Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው እሴት የሚጨምሩ የሎጂስቲክስ አገልግሎቶች፣ የማምረት ሥራዎች እንዲሁም ንግድ የሚከናወንባቸው ከባቢ ናቸው የሚል ትርጓሜ ሲሰጣቸው ይሰማል፡፡

ከዚህ በሻገር ነፃ የንግድ ቀጣና ማለት ምንም ዓይነት የንግድ እንቅፋት የሌለበት ሥፍራ ወይም ታሪፍና ታክስ ያነሰበት አካባቢ ተብሎ እንደሚጠራም በጉዳዩ ላይ የተሰነዱ የተለያዩ ጽሑፎች ያስገነዝባሉ፡፡

ኢንቨስተሮች በነፃ የንግድ ቀጣናዎች መክፈል ያለባቸው ታሪፍና ታክስ ስለሚቀንስ ኢንቨስት ለማድረግ ብዙ ካፒታል የሚያገኙበት፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያግዝ፣ የቢሮክራሲ ሒደቶች የሚቀንስ አማራጭ ስለመሆኑም በተለያየ ጊዜ ሲነገር ይደመጣል፡፡

ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩትም፣ በነፃ የንግድ ቀጣናዎች የሚገቡ ነጋዴዎች የተለያዩ የታክስ ነክ እንዲሁም ከታክስ ጋር ያልተያያዙ ማበረታቻዎች የሚያገኙ ሲሆን፣ ነፃ ቀጣናዎቹ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ለአገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ፣ ለግሽበት መቀነስ የሚኖራቸው ወሳኝ ሚና፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያላቸው አበርክቶ፣ ባጠቃላይ የሚፈጥሩትን በጎ የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ምክንያት በማድረግ አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ስለሚመሠረተው የነፃ የንግድ ቀጣና በተመለከተ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የጎረቤት አገሮች ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ለንግድ መቀላጠፍ ያበረከቱት በጎ ተፅዕኖ መኖሩን አንስተው፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር፣ ሰፊ መሬት ያላት ኢትዮጵያ ግን ይህንን ሥርዓት እስከ ዛሬ ባለማቋቋሟ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳጣች ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠና አቋቁማ ቢሆን ኖሮ ትልቅ ገበያ በመመሥረት ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከመላ ዓለም ጋር በሚኖራት የንግድ ግንኙነት ላይ የወሳኝት ሚና ይኖራት እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ይህ ባለመሆኑ ግን ማግኘት የሚገባትን እንድታጣና በንግድ ግንኙነቶች ላይ የወሳኝነት ሚና እንዳይኖራት አድርጓል ብለዋል፡፡

በታቃራኒው መሆን የነበረበትና ትክክለኛው አካሄድ በአገር ውስጥ በርከት ያሉ የንግድ ቀጣናዎችን በማቋቋም ዓለም አቀፍ ነጋዴዎች በእነዚህ የነፃ ንግድ ቀጣናዎች በመግባት በኢትዮጵያ ያለውን ትልቅ ገበያ ለመያዝ ውድድር ማድረግ ነበረባቸው ሲሉም ሐሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡

መንግሥት በሎጂስቲክስ ዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን፣ እንዲሁም ውጫዊ ተግዳሮቶችና ዕድሎችን በመለየት ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲዎች የመነጨ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ሲሆን፣ ሰነዱም ስድስት ዓበይት ስትራቴጂዎች፣ 22 ንዑሳን ስትራቴጂዎችና 98 ኢኒሼቲቮችን አካቶ በአሥር ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አፈፃፀም በዚህ ወቅት ካለበት 122ኛ ደረጃ በማሻሻል ወደ 40ኛ ደረጃ ከፍ ማድረግን ያለመ ስለመሆኑም የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡ 

በብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂና በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ ውስጥ ከተጠቀሱት ኢኒሼቲቮች አንዱ ‹‹ነፃ የንግድ ቀጣና ማቋቋም›› እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት የተጣለው ግብ በሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ውስጥ ከተካተተ ጀምሮ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ጥናት ሲከናወን መቆየቱ የሚገለጽ ሲሆን፣ የተደረገው ጥናት አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ በብሔራዊ የሎጂስቲክስ ካውንስል ልዩ የኢኮኖሚክ ቀጣናዎችን ማቋቋም እንደ አንድ የፖሊሲ ፕሮግራም፣ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ደግሞ እንደ ፓይለት ፕሮጀክት ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የፕሮጀክቱ መሳካት አገሪቱን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በመሻሻል የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ቅልጥፍናን የሚያመጣ፣ ለኢንዱስትሪና ከተሞች ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል መፈጠር፣ ለኑሮ ውድነት መቀነስና ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ስለመታመኑ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ያስረዳሉ፡፡ 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ማቲዎስ ኢንሳርሙ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ከዚህ ቀደም በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በነበረ የውይይት መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፣ ይህ ነፃ የንግድ ቀጣና የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውት የሚሠራበት መሆኑን አንስተው፣ ከዚያም ውስጥ ኢንዱስትሪ ፍሪ ዞን፣ ኤክስፖርት ፕሮሰሲንግ ዞን የሚሉትን ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም ላይ 5,400 የሚደርሱ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች እንዳሉ ተገልጾ፣ ለአብነትም በቻይና የሼንዜንና ሃይናን ኤክስፖርት ፕሮሰሲንግ ዞኖች የቻይና ሕግ የማይሠራባቸው ዞኖች ተብለው እንደሚወሰዱ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸውታል፡፡ 

የነፃ ንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ መፈጠር በትልቅ ዜናነቱ የሚያነሱት በርካቶች ሲሆኑ፣ ይህም የሚያመጣቸውን የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ከግምት በመውሰድ ነው፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣና በዋነኛነት በሦስት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት ጉዳይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የአምራች ዘርፉን የተመለከተ ሲሆን፣ ይህም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርት ወይም ከተመረተ በኋላ ኤክስፖርት የሚያደርገውን ነው፡፡ ሁለተኛው የአስመጪና ላኪ ድርጅቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ይሄ ደግሞ ጥሬ ዕቃና አላቂ ዕቃ አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ ዕቃዎችን በማምጣት በቀጣናው ውስጥ የሚያከማቹበት፣ የሚያቀናብሩበት እንዲሁም መልሰው ወደ ውጭ አገሮች የመላክ ሥራዎች የሚያከናወኑበት ነው፡፡ እንዲሁም ሒደቱን ለማሳለጥ ቀልጣፋ የሆነ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጥበትም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣናው የሚሰጠውን አገልግሎቶች የሚያቀላጥፉ የባንክ፣ የኢንሹራንስ፣ የደረቅ ጭነትና የምክር አገልግሎቶች በቅንጅት የሚሰጥበት ነው፡፡

በነፃ ቀጣናው የአገሪቱ የጉምሩክ ሥርዓትና አጠቃላይ ሕጎች ልማቱን ለማሳለጥ በሚያስችል ሁኔታ ላልተው የሚተገበሩበት መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፣ በዚህ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ የሚገቡ አምራቾች ከነፃ የንግድ ቀጠናው ሳይወጡ የምርት ግብአቶችን የሚያገኙበት ከመሆኑ ባሻገር፣ ከነፃ የንግድ ቀጠና ውጪ የሚያመርቱ ኩባንያዎች በግብዓትነት የሚጠቀሟቸውን ያላለቁ ምርቶች ከውጭ ሲያስገቡ እንዲከፍሉ የሚጠበቅባቸው ቀረጥና ታክስ በነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ ተግባራዊ የማይደረግ በመሆኑ የምርት ወጪ የሚቀነስ ነው። ይህም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ቀጣና እንዲገቡ ትልቅ ብርታት የሚሰጥ እንደሚሆን ይታሰባል። በመሆኑም ነፃ የንግድ ቀጣና መቋቋም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከዚያው ጎን ለጎንም የውጭ ምንዛሬ፣ የኤክስፖርት ዕድገት፣ የኤክስፖርት ምርት ስብጥር ከማሳደግ በሻገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨሰትመንትን በመሳብ ረገድ የሚጫወተው ሚና በትልቁ የሚነሳ መሆኑ ይብራራል፡፡

የመንግሥት ገቢ በማሳደግ ረገድም የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል የሚባለው የነፃ ንግድ ቀጣና እንቅስቃሴ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና የሠራተኞች ክህሎትን ለማሳደግ የሚጫወተው ሚና ግዙፍ ነው። በተጨማሪም የነፃ ንግድ ቀጣናው የሚመሠረትበት አካባቢን ወይም ቀጣናን በማልማትና በማሳደግ ረገድ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑም ይገለጻል፡፡

የባህር ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው፣ የንግድ ቀጣናው መመሥረት ለደርጅቱ ትልቅ ዕድል መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ከታክስ በፊት 78 ሚሊዮን ዶላር ታክስን ጨምሮ ደግሞ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት በመጨረሻው ምዕራፍ ከመገኘቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ የነፃ የንግድ ቀጣናዎች በመገንባታቸው በአገሮች መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት የሚሳለጥ መሆኑን፣ እንዲሁም አፍሪካ በተሰጣት የቀረጥ ነፃ መብት ዕድሎች ላይ ተጨማሪ ጥቅም እንዲገኝ የሚያስችል እንደሆነም አቶ ሮባ ይናገራሉ፡፡

የመጀመሪያው ነፃ የንግድ ቀጣና በድሬዳዋ እንዲመሠረት ለምን ተፈለገ?

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ አገር እንደመሆኗ መጠን የገቢ ዕቃዎችን በዋናነት የምታስገባው የጂቡቲ ወደብን በመጠቀም መሆኑ ይታወቃል። በተመሳሳይ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ዕቃዎችም ይህንኑ የጂቡቲ ወደብ በመጠቀም ወደ መዳረሻ ገበያዎች ይጓጓዛሉ። ድሬዳዋ ደግሞ ከጅቡቲ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከመሆኗ ባሻገር ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚያደርሱ ለጭነት ተሽከርካሪዎች ምቹ የሆነ መንገድና የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት መስመር የሚያልፍባት በመሆኗ ለሎጂስቲክስ አገልግሎት ምቹ አድርጓታል። 

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የኋላሸት ጀምበሬ (ኢንጂነር)፣ ስለ ነፃ የንግድ ቀጣና ምንነትና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ከዚህ ቀደም ባቀረቡት ማብራሪያ፣ ከጂቡቲ ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው የሚገቡት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕቃዎች የሚከትሙት በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል (ኢስተርን ዞን) በተለይም በድሬዳዋ ደግሞ 50 ከመቶ የሚሆኑት የሚራገፍበት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በድሬዳዋ ነፃ ንግድ መቋቋሙ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በአዋጭነት ጥናቱ አመላካች ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹ድሬዳዋ ውስጥ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ አለ፡፡ ድሬዳዋ ላይ የለማ፣ ከአራት ዓመት በፊት የተጠናቀቀና እንደ አገር በውጭ ምንዛሪ ዕዳ እየከፈልንበት ያለ፣ ነገር ግን አምራቾች ሊገቡበት ባለመቻላቸው ወጪውን እንኳን መጋራት ያልቻልነው፣ ለመንግሥት ብቻ ሸክም (በርደን) የሆነና ጥቅም ላይ ያልዋለ የኢንዱስትሪ ፓርክ አለ፤›› በማለት የተናገሩት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ የነፃ ንግድ ቀጣናውን በድሬዳዋ ለማቋቋም ሲወሰን እንደ መነሻ ከታዩት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይህ ተገንብቶ የተጠናቀቀ የኢንዱስትሪ ፓርክ በድሬደዋ ውስጥ መገኘቱ እንደሆነ አስረድተዋል።

ድሬዳዋ በተዘረጉ የባቡርና መንገድ መሠረተ ልማቶች፣ ኢንዱስትሪ ፓርክና የደረቅ ወደብ አማካይነት ነፃ የንግድ ቀጣናውን ዕውን ለማድረግ አመቺ መሆኗ ሌላው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

በድሬዳዋ በሚቋቋመው ነፃ የንግድ ቀጣና ለመጋዘንነትና ለኤክስፖርት ማቀነባበሪያነት የሚያገለግሉ ሼዶች በዚህ ወቅት ዝግጁ መሆናቸው፣ በቀጣናው ውስጥ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ከሞላ ጎደል በመጠናቀቅ ላይ መሆኑና ለንግድ ቀጣናው መሳለጥ አስፈላጊ የሆኑ እንደ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ መጋቢ መንገዶች፣ የውኃ አቅርቦትና ተያያዥ አገልግሎቶች የተሟሉ መሆናቸው ድሬዳዋን ተመራጭ አድርጓታል። በመሆኑም የመጀመሪያ የሚሆነው የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

በድሬዳዋ በሚመሠረተው ነፃ የንግድ ቀጣና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ የተለያዩ አልሚዎች ገብተው በንግድ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢምፖርትና ኤክስፖርት የሥራ መስኮች ሊሰማሩ እንደሚችሉ፣ ለዚህም በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝና በቀናት ውስጥ ምሥረታው ዕውን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የስትራቴጂ አማካሪ የሆኑት አቶ ኪያ ተካልኝ እንዳስታወቁት፣ የነፃ ቀጣናው የዝግጅት ሥራዎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና አካላት በኩል ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ወራት በነፃ ቀጣናው የሚተገበሩ የሕግ ማዕቀፎችን ጨምሮ ምሥረታውን ለመጀመር የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝግጅት በኮርፖሬሽኑ በኩል ተጠናቆ አገልግሎት መጀመር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ኮርፖሬሽኑ ከሰሞኑ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አስታውቋል፡፡

በዓለም ላይ ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን (ነፃ የንግድ ቀጣናዎች) መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ኪያ፣ በተለያዩ የአደጉ በሚባሉ አገሮች ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና የተጫወተው የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ መመሥረቱ የወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን ለማሳደግ፣ የዕውቀት ሽግግርን ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ይናገራሉ፡፡

ይህ የነፃ ንግድ ቀጣና አሠራር በአፍሪካ ውስጥ  በጂቡቲ፣ በሶማሌላንድ፣ ኬንያ ውስጥ ውጤታማነቱ በተሞክሮነት የተወሰደ መሆኑን ያስረዱት የስትራቴጂ አማካሪው፣ ከዚያም አልፎ ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ የቱርክ አገር ተሞክሮ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

በጥናት የሚመለስ ቢሆንም የተለያዩ ዝርዝር መሥፈርቶችን መሠረት በማድረግ ከመገኛ ቦታቸው፣ ለገበያ ካላቸው ቅርበት አንፃር ሞጆ፣ አዳማ፣ ሰመራ ዓይነቶቹ አካባቢዎች በቀጣይ ለነፃ የንግድ ቀጣና ዞንነት ታሳቢ ከተደረጉት ውስጥ እንደሚገኙበት አቶ ኪያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች