የድርድር ሒደቱን አገር በቀል ወይም አኅጉራዊ ባለቤትነት እንዲኖረው ያደርጋል? ወይስ አሳልፎ ለምዕራብ አገሮች ይሰጣል? የሚሉትን ቀረብ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡
የአደራዳሪዎቹና የዕጩ አደራዳሪዎቹ አቋም ሲመዘን
የአሜሪካ መንግሥት ከሰሜኑ ጦርነት እየገፋ መምጣት ጋር ተያይዞ ጦርነቱ እንዲቆምና ችግሩንም ተፋላሚዎቹ ወገኖች በሰላም እንዲፈቱ የሚል ዕወጃ ሲያሰማ የቆየ ቢሆንም፣ በድርድሩ ውስጥ ዋና ዋና በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ግልጽ አቋም ይዞ ይህ መደረግ አለበት የሚላቸውን ለማስፈጸም በተለይም በኢትዮጰያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ ተፅዕኖዎች ውስጥ የተለያየ ማዕቀብ መጣል፣ የፀጥታ ትብብርና የበጀት ድጎማ መከልከልና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአጀንዳነት አስይዞ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ውግዘትና ተፅዕኖ እንዲደረግበት በተደጋጋሚ ማድረጉ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በድርድሩ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ይፈጥራል በሚባለው የወልቃይት ጠገዴና የአማራ ልዩ ኃይል በዚህ ቦታ የመገኘት ጉዳይ በተመለከተ፣ የአሜሪካ መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል ከአካባቢው መውጣት አለበት በማለት ደግሞ ደጋግሞ በተለያዩ ባለሥልጣናቱ በኩል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው አለ የሚሉትን የኤርትራ ሠራዊትም ከኢትዮጵያ መውጣት አለበት በማለት፣ ኢትዮጵያ የውስጥ አስተዳደር ክልሎችን ድንበር መቀየር የለባትም፣ ወዘተ በማለት በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ደግሞ ደጋግሞ በመግባት ሲናገሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ይህ መጠነኛ መረጃ የሚያሳየው የአሜሪካ መንግሥት የትግራይ ግጭትን በተመለከተ እጅግ ጠንካራ አቋም ወስዶ፣ እሱንም ለማስፈጸም ከፍተኛ ዕርምጃ እንዲወስድ ነው፡፡ ይህም የአሜሪካ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ (Impartiality) አለመሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ ነው፡፡
አሜሪካ በመላው አፍሪካና በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የቻይናን በቅርቡም የሩሲያን እየተጠናከረች መምጣት አጥብቃ የምትቃወም፣ ይህንንም ለማስቆም የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደምትወስድ ይታወቃል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊትም የቻይና መንግሥት በትግራይ በኩል የሚታየውን ግጭት በሰላም ለመፍታት እፈልጋለሁ ብሎ ለዚህ ቀጣና ልዩ መልዕክተኛ መመደቡም የሚታወቅ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብፅ መንግሥት የሚያራምደውን አቋም፣ በአሜሪካ በኩል ለማስፈጸም ያደረገውንና አሁንም እያደረገ ያለውን ጥረት፣ የአሜሪካ መንግሥትም (ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እንደሰማነው) የግብፅን አቋም ለማራመድ ምን ያህል ሊጓዝ እንደሚችል በግልጽ የታየ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአሚሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ጉዳይ ይዞ የሚጓዘውን ዘርፈ ብዙና የተወሳሰበ ጉዳይ ስናጤን፣ የአሜሪካ በአደርዳሪነት መግባት የአገራችንን ችግር ከመፍታት ይልቅ እንዳያወሳስበው ያሠጋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት
የአውሮፓ ኅብረትም ከላይ የተነሱትን ጉዳዮች በተመለከተ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳየው አቋም ከአሜሪካ መንግሥት የተለየ አይደለም፡፡ ይህም መሠረታዊ የሆነውን የአሸማጋዮች ገለልተኛነትን አስፈላጊነት የሚቃረን፣ የድርድር ውጤቱንም ከማገዝ ይልቅ አስቸጋሪ ቅርቃር ውስጥ ሊጥል የሚችል አደጋ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙውን ጊዜ በተመሳሳይ የቅራኔ አፈታት ሽምግልና ውስጥ ራሱን የሚያስገባው በፀጥታ ምክር ቤት ውሳኔና በቅራኔው ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች በሚያቀርቡት ጥያቄ ወይም ግብዣ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተመሳሳይ ሒደት ውስጥ ራሱን ለመዝፈቅ እጅግ የሚጠነቀቅ ቢሆንም፣ በተለይም ኃያላን መንግሥታት የእነሱን አካሄድና ፍላጎት ድጋፍ ለማስገኘት ተሳታፊ እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት ያካሂዳሉ፡፡ በአገራችን ሁኔታ ታዲያ በዚህ የድርድር ሒደት ውስጥ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሳተፉ ጥሪ አድርጎ ነበር? የፀጥታው ምክር ቤትስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያትቶ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር? የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡
በእርግጥ የሕወሓቱ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ተከታታይ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደጻፈ ቢታወቅም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ ግብዣ መቅረቡ አይታወቅም፡፡ በዚህ አኳያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በድርድሩ ቀጥተኛ አደራዳሪ ሆኖ መቅረብ ምናልባት ድርድሩ ውስጥ የሚነሱ የአደራዳሪዎች ሐሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት አልቀበልም ቢል፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጨምር ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ለማድረግ ታቅዶ የተወሰደ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ነው ብሎ መገመትም ይቻላል፡፡
የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማግኘትና የሽምግልናው ሒደት አገር በቀል በሆነ ባለቤትነት መመራቱ
አለመታደል ሆኖ የሰሜኑን የአገራችንን ችግሮችንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን በአገር በቀል ድርጅቶችና የአገር ሽማግሌዎች ለመፍታት ኢትዮጵያውያን አልታደልንም፡፡ ትናንት ከትናንት ወዲያ እጅግ ውስብስብ ችግሮችን በሱዳን፣ በናይጄሪያ ቢያፍራ፣ ወዘተ ይፈቱ የነበሩ አባቶቻችንና እናቶቻችን ልጆች እንዳልሆንን ሁሉ፣ እነሆ ዛሬ ቅራኔ ለመፍታት ሳይሆን ለማሸማገልም አስቸጋሪ እየሆነ መጥተናል፡፡
የሰሜኑን ግጭት ለመፍታት ለድርድር ሒደቱ አገራዊ ባለቤትነት ያስፈልጋል ሲባል ኢትዮጵያዊ አደራዳሪ ባይኖርም፣ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ በአጀንዳ አቀራረፅ፣ በአሸማጋዮች ምርጫ፣ ወዘተ ላይ ተፋላሚዎች ሙሉ ባለቤትነት ወይም ወሳኝነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ አደራዳሪውም ኢትዮጵያዊ ድርጅት ባይሆንም ቢያንስ አፍሪካዊ የማድረግን አስፈላጊነት ያሳያል፡፡ ከዚህ አኳያ አፍሪካ ሰውም ብቃትም እንደሌላት በሚያስመስል ደረጃ የድርድሩን ሒደት ቁልፍ ተግባር፣ ማለትም አደራዳሪነትን ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካ መስጠት የአገር በቀል ባለቤትነት መንፈስን የሚፃረር ነው፡፡
አስፈላጊ ከሆነ የአፍሪካ ኅብረት የድርድር ኮሚቴውን በአፍሪካውያን ባለሙያዎች እንዲጠናከር ማድረግ እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በመላው አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው ጥቁር ሕዝብ ዘንድ የነፃነት ታላቅ ምሳሌ የሆነችው ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ለመፍታት ራሷን አለመቻሏ እጅግ አሳፋሪ ቢሆንም፣ ከዚህ አልፎ ከአፍሪካዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሳይሆን የምዕራቡን አደራዳሪነት መጋበዝ ታላቅ ሥነ ልቦናዊ ሽንፈትም ነው፡፡ አፍሪካ የደቡብ አፍሪካው የእነ ታቦ ኢምቤኪ፣ የላይቤሪያዋ ኤሊኖር ጆንሰንን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ያሉባት አኅጉር መሆኗ ከቶውንም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ያለ ሁሉም ተደራዳሪዎች ምዕራባውያኑን አገሮች በአሸማጋይነት ማካተት የራሱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመርያን ብቻ ሳይሆን፣ የአሸማጋዮች ተቀባይነት ማገኘት (Consent) ጽነሰ ሐሳብ የሚፃረር ነው፡፡
ምን መደረግ አለበት?
በአገራችን ውስጥ የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር ማስቀጠል ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለገዥው ድርጅት የሚያስገኘው ጠቀሜታ የለም፡፡ በተፃራሪው ግጭቱ እየቀጠለ ሲሄድ በአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስተሮች በካፒታል ፍሰት፣ በቱሪዝም፣ በሰላም ከቦታ ቦታ በመዘዋወር፣ በሕዝብ መፈናቀል፣ ወዘተ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሰላምን መምረጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ይህንም ለማደረግ የተጀመረው ወይም ይጀመራል የሚባለው ድርድር እኩልነትን፣ ተጠያቂነተን፣ የሕዝብን መብት፣ የአገር አንደነትንና ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ውጤትን ለማስገኘት በሚያስችል መንገድ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ውስብስብ የሆነውን የአገራችንን ግጭት ይበልጥ ሊያወሳስቡ የሚችሉ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በዚህ ውስጥ እንዲታከሉ ማድረግ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ከዚህ አኳያ በአፍሪካ አንድነት የተጀመረው የሽምግልና ሒደት ውጤታም እንዲሆን የሚከተሉትን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት
በመንግሥት በኩል ይህን ጉዳይ ለብቻው ሊወጣው እንደማይችል ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ ድጋፍ የሌለው የድርድር ሒደት በድርድር ጠረጴዛ ዙሪያም ተደራዳሪዎችን በሙሉ ልብ እንዳይሠሩ ተጋላጭ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት (ብልፅግና) ሕዝብን በተመለከተ የተሰበረውን መተማመን ለመጠገን የሚያስችለው፣ መሠረታዊ ዕርምጃዎችን በአስቸኳይ ሊወስድ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓባይን በተመለከተ በተደረገው ድርድር በትራምፕ አስተዳደር የተሰነዘረበትን ተፅዕኖ ተወጥቶ የአገርን ጥቅም የሚያስከብር የድርድር አቋም የያዘው፣ በጊዜው መሉ የሕዝብ ድጋፍ አብሮት ስለነበረ እንደሆነ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ አሁንም በየቦታው ከሚገኘው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገቡትን ጉዳዮች (ለምሳሌ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ) ለመፍታት አዲስ ጥረት በመጀመር መተማመንን መገንባት መጀመር ይኖርበታል፡፡ ከዳያስፖራ ኮሙዩኒቲውም ጋር ምክክር በማድረግ ቅሬታዎችን ለመፍታት አስቸኳይና ልባዊ ጥረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ከውስጥም ከውጭም የሚኖረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ በአስቸኳይ መመካከርና የጋራ አቋም በመያዝ፣ በቀጣይም የተቃዋሚው ድምፅ በድርድሩ ሒደት የሚደመጥበትን አሠራር ጊዜ ሳይፈጅ ከድርድሩ በፊት ሊያስተካክል ይገባል፡፡ ድርድሩ በአፍሪካ ድርጅትና በአፍሪካውያን ብቻ መካሄድ እንደሚገባው፣ የምዕራባውያኑ ሚና በሚጠየቁበት ጉዳይ ላይ ድጋፍ ከመስጠት ያለፈ ሊሆን እንደማይገባው፣ ይህም በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በይፋ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
በኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች
የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥትን በመቃወምና የአገርን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት መሀል ያለውን ልዩነት እንደሚረዱ በመገንዘብ፣ አሁን የምዕራባውያን መንግሥታት በድርድሩ ውስጥ በአስታራቂነት ወይም በሽምጋይነት እንዲገቡ የቀረበው ሐሳብ ለአገራችንና ለሕዝባችን ዘላቂ ጥቅም ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን አንድምታ በመገንዘብ፣ ይህ ሽምግልና የአደራዳሪነት ተግባር ገለልተኛነትን በሁሉም ተቀባይነትን መሠረት አድርጎ በአፍሪካ ኅብረት ሥር በሚዋቀር አፍሪካዊ አደራዳሪዎች ብቻ እንዲመራ መታገልና ተፅዕኖም ማድረግ ጊዜው የሚጠብቀው ተግባር ነው፡፡
