Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ...

አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

ቀን:

ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች በመታወቂያ እየተለዩ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ይደረግ የነበረው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ቆሞ፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች አመራሮች ተወያይተው መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ነፃ እንዲሆን መደረጉ ተገለጸ፡፡

ከአማራ ክልል በተለይም ከሰሜን ወሎና ከደቡብ ወሎ አካባቢዎች ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የአማራ ክልልን አልፈው በኦሮሚያ ክልል ከሸኖ ከተማ ጀምሮ እስከ ሰንዳፋ ባሉት አካባቢዎች በሚደረግ ፍተሻ፣ በመታወቂያ እየተለዩ እንዲመለሱ ሲደረጉ እንደነበር መንገደኞች መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ችግሩ ተቃሎ መንገደኞች በሰላም መጓዝ መጀመራቸውን፣ በነበረው የማስተጓጎል እንቅስቃሴ ከሕግ ውጪ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበሩ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚጀመር ከክልሉ አመራሮች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን የሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታና አስተዳደር መምርያ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ መንገዱ ነፃ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዋሲሁን፣ በዚህም እስካሁን የገጠመ ችግር እንደሌለና በቀጣይ ምንም ዓይነት መሰል ክስተት ከታየ ዕርምጃ ለመውሰድ ክልሎቹ መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡

የታየው ክልከላ የቅርብ ጉዳይ እንዳልሆነ፣ የዋለና ያደረ የብዙ ጊዜ ሥቃይና እንግልት የታየበት ሒደት እንደነበር አቶ ዋሲሁን ገልጸዋል፡፡

‹‹የችግሩ ፈጣሪዎች የኦሮሚያ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉ በመሆናቸው ፍላጎታችን በፌዴራል የፀጥታ መዋቅር እንዲጠበቅ ነው፤›› የሚሉት አቶ ዋሲሁን፣ በቀጣይ የሁለቱ አዋሳኝ ዞኖች በጉዳዩ ላይ ይመክሩበታል ብለዋል፡፡

ችግሩ በይፋ ከተነገረ ሁለት ሳምንታት በኋላ ዘግይቶም ቢሆን ዓርብ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚመጡ ትራንስፖርት ተጠቃሚ የሆኑ መንገደኞች በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ባሉ የፍተሻ ጣቢያዎች በዋናነት በሸኖ፣ በአሌልቱ፣ በበኬ፣ በሰንዳፋና በለገጣፎ አካባቢዎች በሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች መታወቂያቸው እየታየ ወደመጡበት እንዲመለሱ በማድረግ፣ ከፍተኛ የሆነ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደ ደረሱት አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ይህ ሕገወጥ ድርጊት አንድ ወር በላይ እንደሆነውና በአንዳንድ ኬላዎች ላይ ተጓዦች ለማለፍ ሲሞክሩ ገንዘብና የአዲስ አበባ መታወቂያ ይጠየቁ እንደነበር፣ እንዲሁም መንገደኞች ለሕክምናና ለተለያዩ አገልግሎቶች በሚጓዙበት ወቅት ያላግባብ እንግልት እንደ ደረሰባቸው መረጃ ማግኘቱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

መንግሥት ከተለያዩ የአማራ ክልል ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መንገደኞችን የመንቀሳቀስ መብት እንዲያከብርና እንዲያስከብር፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በአፋጣኝ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት የሰዎችን በአገራቸው የመንቀሳቀስ መብት እንዲያከብርና እንዲያስከብር ሲል ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም  በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ መንገደኞችን የሚያጉላሉ፣ ያላግባብ ገንዘብ የሚቀበሉ፣ የሚደበድቡና የሚያስሩ የፀጥታ አካላትን ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩ የሕወሓት የሽብር ቡድን በወረራ ይዟቸው ከነበሩት የአማራ ክልል አካባቢዎች የተለያዩ የመታወቂያ ማኅተሞችና የአስተዳደር ሰነዶችን በመዝረፉ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህን ሐሰተኛ መታወቂያዎችና ሰነዶች የያዙ ሰርጎ ገቦች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ በመያዛቸው ምክንያት የሚደረግ የክትትል ሥራ መሆኑን ይናገራል፡፡

በመሆኑም የጥፋት ተልዕኮ የያዙና ከአማራ ክልል ተዘርፈው በተወሰዱ ሰነዶች ተመሳስለው የተሠሩ መታወቂያዎችን የያዙ ግለሰቦች አሁንም ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እንዳለ ለፀጥታ ኃይሎች መረጃው በመድረሱ፣ ይህንን ለመከላከል ጥብቅ ፍተሻዎችና ማጣራቶች እየተደረጉ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለሪፖርተር መናገሩ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...