የባህር ዳር ስታዲየም ጨዋታ እንዲያስተናግድ ጊዜያዊ ፈቃድ አገኘ
በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በአፍሪካ የውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን)፣ ከሩዋዳ አቻው ጋር አንድ የደርሶ መልስ ማጣሪያ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሜዳው ውጪ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ይጫወታል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከዑጋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያርግም ይጠበቃል፡፡
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ቀደም ሲል ከደቡብ ሱዳን ጋር በታንዛኒያው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ባደረገው የደርሶ መልስ ጨዋታ 5ለ0 በሆነ ድምር ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ አልጄሪያ ለምታስተናግደው ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ፣ ከሩዋንዳ አቻው ጋር በሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ዕጣ ፈንታው ይወሰናል፡፡ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ከሜዳው ውጭ ነሐሴ 20 ከተጫወተ በኋላ፣ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ከደቡብ ሱዳን ጋር በተጫወተበት በታንዛኒያው ቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል፡፡
ቡድኑ ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ በሌላ ምድብ ማጣሪያ እያደረገ ከሚገኘው የዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር፣ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ መስማማቱ ታውቋል፡፡ ጨዋታው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ነሐሴ 12 እና 14 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ የዑጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከታንዛኒያ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከሜዳ ጥራት (ስታንዳርድ) ጋር በተገናኘ፣ በካፍ ዕገዳ ተላፎበት የነበረው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም፣ ለአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለሚደረጉ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ በሜዳቸው ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ጊዜያዊ ፈቃድ አግኝቷል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ በ2014 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ተከትሎ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ሲሆን እንዲሁም ፋሲል ከተማ ለአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