- ሦስተኛ ዙር ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጀመረ፡፡ ሦስተኛው ዙር የግድቡ ውኃ ሙሌት በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
የሦስተኛው ዙር ሙሌት መጠናቀቂያ ማብሰሪያ ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ተካሂዷል፡፡
የህዳሴው ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ሁለተኛው ተርባይን ዛሬ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደጀመረ ተበስሯል፡፡ ሥራ የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡ የመጀመርያው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው ከስድስት ወራት በፊት የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በዛሬው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የግድቡ የመሀለኛው ክፍል 600 ሜትር፣ የግራና የቀኙ ክፍል ደግሞ 611 ሜትር እንደደረሰ አስታውቀዋል፡፡
የመጀመርያው ሙሌት በተደረገበት 2012 ዓ.ም. የግድቡ ቁመት 565 ሜትር ሆኖ፣ 4.9 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ መያዙ ተገልጾ ነበር፡፡ የግድቡ ቁመት 595 ሜትር ሲደርስ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መያዝ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
አሁን የግድቡ ቁመት 600 ሜትር መድረሱ የሚይዘው የውኃ መጠን ከ18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የመያዝ አቅም አለው፡፡ ግድቡ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ቁመቱ 640 ሜትር ይደርሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በዚህ ዓመት 22 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መያዝ የሚያስችል ሥራ ቢሠራም፣ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን የውኃ ድርሻ እንዳይቀንስ በተራዘመ ጊዜ ለመሙላት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚደረጉ ንግግሮች እንዲቀጥሉ የጠየቁት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ከድርድር ውጪ ያለ አማራጭ ግድቡ ላይ የሚከናወን ሥራ እንደማያስቆም ገልጸዋል፡፡