Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉባንኮቻችን ወዴት እየተጓዙ ይሆን?

ባንኮቻችን ወዴት እየተጓዙ ይሆን?

ቀን:

በአንዱ ነ.

የባንኪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአንድ አገር ዕድገት የደም ሥር ነው ይባላል፡፡ ይህም ማለት ለአንድ አገር ሕዝብ የተስተካከለ የገንዘብ ሥርጭትና ፍሰት በባንኮች አማካይነት ስለሚደረግ የተፋጠነ የግብይት ሒደት ከመፍጠሩ ባሻገር፣ በአገሮች መካከል የተነቃቃ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት አሌ የማይባል ነው፡፡ እንዲሁም ባንኮች የማይተካ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህ እውነታ በአገራችንም በመንግሥታዊና በግል ባንኮቻችን አማካይነት አጠቃላይ የአገራችን ዜጎች የባንክ አገልግሎቶችን ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ በተዘረጉ ቅርንጫፎቻቸው በኩል እንዲጠቀሙ ከማድረጋቸውም በላይ፣ ኅብረተሰቡንም ስለባንክ ጥቅሞች በማስተማር የማይተካ ሚና እያበረከቱ ስለሚገኙ ቁጥራቸው ይደግ ይመንደግ ያስብላል፡፡ በተጨማሪም የውጭ አገር ባንኮችም ወደ አገራችን ገብተው የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአሠራር ሥልጠት፣ የሰው ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ሽግግር ቢያደርጉ እኛም በዘርፉ ዓለም የደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ እንድንደርስ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ባንኮች በመደበኛነት ከሚያከናውኗቸው አንኳር ሥራዎች መካከል አንዱና ዋናው  ሀብት የማሰባሳብና የማሳደግ ሥራ ነው፡፡ ይህም የሚገለጸው ተቀማጭ ገንዘቦችን በቁጠባ መልክ፣ በተንቀሳቃሽ ሒሳብና በጊዜ ገደብ ተቀማጭ የሒሳብ ዘርፎች ዜጎች እንዲያስቀምጡ ዕድል በመፍጠር፣ እንዲሁም ጠንካራ ትስስር በማድረግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሐዋላ አገልግሎቶችን በመጠቀም ገንዘብን ከአንዱ የአገራችን ክፍል ወደ ሌላ በማስተላላፍ ዜጎች ገንዘብ በቀላሉ እንዲቀባበሉና  እንዲደርሳቸው የማድረግ ኃላፊነት የባንኮች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዱ ባንክ ከሌላ ባንክ የሚለየው ልኬት በሀብት ክምችትና መበላለጥ ሲሆን፣ በዋናነት አንዱ ባንክ ከሌላ ባንክ ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርገው ባንኮቹ የሰበሰቡት ወይም ያከማቹት የተቀማጭ ገንዘብ ሀብት መጠን ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባንኮች ዘወትር በአትኩሮትና ያለመታከት ሀብትን የማሰባሰብ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

- Advertisement -

ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት የተቀማጭ ሀብት ክምችት ነው፡፡ ተቀማጭ ሀብት ሲኖር ኢንቨስትመንት ይነቃቃል፡፡ ይህም ማለት በተጠና መልክ፣ ሀብት ሀብትን እንዲጨምርና እንዲተካ በሚያስችል ልዩ ሁኔታ፣ አዋጭ ዘርፎችን ነቅሶ  በማውጣትና በመለየት፣ ማለትም ተጨማሪ እስቶችን በሚጨምሩ ፕሮጀክቶችና የኅብረተሰቡን ችግሮች ሊፈቱ በሚችሉ መስኮች ላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የግል ድርጅቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ የልማት ተቋማትና በንግድ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች በሚያቀርቡት ፕሮፖዛሎች መሠረት፣ እንዲሁም ሕጋዊ ማዕቀፍ ሲኖራቸውና ሲያሟሉ ብቻ ባንኮች ከዜጎች የሰበሰቡትን ተቀማጭ ሀብት ሥልታዊ ጥናቶችን በማድረግ፣ የፕሮጀክቶቹ አዋጭነት በማገናዘብ፣ የአከፋፈል ሁኔታ በሚገባ ተዳሶ፣ የመክፈያ ጊዜ ተገምቶ፣ ተሠልቶና በበቂ ዋስትና ሲደገፍ ብቻ ማበደር ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ባንኮች የሚያበድሩት ገንዘብ ለባንኮቹ ለራሳቸው ኢንቨስትመንት ሲሆን፣ ከዜጎች በቁጠባ መልክ የሰበሰቡት ገንዘብ  ደግሞ ለባንኮቹ ብድር ወይም ዕዳ ነው፡፡  

የብድር አሰጣጥ ሒደትና መርህ መሆን ያለበትም ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ሊፈጠሩ ለሚችሉ ፕሮጀክቶች፣ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል የሚፈጠረውን  አለመጣጣም በአጭር ጊዜም ሆነ ከመካከለኛ እስከ ረዥም ጊዜያት ሊሞሉ በሚችሉ ዘርፎች፣ የግብርና ዘርፍን ለማዘመን ቀጥተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታሳቢ ተደርጎ ማለትም ሰፋፊና ሜካናይዝድ እርሻዎችን ለሚሠሩ ክፍሎች፣ የዜጎቻችንን የሁልጊዜ የቤት እጥረት ሊቀርፉ ለሚችሉ በመንግሥትም ሆነ በግል ባለሀብቶች ለሚለሙ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ከውጭ አገሮች የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት፣ እንዲሁም ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያዎች ለማቅረብ ለሚረባረቡ የኢንዱስትሪ ዘርፎች፣ የግብርና ምርቶችን በጥሬውም ሆነ አቀነባብረው ለዓለም ገበያ ለሚያቀርቡ ክፍሎች፣ ለአገርና ለሕዝብ ጉልህ አስተዋጽኦ ለሚያበረክቱ ፕሮጀክቶችና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ቢሆን በእጅጉ ይመረጣል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ በቂ ጥናትና መርህ ወደ ኅብረተሰቡ በባንኮች በኩል የሚረጩ ብድሮች፣ የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሱና የስግብግብ ነጋዴዎች ልዩ በረከት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

ለዚህ መጣጥፍ መንደርደሪያ የሆነኝ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የሚገኙ የግል ባንኮችን በአብዛኛው የሚመለከት ሲሆን፣ ባንኮቹም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለበላይ የሥራ ኃላፊዎችና ለሥራ አስፈጻሚዎች ብቻ ዓይነታቸውና ቁጥራቸው በዛ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ይከፍላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ በእንዲህ እንዳለ  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተተገበረ የሚገኘው ኮሜርሻል ሎን (Commercial Loan) በማለት እስከ ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም የግል ፍጆታ ብድር (Consumer loan) እስከ ሚሊዮን ብር የሚገመት እጅግ በጣም አነስተኛ በሆነ የወለድ ምጣኔ፣ እንዲሁም እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ የዕፎይታ ጊዜ (Grace period) ብድር እየሰጡ መሆኑን ልብ ለሚሉ አካላት በሙሉ ግርምትን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ፣ ሕጋዊ ጥያቄዎች እንዲነሱ በር የሚከፍት ሆኖ ይታያል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዓመታዊ ትርፋቸው ላይ ለሥራ አስፈጻሚዎቻቸው በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠሩ ማበረታቻ (በጉርሻ) መልክ እየከፈሉ መሆኑ፣ ሌላው አግራሞትን የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን ተከራይተው ወይም ገዝተው ወይም ገንብተው ለመኖሪያ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ይህም አልበቃ ብሎ ለብዙ ችግሮች መፍቻ ሊውል የሚችል የሕዘብ ገንዘብ ለጥቂት የባንክ ባላሥልጣናት በብድር መልክ የሚሰጥበት አኳኋንና የብደሩ አስፈላጊነት፣ በአነስተኛ የወለድ ምጣኔ እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት፣ የዕፎይታ ጊዜ ታሳቢ የተደረገበት ሁኔታ፣ የብድሩ ዓላማና ውጤቱ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በብድሩ አሰጣጥ (The Benefit Scheme) የበታች ሠራተኞች አለማካተቱ ጭምር ሊታይ የሚገባ ሲሆን፣ አግባብነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ 

የሠራተኞችን ጥቅማ ጥቅሞችን በተመለከተ የአገሮች ተሞክሮዎች የሚያስተምሩን ቁልፍ እውነታዎች ቢኖሩ፣ ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ ሠራተኞች በሚሠሩባቸው ድርጅቶች ውስጥ የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርባቸው ለማስቻል፣ የገቢ አቅማቸው እንዲደረጅ፣ በሥራና በአመራር ሒደት ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን በተግባር ላይ እንዲያውሉ በማሳብ  በአጠቃላይ (Highly engaged and Involved Work Force) እንዲኖራቸው ከመደበኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች በተጨማሪ  ያልተጣራ ትርፍ ማጋራት (Gain Sharing)፣ የተጣራ ትርፍ ማጋራት (Profit Sharing) እና እንዲሁም ጉርሻ መስጠት (Bonus Payment) የተለመደ መሆኑን ነው፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው የድርጅቶቻቸውን ምርታማነት ለማሳደግ ከመቻላቸውም  ባሻገር፣ የልዩ ልዩ ክህሎቶችና በፈጠራ የተካኑ ሠራተኞች እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል፡፡

የአገራችን ባንኮች ሁሉንም ሠራተኞች ሳያማክሉ ከዓለም ባንኮችና የንግድ ድርጅቶች አሠራር በተፃራሪ ለበላይ የሥራ ኃላፊዎችና ሥራ አስፈጻሚዎች የሚያደርጉት ጥቅማ ጥቅም በጤናማ የፉክክር ዕሳቤዎች ላይ ያልተመሠረተ፣ እንዲሁም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና በብዙኃኑ፣ በአስቀማጩ፣ በባለአክሲዮኖች ሀብትና ገንዘብ ጥቂት ግለሰቦች የሚበለፅጉበት ነው፡፡ የአገራችንን የብድር አሰጣጥ ደንቦችንና ሕግጋትን ያልተከተለ ከመሆኑም በላይ፣ የዋጋ ግሽበትን የሚያጋግልና በባንኮች መካከል  ተገቢ ያልሆነ  ፉክክር  እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን፣ ከጠቀሜታው ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን የብድር ዓይነት ወይም የብድር ጉቦ ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሌሎቹ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ሒደቱን በጥሞና እንዲመለከቱትና ከወዲሁ የዕርምት ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል በማለት ትዝብቴን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...