በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል
በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በትራፊክ አደጋ ምክንያት የደረሰው የንብረት ጉዳት በ494 በመቶ መጨመሩ ተነገረ፡፡
በ2014 ዓ.ም. በትራፊክ አደጋ ሳቢያ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው የሞት አደጋና ቀላል የአካል ጉዳት በቁጥር አነስ ብሎ ቢመዘገብም፣ በአንፃሩ በንብረት ላይና በሰዎች ላይ የደረሰው ከባድ የአካል ጉዳት መጨመሩን የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በተለይ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያና ሁለተኛ የሩብ ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ ተከስቶ የነበረው የንብረት ውድመት ከፍተኛ እንደነበር ታውቋል፡፡ ነገር ግን ከመጋቢት ወር አንስቶ በነበሩት ወራት የአደጋ መጠኑ መቀነሱ ተገል ጿል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ሥራዎችን ከማከናወን ጎን ለጎን የትራፊክ ሕግ ለማስከበር በተከናወነ ሥራ ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 3,971 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ የአደጋ መጠኑ በ2013 ዓ.ም. ከነበረው አኃዝ በ191 ቀንሶ ታይቷል ተብሏል፡፡
ከትራፊክ አደጋ ባሻገር የመድን አገልግሎት ፈንድ የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው አገልግሎቱ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 1.1 ሚሊዮን ያህል ተሽከርካሪዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን እንዲያገኙ ለማድረግ አቅዶ፣ 829,992 ተሽከርካሪዎች ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በዚህም ለካሳ ከሚሰበሰበው ፈንድ ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል፡፡
የአስቸኳይ ሕክምና ፈንድ በመሰብሰብ ረገድ ደግሞ ተቋሙ ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን፣ በተሰበሰበው ገቢ 26,499 የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች በተለያዩ የመንግሥትና የግል የሕክምና ተቋማት የነፍስ አድን አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡
አቶ ጀማል እንዳስታወቁት ከፖሊስና ከጤና ተቋማት የሚመጡ መረጃዎችን በኦንላይን ለማግኘት እንዲቻል፣ ከውጭ ድርጅት ጋር ስምምነት ተደርጎ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የፈጸመውን ስምምነት የሚመራው የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ስምምነቱ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሽከርካሪ አደጋ ሲደርስ ተፈላጊውን መረጃ ኦንላይን መዝግቦ ወደ ዳታ ቤዝ የማስገባትና መሰል ሥራዎችን የሚመራበትን ቴክኖሎጂ ማቅረብን የተመለከተ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
‹‹የአገራችን የዳታ ሲስተም በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ በጣም ፈተና ውስጥ ነን፤›› ያሉት አቶ ጀማል፣ በየዓመቱ አዲስ ሰሌዳ ለጥፈው ወደ ሥራ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ሁሉ የአገልግሎት ጊዜያቸው ተጠናቆና ሰሌዳቸው ተነስቶ ከአገልግሎት ውጪ የሚሆኑም እንደሚገኙ ገልጸው፣ ሆኖም ሁለቱም ዓይነት ተሽከርካሪዎች በሥርዓቱ ተመዝግበው ወደ መረጃ ቋት የማስገባት ሒደት ላይ ሁነኛ መረጃ ማግኘት ለመሥሪያ ቤታቸው ፈተና እንደሆነበት ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ በ2014 በጀት ዓመት በተደጋጋሚ ጥፋት ያጠፉ 1,884 አሽከርካሪዎች ሥራ እንዲያቆሙ ተደርጓል ያሉት አቶ ጀማል፣ መንጃ ፈቃዳቸው ተነጥቆ ከነበሩት ከእነዚህ አሽከርካሪዎች ውስጥ 1,316 ያህሉ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ዳግም መንጃ ፈቃዳቸው መመለሱን አክለዋል።