Tuesday, October 3, 2023

የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት በተመለከተ ‹‹ለሕዝብ ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ለመፍታት እየሠራሁ ነው፤›› ሲል ይደመጣል፡፡ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው ደቡብ ክልልን በክላስተር ክልል አስተዳደሮች የመክፈል ዕቅድ ግን ተቃውሞ እየገጠመው ነው የሚገኘው፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ሰፊ መግለጫ፣ በደቡብ ክልል ከክልል አደረጃጀት ጋር የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረት ተመልክቶት ነበር፡፡ ከብሔር ብሔረሰቦች የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በተመለከተ፣ ጥያቄዎቹን ለመፍታት አመቺ ሁኔታ መፈጠሩን የምክር ቤቱ መግለጫ ያትታል፡፡ በኢመደበኛ አደረጃጀት ተደራጅተው ጫና የሚያሳድሩ ኃይሎች ወደ መደበኛ አደረጃጀት ገብተዋል ሲልም ያክላል፡፡ ጥያቄዎቹን በሕገወጥ መንገድ ለመፍታት የሚፈልጉትን ወገኖች አስቀድሞ በመለየት ሕጋዊ ዕርምጃ መንግሥት እየወሰደ መሆኑን በማከል፣ ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የምክር ቤቱ መግለጫ ያተተው፡፡

መንግሥት ይህን ይበል እንጂ በደቡብ ክልል በተለይ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ባነሱ ዞኖች ውስጥ ከሰሞኑ ውጥረቱ ማየሉ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ በወላይታ ዞን፣ በጎፋ ዞንና በጉራጌ ዞን አካባቢዎች የፖለቲካ ውጥረት ማየሉን የአካባቢዎቹ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ክልል ለቆዩ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች በመንግሥት መፍትሔ ተብሎ የቀረበው በክላስተር ክልሉን ሸንሽኖ የማደራጀት ፍላጎት በብዙ አካባቢዎች ቁጣና ተቃውሞ መቀስቀሱ ነው፡፡

በጉራጌ ዞን በምዕራብ ቸሀ፣ በጉንችሬ፣ በወልቂጤ ከተማና በሌሎችም ከተሞችና አካባቢዎች እንቅስቃሴና ሥራ የማቆም አድማ ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. መካሄድ መጀመሩ ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ በብዙ የአገሪቱ ክፍሎች ተሠራጭቶ የሚኖረውና የንግዱ ዘርፍ ዋና አንቀሳቃሽ በመሆን የሚታወቀው የጉራጌ ማኅበረሰብ፣ በያለበት የሥራ ማቆም አድማ ቢያደርግ ከዞኑ ውጪ ያለፈ ተፅዕኖ እንዳለውም እየተሠጋ ነው፡፡

መንግሥት ክልል እንሁን ጥያቄ ባነሱ ዞኖች የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የክልልም ሆነ ሌሎች የአስተዳደር አደረጃጀቶች በቀረቡባቸው አካባቢዎች ብዙ ጊዜ ደም መፋሰስና ግጭት መፈጠሩ የተለመደ እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በወላይታ ዞን የተፈጠረው ደም መፋሰስ ዘንድሮም እንዳይደገም የሚሠጉ በርካቶች ናቸው፡፡ የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ እየገፋ ከሄደና ከሰሞኑ እየታዩ ያሉ ውጥረቶች ተባብሰው ከፈነዱ፣ የካች አምናው ላለመደገሙ አንዳችም ዋስትና አይኖርም ሲሉ ብዙዎች ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡

በጎፋ ዞንም ተመሳሳይ ውጥረትና ሥጋት መስፈኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡ መንግሥት በየእርከኑ ያሉ የዞን አመራሮችን ጨምሮ ሰዎችን ማሰሩንና ማሳደዱን እንደቀጠለ የአካባቢው ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ቁጥርና ክትትል በዞኑ መጨመሩንም ይናገራሉ፡፡ ይህ ውጥረት እየከረረ ሲሄድ ሊፈጠር የሚችለው ችግር ያሠጋናልም ይላሉ፡፡

‹‹በክላስተር ለመደራጀት ከሆነ ጥያቄያችን መጀመርያውኑ ከሌሎች ተነጥለን ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር የሚል ጥያቄ ለምን አቀረብን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ ለጎፋ ብሔረሰብ የክልልነት ጥያቄ እንደሚታገሉ የሚናገሩት አቶ ዓይናለም ታደሰ አስተያየታቸውን ሲጀምሩ፡፡

የጎፋ ሕዝብ ጥያቄ ለረዥም ዘመን ሲታፈን መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ዓይናለም፣ የደቡብ ክልል በመንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ የተመሠረተና የብዙ ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ታፍኖ የቆየበት ክልል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት ባለፈው ሳምንት በክላስተር ተደራጁ የሚል ውሳኔ ይዞ መጥቶ አስወሰነ የሚሉት አቶ ዓይናለም፣ ‹‹የዞኑ የብሔረሰብ ምክር ቤት በ2012 ዓ.ም. ተሰብስቦ ራሱን ችሎ በክልል የመደራጀት ጥያቄን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አቅርቦ ሳለ የክልል ምክር ቤቱ ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ጥያቄያችን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምርቶ ምላሽ እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ መንግሥት በክላስተር ተደራጁ የሚል ሐሳብ ይዞ መጥቶ ልጫን ማለቱ ሕዝቡን አሳዝኖታል፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ጥናት ተብሎ በክላስተር ለመደራጀት በመንግሥት እየቀረበ ያለው ማሳመኛ ተቀባይነት የሌለው ነው፤›› የሚሉት አቶ ዓይናለም፣ መንግሥት የላካቸው ሰዎች እዚህ መጥተው የሚፈልጉትን ሰው ብቻ አናግረው ነው የተመለሱት ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ አገሪቱ በአስቸጋሪ ቀውስ ውስጥ ገብታለች ተብሎ ኅብረተሰቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄውን ለጊዜው በያዘበት ወቅት፣ መንግሥት በአቋራጭ በክላስተር ተደራጁ የሚል ዕቅድ አምጥቶ ላስፈጽም ማለቱ አደገኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በጥናት አይፈታም፡፡ በሕዝብ ውሳኔ ነው የሚፈታው፡፡ ወደ እዚያ ከመገባቱ በፊት ግን ጥናቱ ምን ያህል ሀቀኛ ነው ወይ ስለሚለው መጠየቅ አለብን፡፡ ጥናቱ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ ገለልተኛ አጥኚዎች ተወዳድረው የተደረገ አይደለም፡፡ ጥናቱ መንግሥት ያፈለቀው ሐሳብ፣ መንግሥት የመራውና መንግሥት ያስፈጸመው ነው፡፡ የወሰዱት ናሙና ወይ የጠየቁት ሰው ማን ነው? የዞን ምክር ቤቶች ወስነዋል? ሕዝቡ ደቡባዊ ማንነትን ይፈልጋል? የሚሉት ምን ላይ ተመሥርተውስ ነው?›› በማለት አቶ ዓይናለም የክላስተሩን ሐሳብ ይሞግታሉ፡፡

በዚህ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ላይ ፌዴራል መንግሥት ጣልቃ የሚገባበት አንዳችም ሕገ መንግሥታዊም ሆነ የሕግ መሠረት እንደሌለ አቶ ዓይናለም ያክላሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥናት ቡድን አያዋቅርም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄን ተቀብሎ የማስፈጸም ግዴታ አለበት፡፡ እኛ አገር ሕገ መንግሥት ቢኖርም ሕገ መንግሥታዊነት ባለመኖሩ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄያችን ታፍኗል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ሕዝቦች ራሳቸውን በማስተዳደራቸውና በማደራጀታቸው መጨቆን ወይም ማፈን የሚፈልጉ ኃይሎች ምቾት ስለሚያጡ ነው ጥያቄያችን እየታፈነ የሚገኘው የሚል የግል ሐሳብ እንዳላቸውም አቶ ዓይናለም ይናገራሉ፡፡

 የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ወብን)  ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ በበኩላቸው፣ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ለደቡብ ክልል ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀረበ መቆየቱን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹እኛ የምንጠብቀው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ታች ዞኑ ጋር ወርዶ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ነው፡፡ ባለፈ ጉዳይና በማይመለከታቸው ነገር ክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በክላስተር ካልተደራጃችሁ ሊሉን አይችሉም፤›› ብለዋል፡፡

ወላይታን በክላስተር ካልተደራጀ የሚለው እንቅስቃሴ ‹‹አንደኛ የሕዝብ ጥያቄ ባለመሆኑ፣ ሁለተኛ ሕገ መንግሥታዊነትን የተከተለ ባለመሆኑ፣ ሦስተኛ የሕዝቡ ፍላጎት ባለመሆኑና ለአሠራርም የማይመች በመሆኑ በነዚህ ሁሉ አጥብቀን እንቃመዋለን፤›› በማለት ፖለቲከኛው አቶ አማኑኤል ያክላሉ፡፡

ወብን ፍፁም ሰላማዊ የትግል ስትራቴጂን ተከትሎ የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ እንደሚታገል ያመለከቱት አቶ አማኑኤል፣ መንግሥት በክላስተር ካልተደራጃችሁ ብሎ ከባድ ጫና እያሳደረ መሆኑንና ይህም ፖለቲካዊ ውጥረት መፍጠሩን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ነገር እስራት፣ ሞት፣ ወይም መስዋዕትነትን ፈርቶ ጥያቄውን ይዞ ወደ ቤት የሚመለስ ሕዝብ ግን የለም፡፡ ወላይታ እኮ ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ሠልፍ የወጣ እውነትንና ፍትሕን በሰላም ሲጠይቅ የኖረ ሕዝብ ነው፤›› ያሉት አቶ አማኑኤል፣ በክላስተር ካልተደራጃችሁ በሚል አላስፈላጊ ጫና ሕዝቡ ላይ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢሕአዴግ አስተዳደር ዘመን በሽብር ክስ ለረዥም ዓመታት ታስሮ መቆየቱን የሚያስታውሰውና ‹‹በአገሪቱ የመጣው ለውጥ ነው ከእስር ያስታፈኝ፤›› የሚለው አቶ ሚስባህ ከድር፣ ለውጡ የሌሎች ሕዝቦችን መልሶ የጉራጌ ሕዝብን ጥያቄ ወደ ጎን ማለቱን ይናገራል፡፡ ‹‹ከሌሎች ጋር የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄን ማፎካከር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ እየተባለ የሐረሪ ክልል ሲፈጠር ዓይተናል፡፡ የሲዳማ ጥያቄ በቅርቡ ሲመለስ ዓይተናል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ምዕራብ ክልልም ተፈጥሯል፡፡ የጉራጌ ክልል የመሆን ጥያቄ ለምን ቸል ይባላል?›› ሲል ይጠይቃል፡፡

ከእስር ከተፈታ በኋላ ‹ፍቅር ያሸንፋል› የሚል ማኅበር በማቋቋም በሃይማኖቶችና በሕዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር በጎ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱንም ይናገራል፡፡ የጥምቀተ ባህርን፣ የሶላት መስገጃዎችንና የበዓላት ማክበሪያዎችን የማፅዳት ሥራ ማኅበራችን ይሠራል ሲል የሚናገረው አቶ ሚስባህ፣ የጉራጌ ሕዝብን ክልል የመሆን ጥያቄ በማቅረብ የማኅበራዊ አንቂነት ሥራ በግሉ እንደሚሠራም ይገልጻል፡፡

‹‹በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳ ዳሶሬ ቀበሌ አካባቢ የኢንቨስትመንት ቦታ ነበረኝ፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስጨረስ ስፈልግ ግን ከጉራጌ እየተነሳሁ ሐዋሳ ድረስ መመላለስ ነበረብኝ፡፡ ጉራጌ ራሱን በራሱ ማስተዳደሩና ክልል መሆኑ ለልማት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ሐዋሳን ሕዝቡ ከተማዬ ብሎ ሲያለማ ቆይቶ በመጨረሻ ግን የአንተ አይደለም ውጣ ነው የተባለው፡፡ አሁን ደግሞ በክላስተር ተደራጅተህ ወደ ሆሳዕና ተመላለስ እያሉት ነው፤›› ሲል አቶ ሚስባህ የክልልነት ጥያቄው የአስተዳደር አመቺነትና የኢኮኖሚ ጥያቄንም መያዙን ይናገራል፡፡

