Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሽያጭ ታሪፍ ማስተካከያ ተደረገበት፡፡ 

ሁለቱ አገሮች ከአሥር ዓመታት በፊት ለኃይል ሽያጭ አንድ ኪሎ ዋት በሰዓት በሰባት የአሜሪካ ሳንቲም ታሪፍ ስምምነት ላይ ደርሰው የነበሩ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ ሽያጩ በመዘግየቱ ምክንያት ኬንያ ታሪፍ እንዲቀነስላት ጠይቃለች፡፡

በየካቲት 2014 ዓ.ም. ሁለቱ አገሮች በድጋሚ ንግግር ሲጀምሩ የመጀመሪያ ስምምነታቸው ላይ ለማስተካከል የተስማሙባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ የታሪፉ ጉዳይ መቋጫ አላገኘም ነበር፡፡ ሁለቱ አገሮች ከሦስት ሳምንት በፊት በኬንያ የመጨረሻውን ስምምነት ከመፈጸማቸው በፊት የዋጋ ማስተካካያው ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በጥቅምት 2015 ዓ.ም. የኤሌክትሪክ ሽያጩ ሲጀመር ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሰዓት በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም እንደሚቀርብላት አቶ አሸብር ገልጸዋል፡፡ ይህ ታሪፍ ኬንያ ቅናሽ ተደርጎ እንዲሸጥላት ከጠየቀችው አምስት የአሜሪካ ሳንቲም የሽያጭ ታሪፍ በ1.5 ሳንቲም የጨመረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥበት ታሪፍ ከዚህኛው ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡ ለጂቡቲ የሚሸጠው የኃይል ታሪፍ እንደ ወቅቱ የሚለያይ ሲሆን፣ አንድ ኪሎ ዋት ኃይል በሰዓት በስድስትና በሰባት የአሜሪካ ሳንቲም ይሸጣል፡፡ በ2014 ዓ.ም. በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለጂቡቲ ከተሸጠው ኃይል 28.4 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡

ኬንያና ኢትዮጵያ በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም መስማማት ላይ የደረሱት ሁለቱም አገሮች ከጥቅማቸው በመቀነስ መሆኑን ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹የ25 ዓመት ውል ነው የገባነው፣ ለእኛ ጥሩ ስምምነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በንግግሩ ወቅት ኬንያ ዋጋ እንዲቀነስላት ስትጠይቅ ያነሳችው አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያ ለሱዳን ከሰባት የአሜሪካ ሳንቲም ባነሳ ዋጋ ኃይል ትሸጣለች የሚል ነው፡፡ በጊዜው የታሪፍ ቅናሹን ያልተቀበለው የኢትዮጵያ መንግሥት በተቃራኒው፣ ዋጋው በየጊዜው እየተከለሰ ጭማሪ እንዲደረግበት ካልሆነ ቢያንስ ስምምነቱ ላይ ባለበት ይቀጥል የሚል ነበር፡፡

አሁን ከኬንያ ጋር ስምምነት የተደረሰበት ታሪፍ አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ሦስት ብር ከአርባ ሳንቲም ገደማ ይደርሳል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሰዓት 500 ኪሎ ዋት ፍጆታ ካላቸው ደንበኞቹ አንድ ኪሎ ዋት በሰዓት ከሚሸጥበት ሁለት ብር ከ48 ሳንቲም ጋር ሲነፃፀር በአንድ ብር ገደማ ይበልጣል ፡፡

ሁለቱ አገሮች በሐምሌ ወር ስምምነታቸውን ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ አሁን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን የመፈተሽ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ አከባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ በይፋ እንደሚጀመር አቶ አሸብር ገልጸዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ሽያጩ ሲጀመር ከአሥር ዓመት በፊት ውል የተገባበት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ለኬንያ አይቀርብም፡፡ ሁለቱ አገሮች ኢትዮጵያ ከ400 ሜጋ ዋት ኃይል ውስጥ ቢያንስ 85 በመቶውን ሳይቆራረጥ እንድታቀርብ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ኬንያ ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ሲጀመር ተቀንሶ በጊዜ ሒደት እየጨመረ እንዲሄድ ተግባብተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ውሉ ተፈጻሚ ከሚሆንበት አጠቃላይ 25 ዓመታት ውስጥ በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ወደ ኬንያ የሚላከው ኃይል በግማሽ ቀንሶ 200 ሜጋ ዋት ይሆናል፡፡ ከአምስተኛው እስከ ሰባተኛው ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚቀርበው ኃይል በቀን ለ18 ሰዓታት 400 ሜጋ ዋት፣ ለቀሪዎቹ ስድስት ሰዓታት ደግሞ 200 ሜጋ ዋት ነው፡፡ ከሰባተኛው ዓመት በኋላ በቀን ለ24 ሰዓት 400 ሜጋ ዋት ኃይል ማቅረብ እንደሚጀመር አቶ አሸብር አብራርተዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረወው የኢትዮ ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ 1,068 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 1.26 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡

የማስተላለፊያ መስመሩ በኢትዮጵያ በኩል 437 ኪ.ሜ ርዝመት ሲኖረው፣ ቀሪው 631 ኪ.ሜ. ያለው በኬንያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው መስመር ከወላይታ-ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ ጀምሮ አርባ ምንጭ፣ ኮንሶ፣ ብርንዳር፣ ያቤሎና ሜጋን ያቋርጣል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ለሩዋንዳ፣ ለታንዛኒያና ለብሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ንግግር እያደረገች ነው፡፡ የኬንያው መስመር ዝርጋታ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ለማቅረብ ላቀደችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በቀጣዩ ዓመት የሚጀመረው፣ የኢትዮጵያና ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ላይ መተማመን እንደሚጨምር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች