Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመሩ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የፈጠረው ደስታ ቃላት ከሚገልጹት በላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በየካቲት ወር የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ አንድ ተርባይን ሥራ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ መድረሷ፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በዓባይ ወንዝ ባክኖ መቅረት ከሚፈጥረው ቁጭት ውስጥ ወጥተው ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከልዩነቶቻቸው በላይ አንድ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ፣ በመሀላቸው ለቅራኔ የሚሆን ሥፍራ እንደማይኖር የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጨማሪ በርካታ ግድቦች፣ የመስኖ እርሻዎች፣ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በቴክኖሎጂ የሚታገዙ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑባት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ተግባራትንም ጎን ለጎን ማካሄድ ይቻላል፡፡ መንግሥትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን ሕግ ሲያከብሩና ሲያስከብሩ፣ ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች በዓይነትም ሆነ በመጠን ይቀንሳሉ፡፡ ለኢትዮጵያ መተባበር እንጂ ተቃርኖ አይጠቅምም፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች በጣም እየበዙ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ሰበብ እያነፈነፉ ቅራኔ መፍጠር በጣም ከመለመዱ የተነሳ፣ ለአገር የሚጠቅሙ ነገሮች ሳይቀሩ የልዩነት ማራገቢያ እየሆኑ ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት አገር ማስተዳደር የሚጠበቅበት መንግሥት አንደኛው የቅራኔ መፈልፈያ ማሽን ሲሆን፣ በግራና በቀኝ የተሠለፉ የፖለቲካ ተዋንያንና አጃቢዎቻቸውም እንዲሁ፡፡ በተደጋጋሚ እንደምንለው ኢትዮጵያ ከመጠን በላይ ችግሮች የተቆለሉባት አገር ናት፡፡ ችግሮቹን በቅደም ተከተል በመለየት ሸክሟን ለማቅለል መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ በየዕለቱ ተጨማሪ ችግሮችን በማባዛት ቅራኔ መዝራት ቀላሉ ሥራ ሆኗል፡፡ ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችን በወፈፍ በረር ለማየት ሲሞከር በርካታ አስተዛዛቢ ነገሮች ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአማራ ክልል ወሎ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ምክንያቱ በውል አይነገርም፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እሮሮዎች ሲቀርቡ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥ መንግሥታዊ አካል የለም፡፡ መሰንበቻውን ደግሞ አዲስ አበባና ኦሮሚያ የአስተዳደር ክልል ወሰን ለማካለል ተስማምተዋል ተብሏል፡፡ የማካለሉ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ተጨማሪ ቅራኔ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ካልተደረገ ችግሩ ተባብሶ ይቀጥላል፡፡

  ለአገር ሰላምና ደኅንነት ሲባል መብታቸውን ለማስከበር የሚነሱ ወገኖች ከምንም ነገር በላይ ሕግ አክባሪ መሆን እንዳለባቸው ሲጠበቅ፣ መንግሥትም ለሚቀርቡለት ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎችን በአግባቡ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ሕግ ለማስከበር የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዕርምጃዎቹ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል በሕዝብና በመንግሥት መሀል ቅራኔ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ጥያቄ አቅራቢው ሰላማዊና ሕጋዊ መንገዶችን ሲከተል፣ መንግሥት ደግሞ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ተገቢውን ዕርምጃ ወስዶ ተቃርኖን ማስቀረት ይኖርበታል፡፡ ከልምድ እንደሚታወቀው ግን ብዙ ጊዜ የመንግሥት ውሳኔ በጣም ቀርፋፋ በመሆኑ፣ የጥያቄ ወይም የአቤቱታ አቅራቢዎችን ትዕግሥት ስለሚፈታተን ችግሮች ይፈጠሩና የኃይል ዕርምጃዎች የበለጠ ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ የመንግሥት ተቋማት ደካማነትና ብቃት ባላቸው አመራሮች አለመመራት ሲሆን፣ በተጨማሪም ሥራን በቅደም ተከተል ለማከናወን የሚያስችሉ ባለሙያዎች አለመኖርም ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ይልቅ ልማዳዊና ብልሹ አሠራር ስለሚበዛ፣ የአገልግሎት ፈላጊዎች ምሬት ጣሪያ ይነካና ቅራኔው ይባባሳል፡፡

