- እጅግ ውብ ዕድሳት ያደረጋችሁት! በእውነቱ በጣም ድንቅ ነው፡፡
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- በጣም ድንቅ ነው። ዕድሳቱን ያከናወነው ድርጅት ጥሩ ልምድ ያለው ይመስላል?
- ተቋራጩ ማን እንደሆነ አልነገርኩዎትም እንዴ?
- የትኛው ተቋራጭ ነው?
- የእርስዎን ቢሮ ዕድሳት ያከናወነው ድርጅት ነው።
- ኦ… እሱማ ልምድ አካብቷል።
- በትክክል። ከእኛ በተጨማሪ የሌሎች የመንግሥት ተቋማትን ቢሮዎችና ሕንፃዎች ዕድሳት በመሥራት ላይ ነው።
- የቀለም ምርጫችሁ ድንቅ ነው፡፡
- እርስዎ የሚወዷቸውን ቀለሞች ብቻ ነው የተጠቀምነው።
- ምን ያህል ጊዜ ፈጀባችሁ?
- የምረቃ ዝግጅቱን ጨምሮ አሥር ወራት ብቻ ነው የወሰደብን።
- አሥር ወራት ብቻ?
- የምረቃ ሥርዓቱ እንደሚዘገይ ስለነገርናቸው እንጂ ቀድሞ ማለቅ ይችል ነበር።
- ለምን አዘገያችሁት?
- እርስዎ ወደ ሥራ እስኪመለሱ ብለን ነው።
- ኦ… ጥሩ አደረጋችሁ። ይህንን የመሰለ ሥራ ባላይ ይቆጨኝ ነበር።
- ከእርስዎ ቢሮ ቀጥሎ ያለው ክፍል ለምን አገልግሎት የሚውል ነው?
- ጥግ ላይ ያለው ትልቁ የስብሰባ አዳራሽ ነው።
- ቀጥሎ ያለውስ?
- እሱ ደግሞ መካከለኛ አመራሮች የሚወያዩበት አነስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ነው።
- በጣም ጥሩ ነው። ቀጥሎ ያለውስ?
- እሱ ከፍተኛ አመራሩ የሚሰበሰብበት ክፍል ነው።
- ጥሩ አድርጋችኋል። ይህኛውስ?
- እሱ ደግሞ እኔን ለማግኘት የሚመጡ የውጭ እንግዶች ካሉ ከነሱ ጋር የምሰበሰብበት ይሆናል።
- ቀጥሎ ያለውስ?
- እሱ ደግሞ የድርጅቱ ኃላፊ ሲደክመው እረፍት የማደርግበት ክፍል ነው።
- መኝታ አለው?
- ክቡር ሚኒስትር ያው እንደሚያውቁት የእኛ ሥራ አድካሚ ነው።
- አውቃለሁ… አውቃለሁ!
- በዚህ ምክንያት መኝታ እንዲኖረው አድርገናል።
- ተገቢ ነው!
- አይደል?
- አዎ። ስብሰባ አድካሚ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ግምገማ ለማድረግና በቀጣይ የሚፈጸሙ ተግባራትን ለመወሰን ከማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ጋር እየመከሩ ነው]
- ዛሬ በቀረበው ሪፖርት ለመመልከት እንደቻልነው ኢኮኖሚው በጥሩ ሁኔታ ላይ ቢሆንም እነዚህን ውጤቶች አጠናክሮ ለመቀጠል ከፍተኛ የበጀት እጥረት ገጥሞናልና ይህንን ችግር ለማለፍ ምን ብናደርግ ይሻላል?
- ክቡር ሚኒስትር ዕድሉን ስለሰጡኝ አመሠግናለሁ። ባለፈው ስብሰባችን እንደገለጽኩት የገጠመን የበጀት እጥረት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ፈተና ነው።
- መፍትሔው ላይ ብታተኩር? ምን መደረግ አለበት?
