በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ከለጋሽ አገሮችና ድርጅቶች ይመጣ የነበረው ድጋፍ በመቀነሱ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅት አሠራር ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው ወርኃዊ የምግብ አቅርቦት ከ50 በመቶ በታች መውረዱ ተገለጸ፡፡
በምግብ አቅርቦት መቀነስ ምክንያት በመጠለያ የሚኖሩ ስደተኞች አማራጮችን ፍለጋ ወደ ወንጀልና አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲሰማሩ እያደረጋቸው መሆኑን፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡
የምግብ አቅርቦቱ መቀነስ ባሰከተለው ተፅዕኖ ስደተኞች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉና ሲገቡ ሊያመጣ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ መሆኑን፣ መሠረታዊ አቅርቦት ከሌለ ከመጠለያዎች ወጥተው ጫካ ከመመንጠር እሰከ ሰብል መዝረፍና ሌሎች መሰል ወንጀሎች ላይ መሳተፋቸው ስለማይቀር፣ ተቋሙ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ለለጋሽ ተቋማት ውትወታ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉት 870 ሺሕ ስደተኞች መሀል 70,000 የሚሆኑት በከተማ ውስጥ እንደሚኖሩ አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡
ስደተኞቹ ከፍተኛ የምግብ አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው የገለጹት አቶ ተስፋሁን፣ ስደተኞችም ቅሬታ እያሰሙ መሆናቸውንና በተለያዩ አጋጣሚዎች ለጋሽ አገሮች ጋር ሸክምን በመጋራት መርህ እንዲሳተፉና ዕገዛ እንዲያደርጉ ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በስደተኝነት ለመኖር የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚያሟሉ አካላት ተቀባዩ አገር የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለጋሽ አገሮች ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ከመቶ ሚሊዮን ማለፉን የጠቆሙት አቶ ተስፋሁን፣ ለጋሽ አገሮች የመሰላቸትና ለትኩስ ጉዳዮች በተለይም ለአፍጋኒስታን፣ ለሶሪያ፣ ለዩክሬንና ለመሳሰሉ አገሮች የበለጠ ትኩረት እየሰጡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ድጋፍ እየቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በስደተኞች ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት እየሰፋ የመጣ ሲሆን፣ እንደ ዋና ምክንያት የተጠቀሰውም የኮቪድ-19 መስፋፋት፣ የተለያዩ አገሮች የፖለቲካ ውሳኔና የአፍጋኒስታንና የዩክሬን ጦርነቶች ተጠቅሰዋል፡፡
ስደተኞች በተለይ ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው አሁንም እየቀጠለ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል በመጠለያ የነበሩና በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለመጡ ኤርትራውያን የከተማ መታወቂያ መሰጠቱንና ያላገኙ ስደተኞችን መታወቂያ እንዲያገኙ ከመንግሥት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