Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከ400 በላይ የትግራይ ተወላጆች ወደ ራያ ቆቦ ከተማ በየቀኑ እየገቡ ነው ተባለ

ከ400 በላይ የትግራይ ተወላጆች ወደ ራያ ቆቦ ከተማ በየቀኑ እየገቡ ነው ተባለ

ቀን:

በከተማዋ የእንቅስቃሴ ገደብ ተደርጓል

የራያ ቆቦ ከተማ ነፃ ከወጣችበት ከታኅሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ራያ አላማጣ፣ ራያ ዘጎ ኮረማና ባላን ሳይጨምር በየቀኑ ከ400 በላይ የትግራይ ተወላጆች ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የትግራይ ተወላጆች በዋጃ በኩል ሌሊትና ቀን በጋሪና በእግር በመጓዝ ለመከላከያ፣ ለፋኖና ለልዩ ኃይል እጃቸውን በመስጠት ወደ ራያ ቆቦ ከተማ እየገቡ መሆኑን የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ምክትል ኮማንደር አባተ ዓለሙ፣ ‹‹ከትግራይ ክልል መሀል ከተማ ከሚባሉ ቦታዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተፈናቅለው የሚመጡ የትግራይ ተወላጆችን፣ በተገቢው መንገድ ምርመራ በማድረግ ወደ መጠለያ ማዕከል እንዲገቡ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከትግራይ ክልል የሚመጡ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ወጣቶቹ ወደ መጠለያ ማዕከሉ ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊ የሆነ ምርመራ እንደሚካሄድባቸው አስረድተዋል፡፡

የራያ ቆቦ ከተማ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ከተማዋ የገቡ የትግራይ ክልል ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን፣ ነገር ግን ይህንን ያህል ገብተዋል የሚለውን ቁጥር ለማወቅ ለጊዜው መረጃ እንደሌላቸው ምክትል ኮማንደር አባተ አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው የሚመጡ የትግራይ ተወላጆችን አስፈላጊውን የሆነ ግብዓት በማቅረብ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹በተለይ ከደኅንነት አኳያ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይደርስባቸው ለማድረግ፣ በየቀበሌው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ወደ ወረዳው በማምጣት፣ የተጠናከረ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተደረገ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአዲግራት ከተማ ተወላጅ የሆነና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ ሕፃናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል ብሏል፡፡ በተለይ ሕፃናትና ወጣቶች ካልታጠቁና ካልተመለመሉ ወላጆቻቸው ይታሰራሉ የሚለው ወጣቱ፣ ከትግራይ ክልል በመሸሽ ለደላሎች ገንዘብ በመክፈል ወደ ራያ ቆቦ ከተማ መግባት እንደቻለ አስረድቷል፡፡

ከአዲግራት ወደ ራያ ቆቦ ከተማ ሲገባ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ መምጣቱን፣ በቀጥታም ወደ ራያ ቆቦ ከተማ ከመግባቱ በፊት አላማጣ ማረፉን አስታውሷል፡፡

ወደ ራያ ቆቦ ከተማም በገባ ወቅት ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠመውና መከላከያ፣ ፋኖም፣ ሆነ ልዩ ኃይል በተገቢው መንገድ በመንከባከብ ለሚመለከታቸው አካላት አስረክበውናል ብሏል፡፡

አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ምክንያት እንደ ልብ ወጥቶ ለመንቀሳቀስ እንደተቸገረ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ያለው መዋቅር አንድ ዓይነት አሠራር ስለሚከተል ማኅበረሰቡ እየተጎዳ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ከመቀሌ 05 ቀበሌ ወደ ራያ ቆቦ ከተማ ተፈናቅሎ የገባው ወጣቱ እንደገለጸው፣ በጦርነቱ ምክንያት አብዛኞቹን የትግራይ ተወላጆች በረሃብ እየተጎዱ ነው፡፡

‹‹በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 20 ሺሕ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ከፍሎች ምግብ ነክ የሆኑ ግብዓቶችን ለመግዛት አቅም ስለሌላቸው ስደትን አማራጭ እያደረጉ ነው፤›› ብሏል፡፡

በጦርነቱም በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ተጎድተዋል ያለው ወጣቱ፣ ወደ ቆቦ ከተማ ሲመጣ ብዙ ኪሎ ሜትር አቆራርጦ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወደ ራያ ቆቦ ከተማ በሚገባበት ጊዜ ዋጃ አካባቢ የመከላከያ ሠራዊት እንደተቀበለው፣ ከብዙ እንግልትና ሥቃይ በኋላ በነፃነት እየኖረ መሆኑን አክሏል፡፡

የራያ ቆቦ ከተማ የትግራይ ክልል አዋሳኝ እንደ መሆኑ መጠን የፀጥታ ችግር እንዳይከሰትና ሰርጎ ገብ የሆኑ ግለሰቦችን ለመለየት፣ ከዚህ በፊት ከጥቅምት 23 እስከ ጥር 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ እንደነበረ የራያ ቆቦ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ነጋ ድንበሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአሁኑ ወቅትም ተነስቶ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ አዲስ በማራዘም፣ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል ሲሉ አክለው አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...