የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑን ከዚህ ውጭ የሚደረግ ሌላው ጥረት ተቀባይነት እንደሌለው መንግሥት አስታወቀ፡፡
መንግሥት የተጀመረውን የሰላም ድርድር በፖለቲዊ መፍትሔ እንዲፈታ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለሰ ዓለም (አምባሳደር) በሳምንታዊ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሊሲንጎ ኦባሳንጆ የጀመሩት የአመቻችነትና የአደራዳሪነት ጥረት እንዲቀጥል የኢትዮጵያ መንግሥት ጽኑ እምነት አለው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አስፈላጊ ከሆነ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ልዩ መልዕክተኛውን የሚደግፍ የአፍሪካ ታዋቂ ግለሰቦች በአደራዳሪነት ቢካተቱ ኢትዮጵያ ተቃውሞ የላትም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ድርድሩ በየትኛውም ጊዜና ቦታ እንዲጀመር ፍላጎት እንዳላት የጠቀሱት ቃል አቀባዩ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይበረታታል ብለዋል፡፡
መንግሥት በትግራይ የመሠረታዊ አገልግሎት መጀመርን ለድርድሩ እንደ ቅድመ ሁኔታ እንደማያቀርብ ነገር ግን ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሌሎችም የአማራና አፋር ክልሎች አገልግሎቱ እንዲጀመር ይፈለጋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አገልግሎቱ እንዲጀመር በሚመለከታቸው አካላት በሚደረግ ጥናት መሠራት የፀጥታና ደኅንነት፣ እንዲሁም የሕግ ጉዳዮች ተፈትሸው ሌሎችን ለመሥራት ጊዜ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማንኛውም ቦታና በየትኛውም ሰዓት ለሰላም ድርድሩ ዝግጁ መሆኗንና ከአፍሪካ ኅብረት አመቻች ጋር አብሮ መሥራቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ሌላ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው መሆኑንና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ድርድሩ ቁርጠኛ ቢሆንም በተቃራኒው የሕወሓት ቡድን ለሰላም ድርድር ቁርጠኛ ካለመሆኑም በላይ ራሱን ለዳግም ጦርነት እያዘጋጀ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እንደታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ሁሉ የአፈሪካ ችግር በአፈሪካውያን መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለው ብለዋል፡፡