የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ምርጫ ጋር በተገናኘ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ፣ ክለቦችና የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ቅሬታውን ያቀረቡት አራት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና ሁለት የክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ላይ ያለው ቅሬታ እንዲሁም ቅሬታውን ተከትሎ በሊጉ ላይ ሊፈጠር ይችላል ያለውን ተግዳሮት አስመልክቶ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቴንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩን መግለጫው ተከትሎ፣ ቅሬታቸውን ያቀረቡት አራቱ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አዳማ ከተማ፣ ውልቂጤ ከተማ፣ ሀድያ ሆሳዕናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆኑ፣ ሁለት ክልል ፌዴሬሽኖች ደግሞ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገትና ልማት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያንቁ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ይሁንና አክሲዮን ማኅበሩ ከሰሞኑ በተለይም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ጋር አገናኝቶ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የአክሲዮን ማኅበሩን አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