Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  ቀን:

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ፣ መስከረም 2014 ዓ.ም. መንግሥት ሲመሠረት በተዘረጋው አዲስ የፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት መዋቅር መሠረት ራሳቸውን አዋቅረው ያጠናቀቁት 31.2 በመቶ የሆኑት መሥሪያ ቤቶች ብቻ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

  ከአሥር ወራት በፊት የፀደቀው የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ካቋቋማቸው 22 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም መዋቅራቸውን ዘርግተው ጨርሰዋል፡፡

  ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ የራሳቸውን መዋቅር ቢጨርሱም፣ በሥራቸው የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት መዋቅር በአብዛኛዎቹ እስካሁን እንዳልተጠናቀቁ፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተቋማዊ አደረጃጀት የሥራ ምዘናና የሰው ኃይል ልማት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ይገዙ የማነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  እንደ ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገለጻ፣ ካሉት 160 መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 50 ያህሉ መዋቅር ዘርግተው ሲያጠናቅቁ፣ 60 ያህሉ የመዋቅር ዝርጋታቸው በሒደት ላይ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 50 መሥሪያ ቤቶች የመዋቅር ዝርጋታ ሥራቸው እስካሁን አልተጀመረም፡፡

  በዚህም ምክንያት አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በአዲሱ አዋጅ የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት ለመተግበር እየተቸገሩ መሆኑን ሪፖርተር ከሌላ የኮሚሽኑ ባለሥልጣን ሰምቷል፡፡

  ከዚህም ባሻገር በመዋቅሩ መሠረት የተሰጣቸው ኃላፊነት ከሌላ መሥሪያ ቤት ጋር የሚደራረብ የሆነባቸው መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ሪፖርተር ተረድቷል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል በማዕድን ሚኒስቴር ሥር ያለው የማዕድን ልማት ኢንስትቲዩትና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ይገኙበታል፡፡

  የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲም አዋጁ ለተለያዩ የመንግሥት ተቆጣጣሪ ተቋማቱ የየዘርፋቸውን ደረጃዎች እንዲቆጣጠሩ መፍቀዱ የኤጀንሲውን ኃላፊነት የቀማ መሆኑን በመጥቀስ ቅሬታ አቅርቦ ነበር፡፡

  አቶ ይገዙ እንደሚያስረዱት፣ የመዋቅር ዝርጋታ ሥራው እስካሁን ግማሽ ያልደረሰበት አንዱ ምክንያት፣ መሥሪያ ቤቶቹ በቶሎ መዋቅራቸውን ይዘው ወደ ኮሚሽኑ አለመምጣታቸው ነው፡፡ ወደ ኮሚሽኑ ከመጡም በኋላ ቢሆን የመዋቅር ሒደቱ እንደ የሥራ ደረጃ ምዘና ያሉ የተለያዩ ደረጃዎችን የሚያልፍ መሆኑም ለመዋቅር ዝርጋተው አለመጠናቀቅ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

  አቶ ይገዙ፣ ‹‹ሥራው በራሱ ሁለትና ሦስት ደረጃ (ስቴጅ) አለው፡፡ በእኛ ከተሠራ በኋላም ከመሥሪያ ቤቶች ጋር ምልልስ ይኖራል፡፡ ቅሬታ ሲነሳ ዳግም የሚመዘን የሥራ ደረጃና ሁለት ጊዜ የሚሠራ መዋቅርም አለ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

  ኮሚሽኑ የመሥሪያ ቤቶቹን የመዋቅር ዝርጋታ ሥራ ለማጠናቀቅ ያዋቀረው ኮሚቴ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ በመሆን ሥራውን እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል፡፡

  የአንድ መሥሪያ ቤት የመዋቅር ዝርጋታ ሥራ በኮሚሽኑ የሥራ ምዘና ተደርጎና ደረጃ ተዘጋጅቶ ቢጠናቀቅም አይቋጭም፡፡ መሥሪያ ቤቶቹ በአዲሱ የሥራ መደብ ላይ ሠራተኞቻቸውን የሚመድቡት፣ ሠራተኞቻቸው ለቦታው ብቁ መሆናቸውን በድጋሚ መዝነው ሲያረጋግጡ ነው፡፡ የየመሥሪያ ቤቶቹ የዘርፍ ኃላፊዎችን ጨምሮ ቋሚ የሆኑ ሠራተኞች በሙሉ በምዘና ውስጥ እንደሚያልፉ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡

  በዚህ ሒደት ውስጥ ከሥራ ውጪ የሚሆኑ ሠራተኞች እንደሚኖሩ ታሳቢ ተደርጎም፣ ኮሚሽኑ በግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ምደባ ያላገኙ ሠራተኞች የሚስተናገዱበት መመርያ አውጥቷል፡፡ በመመርያው መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ምደባ ያላገኙ ሠራተኞቻቸውን ወደ ተጠሪ ተቋሞች በመላክ እንዲመደቡ ያደርጋሉ፡፡ ሠራተኞቹ በተጠሪ ተቋማት ውስጥ ምደባ የማያገኙ ከሆነ፣ ወደ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ተልከው በኮሚሽኑ አማካይነት ሌላ ዘርፍ ያለው መሥሪያ ቤት ላይ እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡

  ሠራተኞቹ አዲስ ምደባ እስከሚያገኙ ድረስም ደመወዛቸው እየተከፈላቸው ይቆያሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት ቆይተው የሥራ መደብ ያልተገኘላቸው ወይም በተገኘላቸው ለመሥራት ፈቃደኛ ያልሆኑ ከ12 ሺሕ ብር የማያንስ የአንድ ዓመት ደመወዝ ተከፍሏቸው ይሰናበታሉ፡፡

  ቢያንስ ከ25 ዓመት በላይ አገልግለው የጡረታ መውጫ ዕድሜያቸው ሊደርስ አምስት ዓመትና ከዚያ በታች የሆናቸው ሠራተኞች ፈቃደኛ ከሆኑ ጡረታ መውጣት ይችላሉ፡፡

  ምደባ ያላገኙ ሠራተኞች በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት የሚፈልጉ ከሆነ፣ መሥሪያ ቤታቸው ለሥራ ክህሎት ሚኒስቴር የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው የማድረግ መብት አላቸው፡፡

  እነዚህን ሁሉ ሒደቶች የሚያልፈው አጠቃላዩ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት መዋቅር ዝርጋታ፣ በቀጣዩ ዓመት ከኅዳር እስከ ታኅሳስ ወራት ባሉት ጊዜያት ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ዳይሬክተር ጄኔራሉ አቶ ይገዙ ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...