ይህ ጉዳይ የሁለት ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ስለሆነ፣ ተቃዋሚው በዚህ ሒደት በቀጣይነት ተሳታፊ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዲመቻች ለማድረግ ግፊት ያስፈልጋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት
የአፍሪካ ኅብረት በአደራደሪነት ወይም አሸማጋይነት ሊቀርቡ የሚገባቸው ገለልተኛ ድርጅቶች፣ የመንግሥታት ተወካዮችና ገለልተኛ ግለሰቦች ብቻ መሆን እንደሚገባቸው፣ እጅ በመጠምዘዝና በድብቅ በማስገደድ የሚገኝ መፍትሔ ዘለቄታ ያለው ሰላምን ሊያስከትል እንደማይችል ተረድቶ፣ በአስቸኳይ አሜሪካንና የአውሮፓ ኅብረትን የአደራዳሪነት ሚና በሌሎች አፍሪካዊያን ሊተካ ይገባል፡፡
የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት
የምዕራቡ መንግሥታት ሊረዱት የሚገባው የቀጣናው ጥቅም ሊጠበቅ የሚችለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ተቀባይነት ባለው የዕርቅ ወይም ሽምግልና ሒደት ውስጥ አልፎ ዕውን በሚሆን በሰጥቶ መቀበል፣ በፍትሕና በአካታች ሒደት ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ነው፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የመጀመሪያው ተግባር የአደራዳሪዎችን ገለልተኛ መሆን በሁሉም ተደርዳሪዎች ተቀባይነት ማግኘት፣ ሒደቱ በተደራዳሪዎች ባለቤትነት ሊካሄድ እንደሚገባው መቀበል ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ኅብረት ግጭቱን በተመለከተ ይዘዋቸው የቆዩትን ግልጽና ወገንተኛ አቋም ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ራሳቸውን ከአደራዳሪነት ሊያገልሉ እንደሚገባ ዕሙን ነው፡፡ ይህ ማለት የድርድሩ ሒደት የሁለቱንም ኃያላን ድጋፍ አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡
ሁለቱም ኃያላን ለድርድሩ ሲጠየቁ ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት፣ የድርድሩን ሒደት በፋይናንስ በመደገፍ፣ በተደራዳሪዎቹ የጋራ ፍላጎትና ውሳኔ ሊቀርቡ የሚችሉትን የተለያዩ የድጋፍ ጥያቄዎች በመመርመርና በመደገፍ ሊተባበሩ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡ እነዚህ ኃያላን ከአሁን በፊት በኢትዮጵያ የውስጥ አስተዳደርና አሰፋፈር ላይ ያንፀባረቋቸው አቋሞች ግልጽ ቢሆኑም፣ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ በመቆጠብና የአደራዳሪዎቹን ነፃነት በማክበር ይህ ሒደት የራሱን ይዞ እንዲጓዝ በማድረግ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁሉም በኩል የሚገኘው የአትዮጵያ ሕዝብ በጦርነቱ የደረሰበትን ጊዜያዊም ሆነ የረጅም ጊዜ ድጋፍ በሚሹ የሰብዓዊና የልማት ተግባሮች ላይ ድጋፍ በመስጠት እጅግ ጠቃሚ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡
የትግራይ ክልልና አጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ
የትግራይ ክልልና ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብም (በተለይም የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎች) መንግሥትና ሕወሓት ራሳቸውን ችለው በውስጣቸው የተፈጠረውን ቅራኔ በሰላም ለመፍታት እንደማይችሉ፣ ወደ ጦርነት የገቡበትና እስካሁንም የቆዩበት ሒደት ራሱ በቂ ማስረጃ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ሁለቱ ድርጅቶች ለብቻቸው በሚያደርጉት ድርድር የሕዝብን ችግር ከሥር ከመሠረቱ ዘላቂ ሰላም ሊያስከትል በሚችል መንገድ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ እጅግ ይከብዳል፡፡
ሰለዚህም ሕዝባችን ወደ ሌላ አሰቃቂ የግጭት ምዕራፍ የሚያሸጋግረውን ሒደት ለማምከን የሚካሄደውን ድርድር በቅርብ በመከታተል፣ ችግር ፈጣሪ ወይም አደናቃፊ የሆኑ አካሄዶችንም በየደረጃው በመታገልና ሕዝባችን በአንድነት፣ በሰላም፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ሊኖርበት የሚችል ድባብ ዕውን ለማድረግ ግፊት ሊያደርግ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊጠቀም የሚችለው ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንዳልሆነ ታሪካችን በተደጋጋሚ አሳይቶናል፡፡ ከዚህ ተምሮ ዳግም እንዳይከሰት መታገል ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