Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቅጥፈት እንጀራ!

የዛሬው ጉዞ ከሲኤምሲ ወደ መገናኛ ነው። በዚህ በከባዱ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ሲፍጨረጨር የማይታይ ሥጋ ለባሽ የለም። ሩጫው በየአቅጣጫው ደርቷል። የማይሮጥ የለም ማለት ይቀላል። ወያላው ይጣራል። እልፍ ብሎ ከመንገዱ በቆሎ ጠባሾች የማንደጃቸውን እሳት ያራግባሉ። ከጠቆረው ሰማይ በስስ ካፊያ ተከልሎ ኃይለኛው ዝናብ እየመጣሁ ነው ይላል። እኛ ደግሞ በውስጣችን ከተለያዩ ስሜቶቻችን ጋር እንታገላለን። ቀስ በቀስ የሞላነው ታክሲያችን ጉዞ ሊጀምር ነው። ወያላው ሙሉ ለሙሉ ተንሸራታች መዝጊያውን ዘግቶ ታክሲያችን ስትፈተለክ፣ ከመዳረሻችን በፊት ያሉት መተላለፊያዎች እየተዘነጉን መጨረሻችንን ብቻ የምናስበው ለምን ይሆን ያሰኛል፡፡ ሾፌሩን አንዳች የሚያቁነጠንጠው ነገር ሰቅዞ ይዞታል። ምቾት አጥቶ ዕረፍት የነሳው ታክሲያችን ቅጥ ባጣ አካሄድ ወሰድ መለስ ይላል። ወያላው ጭምር ግራ ገባው መሰል፣ ‹‹ምነው?›› ይለዋል። ‹‹ምን እባክህ ይኼ ቀበቶ እኮ ሊመቸኝ አልቻለም። እዚህ አገር አዋጁና ሕጉ ሁሉ ሰው ማሰሪያ ነው…›› ብሎ ይመልሳል ሾፌራችን። ‹‹እንዴ በትራፊክ አደጋ የሚቀድመን አገር እንደሌለ እያወቅክ ቀበቶ አስሮ ማሽከርከርን ነፃነት ከማጣት ጋር ታወዳድራለህ?›› ትለዋለች አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት። ‹‹ኧረ ተይኝ እባክሽ፣ አሁንስ አላሠራ ያለን ይኼ ጥቃቅንና አነስተኛ መመርያና ደንብ ነው። ሕዝብ በትራንስፖርት ዕጦት ዕርምጃው ተገትቶና እንዳሻው እንዳይሮጥ ታስሮ የማይታያቸው ሁሉ፣ ይህችን ቀበቶ አድርጉ አታድርጉ እያሉ ሲበረቱብን ነው የሚገርመኝ…›› እያለ ወይ አንደኛውን ቀበቶ ማድረግን ያወገዘ ንግግር አልተናገረ፣ አሊያም ጥቃቅኑ ነገር ላይ የሚያተኩረውን ሕግ አውጭና አስከባሪ አካል አልተቸ እንዳሻው ደባልቆ ይቀደዳል። ይህም እኮ ተንታኝ ይባል ይሆን!

‹‹አሁን ስለትራንስፖርት ችግር ያነሳኸው እውነት ቢሆንም፣ መንገድ ትራንስፖርት ሥራዬ ብሎ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ቢታወቅም ቀበቶ ከማሰር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። መጀመሪያ የራስን ኃላፊነት መወጣት ነው። እውነት እንዲህ የእኛ ተሠልፎ መዋል የሚያሳስባችሁ ከሆነ እናንተስ የምትሠሩት ሥራ ልክ ነው እንዴ? ተው አንተዛዘብ ተው…›› የሚለው ደግሞ ወፍራም ኮስታራ ተሳፋሪ ነው። ሾፌሩ ምንም መልስ አልሰጠም። ነገሩ ባላሰበው አቅጣጫ እየዞረ ነበር። አጠገቤ የተቀመጠች ወይዘሮ፣ ‹‹ክፉ ልምድ…›› ትላለች በሹክሹክታ። ‹‹የራስን ቀበቶ ሳያጠብቁ የራስን ቀዳዳ ሳይደፍኑ ሌላው ላይ ለመፍረድ መሽቀዳደም። ከሰው እንዳልተወለድን ድክመትን እየዘረገፍን መወነጃጀል፡፡ ለመማር ወይም ለማስተማር ከመበርታት ይልቅ ማውገዝና ማሳደድ። ለአገር ግንባታ አንዲት ጡብ ሳያቀብሉ ነጋ ጠባ መተቸትና መሳደብ፡፡ ግን እንዴት ያለ እርግማን ነው አንተዬ?›› ስትለኝ ውስጤ ያለውን ስለተነፈሰች በአዎንታ አንገቴን ነቀነቅኩላት፡፡ በጅምላ ፍረጃና በጅምላ አስተሳሰብ እየተነዳን እስከ መቼ እንደምንቀጥል እንጃ ያሰኛል። እርግጥ ነው!

ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ ነው። ፍጥነትና ታታሪነት የራሱ እንደሆነ ይታያል። ‹‹ምናለበት ሁሉም እንዳንተ ሥራውን አክባሪ ቢሆን?›› ትለዋለች አንዲት ወጣት። ቀና ብሎ እያያት ይስቃል። ‹‹እውነት ለመናገር እኮ የድህነታችንን ያህል አይደለም ሥራ ላይ ያለን ትጋት…›› ትላለች አስከትላ። ‹‹ታዲያስ!›› ይቀበላል ከወዲያ፣ ‹‹ከአስተናጋጅ እስከ ትልልቁ ሹም ድረስ ጥቂት ሠርቶ ብዙ ማረፍ የሚታየው ነው የሚበዛው። ያለ ጠንካራ የሥራ ባህል ልማትና ለውጥ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ሥራ ፈተን ወሬ ላይ መጣዳችን ገና ብዙ ያስከፍለናል…›› ይላል ጎልማሳው። ከኋላ መቀመጫ ረድፍ ደግሞ ተሳፋሪዎች እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባላሉ። አንደኛው፣ ‹እኔን እኮ የማይገባኝ ያላደገብንን የሥራ ባህል በመፈክር በአንድ ሌሊት ሊያሸክሙን ሲጥሩ ነው…›› ይላል። አንደኛዋ ደግሞ፣ ‹‹ዝም በላቸው የስንቱን አገር ልምድና ተሞክሮ ሲያበጥሩ ምነው ሮም በአንድ ቀን እንዳልተገነባች ሳያዩት ቀሩ?›› ስትል ይሰማል። ‹‹ወትሮም መሠረት ያለው አካሄድና ዕድገት ሲለምድብን እኮ ነው። መንግሥትስ ቢሆን ያው የዚህ ኅብረተሰብ ወኪል አይደል? ከፈረሱ ጋሪው ቢቀድምበት ነው የእኛን ባህሪ ማንፀባረቁ እኮ…›› ይላል ሦስተኛው ሰው። ‹‹ለማንኛውም የምክክር አስፈላጊነት ቃል በቃል እንደሚተረጎምልን ሁሉ ጠንካራ የሥራና የትጋት መንፈስ ባለቤት መሆን የምንችልበት ተሞክሮ ጭምር ቢጠናልን ጥሩ ነበር…›› ስትል ፖለቲካ መሰል ንግግር ጣል አደረገች። ያለበለዚያ አይጣፍጥማ!      

ታክሲያችን ሳህሊተ ምሕረትን አልፎ ጉርድ ሾላ ሲደርስ ወራጆች ነበሩና ቆመ። ሁለት ወጣቶች ወርደው ጎልማሶች ተኳቸው። ሾፌራችን በደረሰበት የነገር ኩርኩም አቀርቅሮ እያሽከረከረ ነው። ሁለቱ ጎልማሶች ጨዋታቸው በእጃቸው በሚቀባበሉት መጽሐፍ ዙሪያ ነው። የመጽሐፉ ርዕስ ‘Tower in the Sky’ ይላል። ‹‹አቤት ያን ጊዜ፣ ያን የመሰለ አበባና ብሩህ ወጣት የታየበት ዘመን። የእናት አገር ፍቅር ያንገበገበው፣ የወገን ጥቃት የቆረቆረው፣ ለም አፈር ታድሎ ድርቅ የሚጫወትበት ሕዝብ ኑሮ ያስለቀሰው ትውልድ ነበር እኮ። እኔ ይቅርታ አድርግልኝ የዚያ ትውልድ አባል ስለነበርኩ ኩራቴ እስከዚህ ነው…›› ሲል አንደኛው በምልክት አገጩን እየነካ፣ ‹‹እንዴታ፣ በተለይ እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት ከዚህ በፊት ሰምቼው የማላውቀው ታሪክ ስለሆነ ያ ትውልድ ለዚህች አገር ያደረገው አስተዋፅኦና ሚና ተጽፎ የማያልቅ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ…›› ይለዋል። በአንድ ወገን ይህን ጭውውት እየሰማን ወዲያ ደግሞ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ዛሬም ያው የዕልቂት ታሪካቸውና ፖለቲካቸው አይሰለቻቸውም?›› የሚል ድምፅ ይሰማል። ‹‹እንዴት እንዲህ ትላለህ? የእነሱና የእኛ የሚባል ታሪክ አለ እንዴ?›› ትጠይቃለች ደሟ የፈላ አጠገቡ የተቀመጠች ወጣት። ከዚያማ ጨዋታና ክርክሩ ይቀልጥ ጀመር። ‹‹ኤድያ፣ አብዮት ብለው ነው አገራችንን ደም በደም ያደረጓት…›› ይላል አንዱ የዚህ ዘመን ትውልድ ተወካይ። ‹‹ጎበዝ እያስተዋላችሁ፣ ደሙን ያመጣው ፋሽስቱ ደርግ እንጂ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የዚያን ዘመን ጀግና ትውልድ አልነበረም…›› ይላል ሌላው። ‹‹ኧረ ተባለ እንዴ? ደርግ በቀይ ሽብር ሲጠየቅ፣ ያ ትውልድ የምትለው ደግሞ በነጭ ሽብር ይጠየቃል፡፡ ኃጢያትን ሁሉ አንድ ወገን ላይ እየለጠፉ መሸሽ አይቻልም ገባህ…›› ይላል ሌላው በዕድሜ ከሁሉም አነስ ያለ ልጅ እግር። ታሪኩን የሚያጣጥለው፣ ለታሪክ ቦታ ያለውና የታሪክ ተሳትፎ የነበረው እንዲህ እንዲህ እያለ አንድ ቋንቋ እያወራ በአንድ ታክሲ ተሳፍሮ እየሄደ ሲተረማመስ ላየው ጭብጥ የሌለው ተውኔት የሚመለከት ሊመስለው ይችላል። ምን ይደረግ!

ጉርድ ሾላን ስናልፍ አንዱ የባቡሩን መስመር እያየ፣ ‹‹ጉድ በል ዓይናችን እያየ እኮ ሆነ አሁንማ ለውጡ የሚገሰግሰው። የሚገርመኝ ትናንት የነበረውን ዛሬ ሳጣው ዛሬ ያጣሁትን ነገ ሳገኘው ነው…›› ይላል። ‹‹እውነት ለመናገርማ ለውጡንማ አንድ ላይ ጀምረን አራዶቹ ለብቻቸው ላፉት…›› ብሎ ከመጨረሱ ጎልማሳው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ሲመጣማ ነጣቂ እንደማይጠፋ የታወቀ ነው…›› ብሎ ከመጨረሻ ወንበር አንድ ወጣት ሲናገር ይሰማል። የለውጡ ጨዋታ በአንድ ጊዜው ተቀይሮ ምሬትና ትችት ለማድመጥ አሁንም ደቂቃ አልፈጀም። አንዱ የእጅ ስልኩ ገንዘብ አልቆበት ቴሌን ያሳጣል። አንዷ፣ ‹‹አሁን ደግሞ ከመገናኛ ለምን ያህል ሰዓት ይሆን ታክሲ ጠብቄ ተሳፍሬ ወደ መርካቶ የምሄደው?›› እያለች ስትጨነቅ ይሰማል። ወዲያ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹እርስዎ ሰውዬ በየወሩ የቤት ኪራይ መጨመር እንደማይችሉ የከተማ አስተዳደሩ መወሰኑን አያውቁም ወይ?›› እያለ በስልኩ ይጮሃል። ተንፍሰን ሳንጨርስ የሚያካልበን የችግር አባዜ ጉልበቱን አድሶ በየአቅጣጫው ተሳፋሪውን ሲወጥረው፣ ‹‹እንዲያው ምን ተሻለን እናንተ? መፍትሔው ሁሉ ጊዜያዊ ነው፣ እሱንም የሚሰማ ሲገኝ። ኧረ እንዴት ልንኖር ይሆን ወደፊት?›› ትላለች መሀል ወንበር ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች አንደኛዋ። ብሶት ሲጀመር ማለቂያው ሩቅ በመሆኑ ጆሮዬን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሳዞር ሌላ ወሬ ደርቷል፡፡ የወሬ አድባር ይባላል!

‹‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተለያዩ ወሬዎችን ሲነዙ የነበሩ ሰዎች ለመሆኑ አሁን ምን ብለው ይሆን…›› እያለ አንዱ አዲስ አጀንዳ ሲከፍት፣ ‹‹አልሰማህም እንዴ ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለው ሌላ ወሬ ጀመሩ እኮ…›› ሲል ሌላው፣ ‹‹አንዱማ በቴሌቪዥን ያየነው እኮ ከአንድ ወር በፊት የተቀረፀ ነው ብሎ አዲስ ሙግት አቀረበ…›› አለች አንዲት ቆንጆ ከወደ መሀል፡፡ ሾፌሩ፣ ‹‹ከእኔ በቀበቶ ከማማረርና ከእነዚህ የለየለት ቅጥፈት የቱ ይብሳል…›› ብሎ ሒሳብ ሊያወራርድ ሲነሳ ወያላው፣ ‹‹ኧረ በቃችሁ መጨረሻ!›› ብሎን መገናኛ ደርሰን ስንወርድ ወጣቷ እየሳቀች፣ ‹‹ዘንድሮ ቀጣፊው የባዘው ለምን ይሆን?›› በማለት ስትጠይቅ አንዱ ነገረኛ እየሳቀ፣ ‹‹ቅጥፈት እኮ የእንጀራ ገመድ መሆኑን አትዘንጉ እን…›› በማለት ተሳለቀ፡፡ ‹‹የቅጥፈት እንጀራ ባይበላስ?›› እያሉ አንድ ጠና ያሉ ሰው ሲያጉረመርሙ እኛም በየፊናችን ተበታተንን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት