Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በበጀት ዓመቱ ከቡና ኤክስፖርት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መጨረሻ 1.4 ቢሊዮን ዶላር የተገኘበት የቡና ኤክስፖርት፣ በተያዘው የበጀት ዓመት 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክትር አቶ ሻፊ ዑመር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በ2014 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ወደ የተለያዩ የዓለም አገሮች ከላከችው ቡና 1.4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ይህ ገቢ አገሪቱ ቡና ወደ ውጭ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የመጀመሪያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደነበር አስታውሰው፣ በበጀት ዓመቱ የተሠሩትን በጎ ሥራዎች በማስቀጠል 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 300 ሺሕ ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን የቡና መጠን በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ 360 ሺሕ ቶን ለማድረስ መታቀዱ ታውቋል፡፡

አቶ ሻፊ እንዳስረዱት፣ በበጀት ዓመቱ ከቡና ለማግኘት የታቀደው ዕቅድ ከባድና የተለጠጠ ነው፡፡ ነገር ግን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎችና አሠራሮችና የግብይት አማራጮችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ ነባርና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ዕቅዱን ለማሳከት ይሠራል፡፡

በሌላ በኩል የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው በሆነው የሐምሌ ወር 29,186 ቶን ቡና  ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 26,866 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ መላኩን የተረጋገጠ ሲሆን፣ በዚህም ለማግኘት ከታቀደው 147 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አሥር ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው 157 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

የተገኘው ገቢ ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የ42.49 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ ይህም ጉልህ የሆነ ብልጫ የታየበት አፈጻጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ 31,145 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባ 115 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ መነገሩ ይታወሳል፡፡

አምና የኢትዮጵያ ከፍተኛ የቡና ገዥ የነበሩ አገሮች በሐምሌ ወር ዝርዝር ውስጥም በቦታቸው ሲቀጥሉ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና በቅደም ተከተላቸው በሐምሌ ከፍተኛ የቡና ግዥ የፈጸሙ አገሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በተያዘው ዓመትም የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የተጠናከረና ዘመናዊ አሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ምርት ሳይባክንና ጥራቱ ሳይጓደል በመላክ የሚገኘውን ገቢ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በኮንትሮባንድ የተሳተፉ አካላትን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ላይ የተጀመረው ዕርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከቡና የሽኝት ጣቢያዎች የወሰዱትን ቡና ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃና ማከማቻ ሳያደርሱ ተሰውረዋል የተባሉ 18 ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ላይ ዕግድ መውጣቱንና በፌደራል ፖሊስ አማካይነት ተሽከርካሪዎቹ እንዳይንቀሳቀሱና እንዳይሸጡ ከማድረግ ባለፈ፣ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ በሕግ ጥላ ሥር ከቆዩት ተጠርጣሪዎች ውስጥ በዋስትና የወጡ እንደሚገኙ፣ ሌሎችም የሚፈለጉ እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ በሻገር በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች በፌደራል ፖሊስና በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኩል የማደራጀት ሥራ መከናወኑን ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በ2014 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኝት በዘርፉ የመጀመርያ የሚባል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ሲሆን፣ ከዚህ ገቢ ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነው ድርሻ ከቡና ኤክስፖርት የተገኘ መሆኑ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች