Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

አገራችን በስንዴ ራሷን ከመቻል አልፋ ኤክስፖርት ለማድረግ ተስፋ የሰነቀችበት የኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻ በአመርቂ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በትንሹ በየአሥር ዓመት አንዴ በድርቅ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ ያጣ ወገናችን፣ ከስንዴ ተመፅዋችነት ተላቆ ለዓለም ገበያ የሚተርፍበት ዕድል የሚያገኝበት አጋጣሚ ሲፈጠር ይበል ማለት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ በመስኖ እርሻ ገፍታ ከሠራች በምግብ መትረፍረፍ እንደምትችል ዘንድሮ እየተመረተ ያለው 21 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እኔ ራሴ በአካል ተገኝቼ ካየሁዋቸው ተስፋ ሰጪ የልማት እንቅስቃሴዎች እንደተረዳሁት፣ ጠንክረን መሥራት ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደማሚ ውጤቶች እንደሚገኙ ጥርጥር አይኖርም፡፡ ይሁንና ይህ ልማት ሊሳካ የሚችለው አገር ሰላም ስትሆን ብቻ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከከንቱ ድርጊቶች በመራቅ ለአገራችን ዕድገት ከተረባረብን፣ ዓለምን የሚያስደንቅ ዕድገት እንደምናስመዘግብ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

 ትዝ ይላችሁ እንደሆን “ቢዮንድ ቦርደርስ” የሚባለው ፊልም በኢትዮጵያ ረሃብ ላይ ነበር የተሠራው፡፡ ይህንን ፊልም ባልሳሳት ለአምስት ጊዜያት ዓይቼዋለሁ፡፡ በተለይ በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በደረሰው ረሃብ የተጎዱ ወገኖቻችንን ለመታደግ የውጭ ዜጎች፣ ማለትም ክሊቭ ኦውንና አንጀሊና ጆሊ የተባሉ የፊልም ተዋናዮች የዕርዳታ ሠራተኞች ሆነው የተወኑበት ክፍል ሁሌም ይመስጠኛል፡፡ ማርቲን ካምቤል የተባለው የፊልሙ ዳይሬክተር የገዛ ረሃባችንንና ሞታችንን የሚያሳየውን ፊልም እዚህ አገር መጥቶ ለመሥራት ጥያቄ አቅርቦ በመከልከሉ፣ ፊልሙ ናሚቢያ ውስጥ ነበር የተሠራው፡፡ ይህ ፊልም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖቻችን የሚበሉት አጥተው በጠኔ ያለቁበትን መራራ ታሪካችንን በጨረፍታ የሚያሳይ ሲሆን፣ ድህነት ምን ያህል የእኛ የኢትዮጵያውያን መራር ጠላት መሆኑን ደግሞ በሚገባ ያስገነዝበናል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ድርቅና ረሃብ የማንነታችን መገለጫ እስኪመስሉ ድረስ አዋርደውናል፡፡ በኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ሳይቀር ረሃብ ለሚለው ፍቺ ኢትዮጵያ አገራችን በምሳሌ ተጠቅሳለች፡፡ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ረሃብን ሳናስወግድ የተሰጠንን ስያሜ ከዲክሽነሪው ለማስፋቅ ያደረግነው መፍጨርጨር መሳቂያ አድርጎንም ነበር፡፡ በተለይ አይሪሽ ታይምስ ላይ በመጻፍ የሚታወቀው ማየልስ ማየር የተባለ ዓምደኛ፣ ‹‹መጀመሪያ ረሃቡን አስወግዳችሁ ሌላውን ቀስ ብላችሁ ትደርሱበታላችሁ…›› ነበር ያለው፡፡ በ“ቢዮንድ ቦርደርስ” ፊልም ላይ እንዳየነው በዝናብ ዕጦት ምክንያት በረሃብ የረገፈው ሕዝባችን የመልካም አስተዳደር ችግርም ነበረበት፡፡ ወቅቱ የእርስ በርስ ጦርነት ስለነበር ሕዝቡ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ከመሆኑም በላይ፣ ፖለቲከኞች ለረሃብተኛው ሕዝብ ደንታ እንዳልነበራቸው ያሳያል፡፡

ያ ሁሉ መከራ አልፎ ኢትዮጵያ የ11 በመቶ ኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች ቢባልም፣ መከረኛው ሕዝባችን ግን ከጠኔ የሚያላቅቀው አላገኘም ነበር፡፡ በመሠረተ ልማት ዘርፎች ትላልቅ ለውጦች እየታዩ ነው፣  ከተሞች እያደጉ ናቸው፣ አርሶ አደሩ ሕይወቱ እየተለወጠ ነው፣ በከተሞች አካባቢ የሥራ አጥነት ችግር ቢኖርም ሰዎች ሥራን ካልናቁ በርካታ ዕድሎች አሁንም እየተፈጠሩ ነው፣ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ ሆስፒታሎችና ማኅበራዊ አገልግሎቶች እየተስፋፉ ናቸው ቢባልም ሕዝባችን ዛሬም ይርበዋል፡፡ የኑሮ ውድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዜጎችን እያሳሰበ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበት ሊረግብ አልቻለም፡፡ በየቀኑ በሸቀጦችና በአገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ አለ፡፡ ይህንን የማስተካከል ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ስለሆነ መንግሥት በሕዝቡ ኑሮ ላይ ተጨባጭ የሆነ ዕርምጃ ማምጣት አለበት እየተባለ ነው፡፡ ሌላው መረሳት የሌለበት በአሁኑ ጊዜም ሚሊዮኖች በግጭትና በድርቅ ምክንያት ዕርዳታ ጠባቂ ናቸው፡፡

ከችግሩ ጎን ለጎን ከ120 ሚሊዮን የሚበልጠው ሕዝብ በከፍተኛ መጠን ፍላጎቱ እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ወገብን ጠበቅ አድርጎ ልማት ላይ መረባረብ ግድ ይሆናል፡፡ ይህ ልማት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆንና ሕዝቡም የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ለማድረግ ትልቅ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዝርፊያ ባለበት ሥፍራ የሚበለፅጉት ጥቂቶች የሚደኸዩት ደግሞ ብዙኃን ናቸው፡፡ መልካም አስተዳደር በሌለበት የባለሥልጣናትና የሕዝቡ ግንኙነት የጌታና የሎሌ ዓይነት ይሆናል፡፡ የሰው ልጆች መብቶች ሳይከበሩ ሲቀሩ ዜጎች በገዛ አገራቸው ባይተዋር ይሆናሉ፡፡ ነፃነት ሳይሆን ጭቆና ይበረታል፡፡ ጭቆናና አፈና ባለበት ደግሞ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብት መናገር አይቻልም፡፡ በአገራችን በኢኮኖሚው መስክ ትልቅ መነሳሳት ቢታይም፣ በመልካም አስተዳደርና በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ረገድ ትልቅ እንከን እየታየ ነው፡፡ ሌቦች በየቦታው እየፈነጩ ነው፡፡ የእኩልነት ስሜት ሳይሆን በመገለል መከፋት እየበዛ ነው፡፡

ከላይ ለማንሳት እንደ ሞከርኩት ከስንዴ ልማቱ በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች እመርታዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ የስንዴ ልማት ሲባል ጀርባቸውን የሚያዞሩ ሰዎች መገንዘብ ያለባቸው፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተስፋ ያለው የአገር ልማት ላይ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ለከንቱ የፖለቲካ ዓላማ የሚባክነው ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ገበያ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ያለው ምናባዊ ዓለምና የገሃዱ ዓለም ኑሮ የተለያየ በመሆኑ፣ አፍና እጁን ማገናኘት የተሳነውን ወገናችንን ለልማት ለማሠለፍ ዕውቀታችንንና ክህሎታችንን እናዋጣ፡፡ ኢትዮጵያ በፈጣሪ የታደለቻቸውን የተፈጥሮ ፀጋዎች አልምተን ሳንጠቀም፣ እርስ በርስ በነገር መቋሰል የሚያተርፍልን ዕልቂትና ውደመት ብቻ ነው፡፡ ፈረንጆቹ የሚያከብሩን የልመና ከረጢታችንን ይዘን ስንዞር ሳይሆን፣ የተትረፈረፈ ምርት ይዘን ወደ ዓለም ገበያ ብቅ ስንል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አጉል መኩራራትና መወጠር ግብዝነት ነው፡፡ ግብዝነት ደግሞ የጥራዝ ነጠቅነት ምልክት ነው፡፡

(ዮናስ አምደ ማርያም፣ ከሪቼ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...