- ክቡር ሚኒስትር ባለፈው ያቀረብኩት ሐሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ ዋጋ ለመጨመር ጥናት ተጀምሯል። ከቫት ነፃ የነበሩ አገልግሎቶችንም ወደ ቫት ሥርዓት ለማስገባት የሕግ ማሻሻያ ዝግጅት ተጀምሯል። ነገር ግን በቂ አይደለም።
- ለምን መፍትሔውን አታቀርብም?
- ወደ እሱ እየመጣሁ ነው።
- እሺ ቀጥል…
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር። በእኔ እምነት አሁንም ተጨማሪ ግብር ካልተጣለ የመንግሥት ገቢ ሊያድግ አይችልም። ተጨማሪ ግብር ወይም ቀረጥ መጣል አለብን።
- አንዴ ፀጥታ…. እየተደማመጥን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህንን የመፍትሔ ሐሳብ እቃወማለሁ።
- ምክንያት?
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ መሆኑን አምርሮ እየገለጸ ባለበት ወቅት ተጨማሪ ቀረጥ መጣል ለሕዝብ እጨነቃለሁ ከሚል መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ቀደም ሲል በቀረበው ሪፖርት ላይ እኮ ይህ ችግር እየተቀረፈ መሆኑ ተገልጿል፡፡
- የቱ ችግር?
- የኑሮ ውድነት እያስከተለ ያለው የዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለት ወራት መቀነስ እንዳሳየ ተገልጿል።
- ተቃውሞ አለኝ ክቡር ሚኒስትር…?
- እኔ ሐሳቤን አላጠናቀቅኩም ክቡር ሚኒስትር…
- የቀረበውን ተቃውሞ እናዳምጥና ዕድል እሰጥሃለሁ።
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር በቀረበው ሪፖርት እየቀነሰ ነው የተባለው የዋጋ ግሽበቱ አይደለም።
- ታዲያ ምንድነው ቀነሰ የተባለው?
- የዋጋ ግሸበቱ የሚያድግበት መጠን ቀነስ እንጂ አሁንም የዋጋ ግሽበቱ እንደቀጠለ ነው።
- ታዲያ ምን መደረግ አለበት ነው የምትለው?
- ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጊዜ ሰጥተን ብንወያይ?
- የገጠመን ችግር ግን ጊዜ የሚሰጥ አይደለም?
- ክቡር ሚኒስትር በደንብ ሳንገመግም በጥድፊያ ግብር የሚጣል ከሆነ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ሊያስከትል ይችላል።
- ክቡር ሚኒስትር ተቃውሞ ይገጥመናል የሚለው ሥጋት ትክክል ቢሆን እንኳን ለእሱ መፍትሔ ማስቀመጥ እንችላለን።
- እንዴት ያለ መፍትሔ?
- የምንጥለውን ቀረጥ በዘዴ ወይም በሥልት መጣል እንችላለን።
- እንዴት ማለት?
- ለምሳሌ ለሚጣለው ቀረጥ ልማታዊ ስያሜ መሰጠት እንችላለን።
- ልማታዊ ስያሜ?
- አዎ። በዚህ መንገድ ከተጣለ ሳይታወቅና ጉዳት ሳያመጣ ለመንግሥት ጠቃሚ ገቢ ያስገኛል።
- ልማታዊ ስያሜ መስጠት የሚለው ጥሩ የመፍትሔ ሐሳብ ይመስለኛል። በዚህ ላይ ተቃውሞ አለ?
- በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩነት ቢኖረኝም በኮሚቴው ተቀባይነት እስካገኘ ድረስ ቀረጡ ልማታዊ ስያሜ ተሰጥቶት ቢጣል ችግር የለብኝም።
- በጣም ጥሩ። ስለዚህ አዲስ የሚጣለው ቀረጥ ስያሜ ምን ይሁን ? ምን ብንለው ይሻላል?
- የማኅበራዊ አገልግሎት ቀረጥ!