  ምንም እንኳ በሁሉም መስኮች ችግሮች በበዙባት አገር ውስጥ ሁሉም ነገር በተደላደለ ሜዳ ላይ ይገኝ ማለት ቅንጦት ቢሆንም፣ በተቻለ መጠን ከዘመኑ እኩል ለመራመድ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ማስፈን የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የገጽታ ለውጥ በማድረግ መልካቸው እያማረ ነው፡፡ የገጽታ ለውጡ ሙሉ ሊሆን የሚችለው ግን፣ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ተቋማዊ ጥንካሬ አግኝቶ አገልግሎቱ አርኪ ሲሆን ነው፡፡ ብቃት ካላቸው መሪዎች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች በተጨማሪ ለዘመኑ የሚመጥኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች መኖር አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ተቋም ደጃፉ ላይ ካንጠለጠለው የሥነ ምግባር መመርያ በላይ ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርሆች መገዛቱን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ መርሆች በፍርድ ቤቶች፣ በዓቃቤ ሕግ፣ በፖሊስና በሌሎች የፍትሕና የፀጥታ አካላት ጭምር ተግባራዊ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ ተከብሮ በሥርዓት መኖር መለመድ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ሕግ እንዲያከብር እንደሚጠየቀው ሁሉ፣ ሁሉም የመንግሥት ተቋማትና ተሿሚዎቻቸው ጭምር ሕግ የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡

  ሕግ ሳይከበር ሲቀር ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ነው የሚሰፍነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብዙ ሥፍራዎች ሕገወጦች የበዙት ሕግ የማስከበር ግዴታ ያለባቸው አካላት ስለሰነፉ ነው፡፡ ከመንግሥታዊ ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት የሚዘረፈው ሕግ ማስከበር ስላቃተ ነው፡፡ በሕግ የሕዝብና የመንግሥት ነው የሚባልለት መሬት በጠራራ ፀሐይ ያለ ከልካይ እየተወረረ የሚታጠረው፣ ለሕግ ልዕልና የተሰጠው ሥፍራ እዚህ ግባ ስለማይባል ነው፡፡ ነዳጅን የመሰለ ስትራቴጂካዊ ምርት ከማደያ ጠፍቶ በየመንደሩ የሚቸረቸረው ተቆጣጣሪ ሲጠፋ ነው፡፡ ግብር ከፋዩን ሕዝብ መብቱ የሆነውን አገልግሎት የሚነፍገው ሹም የሚናገረው የሌለው፣ የተቀመጠበት ወንበር ተቆጣጣሪ ስለሌለበት ወይም በጥቅም ተጋሪዎች ከለላ ስለሚሰጠው ነው፡፡ አንድ ችግር አጋጥሞ አቤት ሲባል መልስ የሌለው፣ መልስ መስጠት ያለበት አካል ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለበት ትዝ ስለማይለው ነው፡፡ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ሕዝብ ደም ዕንባ እያለቀሰ ኢትዮጵያ የቅራኔ ማምረቻ ሆናለች፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን ሕግ ያስገድዳል፡፡ ይህ ግዴታ የመጣው ደግሞ ሕዝብ በየአምስት ዓመቱ መርጦ ሥልጣን ላይ የማውጣት ሉዓላዊ መብት ስላለው ነው፡፡

  በአሁኗ ኢትዮጵያ ለተቃርኖ መፈጠር ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያውያንን በማንነት መከፋፈል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ታላቅ አገር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅኝ ካልተገዙ አገሮች በግንባር ቀደምትነት ስሟ የሚነሳው ልጆቿ ተባብረው ለሉዓላዊነቷና ለግዛት አንድነቷ በመዋደቃቸው እንደሆነ ታሪክ ህያው ምስክር ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነትና በመሳሰሉት የተለያዩ መልኮች አሏቸው፡፡ ኢትዮጵያን በዘመናት ቅብብሎሽ እዚህ ያደረሷት ልጆቿ ግን ከልዩነቶቻቸው በላይ የሚኮሩባቸው በርካታ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች አሏቸው፡፡ በእነዚህ አኩሪ እሴቶች ምክንያትም አንድ ላይ ከመኖር አልፈው ተጋብተውና ተዋልደው ተዛምደዋል፡፡ ይህንን የመሰለ ማንም ሊበጥሰው የማይችለው መጋመድ ነው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የነፃነት ቀንዲል ያደረጋት፡፡ ይህንን የመሰለ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በመሻር መታወቂያ ላይ ሳይቀር ማንነትን በግዳጅ በመለጠፍ፣ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ምሥል ቀዶ ለመጣል የሚደረግ ሙከራ ከቅራኔ ውጪ ምንም አይፈይድም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በመፋቅ ክብር ማጣት ከማሳፈር ውጪ ዕርባና የለውም፡፡ ስለዚህ ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  በቴሌ ብር የማይሠሩ ማደያዎች ቀነ ገደብ ተቀመጠባቸው

  ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለመሥራት እየመከረ ነው በኢትዮጵያ...

  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተጀመረው የድርድር ሒደት አሳታፊ እንዲሆን ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣  በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...