‹‹ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል እምቢ፣ ሕገ መንግሥቱ ይከበርልን እምቢ የሚል ከሁለት አንዱን የመምረጥ ነው የመንግሥት ችግር፤›› ሲልም ያክላል፡፡ ጉራጌ በመላ አገሪቱ ተሠራጭቶ በላቡና በጥረቱ ሀብትና ንብረት በማፍራት ብዙ አካባቢዎችን ሲያለማ የኖረ ሕዝብ መሆኑን ያወሳው አቶ ሚስባህ፣ የራሱ ክልል ቢኖረው ራሱን ችሎ መልማትና መበልፀግ እንደሚያቅተው ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ፖለቲከኞች ሕዝቡን አንዴ ደቡብ ሌላ ጊዜ ክላስተር ሁን የሚሉት ነገር ሕዝብን  መናቅ ነው፤›› በማለትም አቶ ሚስባህ የሰሞኑን ሁኔታ ያስረዳል፡፡

የቀድሞው እየተባለ ለመጠራት ጥቂት የቀረ በሚመስለው ደቡብ ክልል የአስተዳደር ጥያቄ በርካታ ገጽታና መልክ ያለው ነው፡፡ ዞን የነበረው ክልልነት ሲጠይቅ ወረዳ የነበረው ደግሞ ዞን ካልሆንኩ የሚልበት ሁኔታ መፈጠሩ ይነገራል፡፡ በተለይ ከለውጡ ወዲህ አብጦና ጎልቶ መታየት የጀመረው በደቡብ ክልል የተስፋፋው የአስተዳደር ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ያገኙትም ሆነ፣ ገና በሒደት ላይ የሚገኙት በአንድ ወይ በሌላ መንገድ የፖለቲካ ቀውስ ምንጮች እየሆኑ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የማንነት ጥያቄ መልስ እያገኘ የመጣው ከማንኛውም ጊዜ በላይ በእሳቸው አስተዳደር ዘመን መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እነዚህ ቁጥራቸው የበዛ የማንነት ጥያቄዎች የፖለቲካ ቁርሾ ወልደው ግጭትና ደም መፋሰስ ከማስከተላቸው በፊት መፈታት አለመቻላቸው ግን ጎልቶ ይነሳል፡፡ በጥናት ተደግፎ የቀረበ ነው የተባለውና ከሰሞኑ ወደ መሬት ካልወረደ በሚል የተጀመረው ከሲዳማና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውጪ ያለውን የደቡብ ክልል ዞን በክላስተር ክልሎች የመክፈሉ ጥረት፣ ባለው ላይ ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሮ የባሰ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳይፈጥር የሚሠጉ ብዙዎች ናቸው፡፡

የጉራጌ ዞን እዣ ወረዳን በመከወል የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ የሕዝቡ ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ሲገፋ መቆየቱን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የጉራጌ ሕዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ሳይፈልግ ቀርቶ አይደለም፡፡ የፌዴራሊዝሙ ቅርፅ ይቀየራል ታገስ፣ ጥያቄህ ይመለሳል፣ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል ችግራችሁ ይቀላል እየተባለ ነው የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄ የከረመው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በጨቦና ጉራጌ አውራጃ ሥር በሸዋ ክፍለ አገር ውስጥ ሲተዳደር የቆየው የጉራጌ ሕዝብ፣ በሽግግሩ ጊዜ በሐይቆችና ቡታጅራ ሥር ዝዋይና ቡታጅራን ማዕከል ባደረገ ክልል መዋቀሩን አቶ ታረቀኝ ያስረዳሉ፡፡ በዚያው በሽግግሩ ጊዜ በክልል ሰባት ሥር ተደራጅቶ ሆሳዕናን ማዕከል በማድረግ እንዲተዳደር የተሞከረ ቢሆንም፣ ይህ አደረጃጀት መፍረሱን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ በደቡብ ክልል ሲተዳደር ቆይቶ ኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ፀድቆ ጉራጌ በክልል ራሱን ችሎ ይተዳደር የሚል ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረቡንም ያክላሉ፡፡

‹‹በዞኑ ባሉ ሦስቱም የብሔር ምክር ቤቶች በማረቆ፣ በቀቤናና በጉራጌ ጥያቄው በሙሉ ድምፅ የፀደቀና የዞኑ ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ያለው ነው፡፡ አሁን ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ መንግሥት በኃይል ለመደፍጠጥ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ዕርምጃ ጀምሯል፡፡ የጉራጌ ሕዝብ ክልልነት ይገባኛል በማለቱ እየታሰረና ማስፈራሪያ እየተካሄደበት ነው፡፡ የጉራጌ ሽማግሌዎች ነገሩን ለማርገብ ቢጥሩም እነሱንም አታስፈልጉም ብለው በኃይል በትነዋቸዋል፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ታረቀኝ፣ መከላከያና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በጉራጌ ሕዝብ ላይ ጫና እያሳደሩ ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ታረቀኝ ይህን ለሪፖርተር በተናገሩ ማግሥት በጉራጌ ዞን ከተሞችና ገጠሮች በቤት የመቀመጥ አድማ እየተካሄደ መሆኑን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በርካታ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የንብረት ውድመት ያስከተሉ ግጭቶች መቀስቀሳቸውም እየተሰማ ነው፡፡

‹‹ጉራጌ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተሰባስቦና ተጎራብቶ መኖርና መተዳደርን አይጠላም፡፡ የጉራጌ የጥንት ታሪክም ከሌሎች ጋር በጋራ መኖሩን ያረጋግጣል፡፡ አሁን  በክላስተር እንዲደራጁ የተባሉት ቋንቋቸው ሊቀራረብ የማይችል የሴምና የኩሽ ሕዝቦችን ነው፡፡ ጉራጌ ከዚህ በፊት ከሌሎች ጋር በጋራ በመደራጀት የተጠቀምኩት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ጠቀሜታ የለም ብሎ ያስባል፡፡ ለአስተዳደርም ቢሆን ለመልማት ወልቂጤ ነው የሚቀርበኝ እያለ ነው፤›› ሲሉ አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል፡፡

ከሰሞኑ የጉራጌ ዞን ጥያቄ አየል ቢልም በክልል የመደራጀት ጥያቄ የፈጠረው ሥጋት በወላይታም ሆነ በጎፋ ዞኖች ተወጥሮ ይገኛል፡፡ በሐዋሳና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የሠሩት የሥነ ማኅበረሰብ ልማት ፖሊሲ ጥናት ምሁሩ መድኅን ማርጮ (ዶ/ር)፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ ማኅበረሰቦች ያነሱት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹ክላስተር አደረጃጀትን ሕገ መንግሥቱ አያውቀውም፡፡ በአንቀጽ 46 ላይ ሕዝቦች ወይም ብሔረሰቦች ማንነትን፣ ቋንቋንና የሕዝብ አሰፋፈርን መሠረት በማድረግ የራሳቸውን የክልል አደረጃጀት ያቋቁማሉ ተብሎ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ስለ ክልል ማቋቋም ሒደቱ በአንቀጽ 47 እና 48 ላይ ሰፍሯል፡፡ የወላይታን ክልል የመሆን ጥያቄ ካየን የራሱን መብት የማስከበር ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ይከበር የሚል ነው ጥያቄው፤›› በማለት መድኅን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የወላይታ ማኅበረሰብ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሳይመለስ ሕዝቡ ላይ ግፍና ግድያ እንደተፈጸመበት ያስረዱት መድኅን (ዶ/ር)፣ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በዞኑ ጥያቄ አነሳችሁ በተባሉ ዜጎች ላይ ግፍ መፈጸሙን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹የደቡብ ክልል የበጀት ድልድል የወረዳ ብዛትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የክልሉ ገቢ አሰባሰብም ቢሆን ልክ እንደ በጀት ድልድሉ ሁሉ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት መድኅን (ዶ/ር)፣ ወላይታ ለአስተዳደር አመቺነት ብቻ ሳይሆን ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሲል ለብቻው በክልል መደራጀትን እንደመረጠ ይናገራሉ፡፡

መንግሥት (የብልፅግና ተመራጮች) በምርጫ ወቅት የወላይታ ሕዝብን የክልልነት ጥያቄ እንመልሳለን የሚል ቃል ገብተው የሕዝቡን ድምፅ መሰብሰባቸውን የሚያስታውሱት መድኅን (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ጥያቄው ውጥረት ተባብሶ ቀውስ ከመፍጠሩ በፊት ችግሩ መፈታት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -