Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ117.2 ቢሊዮን ብር በላይ ቢሆንም የፋይናንስ የተደረገው (ለብድር የዋለው) 35.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ቁጥር አራት የደረሰና አሥራ አንድ ባንኮች ደግሞ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ እነዚህ አሥራ አንዱ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ባንኮችና ወደ ሥራ የገቡት ሁለቱ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት (ዘምዘምና ሒጅራ) ባንኮች በጥቅሉ ከ117.2 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ሰብስበዋል፡፡ 

ይሁንና እነዚህ ባንኮች ካሰባሰቡት ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን ፋይናንስ አላደረጉትም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያለው እንደገሉጸትም እነዚህ ባንኮች ባሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ልክ ፋይናንስ አላደረጉም፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን 117.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ሳለ ለብድር ወይም ለፋይናንስ የተደረገው ግን 35.5 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ የተሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ፋይናንስ ማድረጉ ላይ (ለብድር ማዋል ላይ) የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሳያመለክት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ገበያ የገቡት ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች እስካሁን 86 ቅርንጫፎችን መክፈታቸውን ይኸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡ 

አሥራ አንዱና ሁለቱ ባንኮች በጠቅላላው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የከፈቷቸው አካውንቶች ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ የደረሰ መሆኑንም ከዳይሬክተሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

የወለድ ነፃ የባንክ አልግሎት በመሥራት ደረጃ እየሰጡ ካሉ አሥራ አንዱ ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን ተቀማጭ ገንዘብ ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ69.6 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይህም ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ ባንኮችም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከተቋቋሙት ባንኮች በእጅጉ ከፍተኛ ብልጫ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማሰባሰቡን ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ ፋይናንስ ከማድረግ (ብድር ከመስጠት) አንፃር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያለው መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ማባሰብ ከቻለው 69.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ፋይናንስ ያደረገው 9.3 ቢሊዮን ብር ብቻ በመሆኑ አጠቃላይ ለፋይናንስ የዋለውን የገንዘብ መጠን አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ 

የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማት መካከል የሰበሰበውን ተቀማጭ ገንዘብ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ጠንካራ አፈጻጸም በማሳየት በዘርፉ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ኦሮሚያ ኅብረት ስራ ባንክ ነው። 

ሪፖርተር የተመለከተው የባንኩ መረጃ እንደሚያመለክተው ባንኩ እስከ 2014 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሰበሰበው 16 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 13.5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን መልሶ ለብድር እንዲውል በማድረግ በኢንዱስትሪው የቀዳሚነት ስፍራን ይዟል። ሌሎቹ የፋንናንስ ተቋማት ከሚሰጡት የወለድ ነፃ አገልግሎት ማሰባሰብ የቻሉትን ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ጥቅም ላይ ማዋል ያልቻሉበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም አገልግሎቱ አዲስ መሆኑና ባንኮቹም ከዚህ አገልግሎት እንዴት መጠቀም እንደሚቻል በስፋት አለማስተዋወቃቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል።

እንደ ብሔራዊ ባንክ መረጃ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ አሁን ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ዘምዘምና ሒጅራ ባንኮች ሌላ ራሚስ ባንክም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በተመሳሳይ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው አራተኛው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ሸበሌ ባንክ ነው፡፡ ሸበሌ ባንክ ከሌሎች ከወለድ ነፃ ባንኮች በተለየ መንገድ ተቋቁሞ አገልግሎት ለመጀመር እየተዘጋጀ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ሸበሌ ባንክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ሲያገለግል የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በባንክ ደረጃ ከፍ ብሎ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ያቀረበው ጥያቄ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀበይነት አግኝቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት እየተሰናዳ ነው፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገር ውስጥ ያሉ ንግድ ባንኮች ከሚተዳደሩበት የባንክ ሥራ አዋጅ ጎን ለጎን ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከተ አዲስ ሕግ እንደሚወጣ ተገለጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ከወለድ ነፃ የባንክና የኢንሹራንስ ወይም (ታካፉል) አገልግሎቶችን ከመደበኛው የፋይናንስ አገልግሎት ጎን ለጎን እንዲያቀርቡ ያስቻለ ሕግ እንደወጣው ሁሉ፣ የፋይናንስ ዘርፉ አካል የሆኑት እንደ ካፒታል ማርኬት፣ ቦንድ ማርኬትና የመሳሰሉ የፋይናንስ ዘርፎች ከወለድ ነፃ በሆነ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ሕግ በብሔራዊ ባንክ በኩል እንደሚወጣ አቶ ፍሬዘር ገልጸዋል፡፡ 

ለዘመናት የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ወለድን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ሲሰጥ  ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የዘርፉ አገልግሎት እየተቀየረ መምጣቱንና ከዚህም በኋላ የፋይናንስ ዘርፉ ሁለቱንም አገልግሎቶች (ዱዋል ሲስተም) እያጣመረ የሚሄድበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ጠቁመዋል፡፡ 

በመሆኑም የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከተለመደው አገልግሎት ጎን ለጎን የወለድ ነፃ አገልግሎትንም በእኩል የሚሰጥበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።

መጀመርያ ሙሉ በሙሉ የተለመደውን የፋይናንስ አገልግሎት በማቅረብ ላይ የነበሩት የፋይናንስ ተቋማት በሒደት ከተለመደው አገልግሎት ጎን ለጎን ተጨማሪ አገልግሎቶችን ወደ ማቅረብ ሽግግር እንዳሳዩት ሁሉ፣ እያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ከተለመደው የፋይናንስ አገልግሎት እኩል ከወለድ ነፃ አገልግሎቶችን ወደ ማቅረብ ሽግግር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ የባንክ ዘርፍ አገልግሎቶችን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነና በፋይናንስ ዘርፉ የሚገኙ ሌሎች አገልግሎቶችም ከተለመደው በተጨማሪ ሌሎች አግልግሎቶችን መስጠታቸው የማይቀር በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ይህንን ያገናዘበ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች