Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉድህነት ሰው ሠራሽ እንጂ የተፈጥሮ በረከት አይደለም

ድህነት ሰው ሠራሽ እንጂ የተፈጥሮ በረከት አይደለም

ቀን:

በሥዩም ተጫኔ

በአብዛኛው ሰዎች ስለድህነት ያላቸው ግንዛቤ ለኑሮ የሚያስፈልግ ገንዘብ አለመኖር እንደሆነ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ሆኑ የዓለም ባንክ ድህነትን ሲገልጹ ከሰዎች የቀን ገቢ አኳያ በማስላት ነው፡፡ “ደሃ” (ቅጽል) በቂ መተዳደሪያ የሌለው ሰው ይለዋል የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል አካዳሚ (በገጽ፣ 2006 ዓ.ም.)፡፡ ድህነት “ደህየ” ከሚለው ግስ የተመነዘረ ሊሆን ይችላል፡፡ በዓለም ባንክ የድህነት ወለል (Poverty Line) 1.90 የአሜሪካ ዶላር በታች የቀን ገቢያቸው ያላቸው ናቸው በማለት ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት በኢትዮጵያ 23 በመቶ ከአጠቃላይ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ይገኛል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ የሀብታሟ አሜሪካ አሥር በመቶ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዓለም አሁን ያለው ድህነት 36 በመቶ እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ አሥር በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ በመሆኑም ደሃ በሁሉም የዓለም አገሮች ይገኛል ማለት ነው፡፡ ደሃ የድህነት መገለጫ ውጤት ማለት ነው፡፡ የዓለም ባንክ የድህነት ወለል የሚያስቀምጠው በወቅቱ ያለውን ሁኔታ በመገምገምና የሰዎችን የቀን ገቢ በገንዘብ በማስላት ሲሆን፣ ይህም የሚያሳየው ድህነት ሒደትን ገላጭ መሆኑን ነው፡፡

በሌላ በኩል የፍልስፍና ሰዎች (በተለይ ከአውሮፓውያን አብርሆት ዘመን በኋላ) ድህነት ከአስተሳሰብ ችግር የሚመጣ ሰንኮፍ አድርገው ይገልጹታል፡፡ በዚህም የተነሳ የሰው ልጅ በድህነት ውስጥ ይወለዳል እንጂ፣ ድህነት በሰው ውስጥ አይወለድም በማለት ይገልጻሉ፡፡ እንደ ምክንያት ሲያቀርቡም ሰው ሲፈጠር ከሁሉም እንስሳት በአስተሳሰብ የላቀ እንደሆነና ተፈጥሮን መርምሮ ለማወቅ የሚያስችለው አዕምሮ ባለቤትነትን እንደተጎናፀፈ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ጸሐፊያን ሰዎች በግል ባላቸው የዕውቀት ብቃታቸው፣ ችሎታቸውና ተወዳዳሪነታቸው ተጠቅመው ከደሃ ምድብ በአጭር ጊዜ ወደ ሀብት መንደር ሊገቡ እንደሚችሉ የሚመሰክሩት፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሆኑም ከዚህ በመነሳት ድህነት የገንዘብ ማጣት ሳይሆን፣ የአስተሳሰብ ጉድለት እንደሆነ በርካቶች ያምኑበታል፡፡ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ ‹‹Poor and Rich Dad›› የሚባለው መጽሐፍ ደራሲ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ድህነት በጥበብና በጊዜ ሒደት በሚገኝ ተሞክሮ ዕውቀት ወደ ብልፅግና መንደር መቀላቀል እንደሚቻል፣ በሌላ በኩል ባለብዙ ገንዘቦች ከጥበብና ከዕውቀት በመፋታት፣ አለማወቅን ባለማወቅ ይሁን ወይም በስንፍና የተነሳ ወደ ደሃ መንደር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው በርካታ ገንዘብ በውርስ ወይም በሌላ ምክንያት ቢያገኝ ወደ ብልፅግና መንደር ተቀላቀለ ማለት አያስችልም፡፡ ገንዘቡ እንዴት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያፈራ ካላደረገ፣ ወደ ደሃ መንደር መመለሱ አይቀሬነትን የተረጋገጠ ነው ይላሉ፡፡ አንድ የልጅነቴን እውነተኛ ገጠመኝ ብነግራችሁ፣ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የሠፈራችን ደሃ ሰው 12,500 ብር (በወቅቱ በጣም ብዙ ብር ነበር) ሎተሪ ደረሰውና አዋዋሉና አመነዛዘሩ ሀብታም ለመምሰል በመሆኑ ገንዘቡ አለቀ፡፡ በመጨረሻም አንገቱን ለገመድ ሸለመና ዓለምን እስከ ወዲያኛው ተሰናበታት፡፡

 በሌላ በኩል የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ እንተውና የአገራችንን ብቻ ብንመለከት፣ በርካታ ሰዎች ከምንም ተነስተው ባለብዙ ገንዘብ ባለቤት ሆነዋል፡፡ በአገራችን ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት ፈር ያልያዘ በመሆኑ ከባለሀብት ይልቅ ባለብዙ ገንዘቦች በዝተው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ግን በጊዜ ሒደት ፈር መያዙ አይቀርምና ያኔ የቁርጥ ቀን ሊመጣል ይችላል፡፡ ስለዚህ ነው ድህነት አስተሳሰብ እንጂ ባለብዙ ቁልል ገንዘብ ባለቤት መሆን አይደለም የሚባለው፡፡ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ከሌሎች እንስሳት በመለየት እንዲኖር ሲፈቀድለት፣ አዕምሮውን በዕውቀት በማበልፀግም ይሁን በተሻለ አስተሳሰብ ማለፊያ ኑሮ እንዲኖርና ለቀጣይ ሕይወቱ ተስፋ እንዲሰንቅ ነው፡፡ ጥበበኛነት የሚቀጥለውን ዘመን መረዳት ነውና፡፡ የሰው ልጅ የተቀበለውን/የወረሰውን እንዳለ ባለበት ይሁን አናግቶ ማስተላለፍ አይደለም ግብሩ፡፡

በምዕራቡ ዓለም በተለይ የካታሊዝም መስፋፋት በኋላ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች/አቀንቃኞች የሰው ልጅ የኑሮ ዋነኛው መለኪያ የገንዘብ ክምችት በማድረጋቸው የተነሳ፣ የበርካታ ማኅበራዊ እሴቶች መፋለስ በዓለም ደረጃ ተፈጥሯል፡፡ የምዕራብ አገሮችም “እኔ ወይም የእኔ” አስተሳሰብ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ወደ ታዳጊ አገሮች (በተለይ አፍሪካ) መንፈሱ ሲገባ፣ ልክ እንደ ቫይረስ የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ሲሆን፣ አሳዛኝና አስገራሚ ማኅበራዊ መስተጋብር መቃወስ ለመፍጠር በመሞከር ላይ ይገኛል፣ ከሁለቱም ያልሆኑ ዜጎች እንዳንሆን፡፡

ባለፉት ዘመናት ማኅበረሰቡም ሆነ ማንኛውም ሰው ይመራበት የነበረው ማኅበራዊ ትስስርን/መስተጋብርን አጋምደው የያዙ የግብረ ገብ ሆነ የሥነ ምግባር እሴቶች በመሸርሸራቸው እንደሆነ በርካታ የሙያው ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡ ማንኛውም ሰው እንደ ሰብዓዊ ፍጡርነቱ የእኩይ ነገሮች ወዳጅ መሆን አይሻም፡፡ ለችግር መንስዔና ችግሩ የሚያሳስበውም፣ እንዲሁም ለመፍትሔውም የሚነሳሳውም ራሱ የሰው ልጅ ነው፡፡ በዚህ ዘመን እያንዳንዱ ቀን ከአዳዲስ ችግሮች ጋር ብቅ ይላል፡፡ በዚህ ዘመን በጥቅሉ ሲታይ ለሰው መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ችግርን መፍጠር የቀለለው ይመስላል፡፡ የኅብረተሰቡን ወይም የግለሰቦችን የማንነት ድንበር የሚወስነው፣ ከሌሎች በሚበልጥበት ቁሳዊ የሀብት መለኪያ ከሆነ ለማንነታችን ማነስ ወይም መዝቀጥ መቆሚያ ያሳጣናል፡፡

ሰው መቀበልን እንጂ መንጠቅን ከተመኘ ክፋትን ያነግሣል፡፡ የቁስ አስተሳሰብ በመንገሡ የሥራ ድርሻውን ከመቀበል ይልቅ ነጥቆ ባለብዙ ብር መሆን ነው በዚህ ዘመን የተከበረው፡፡ በሌላ በኩል በቅኝ ግዛት ዘመን የተወረሩ አገሮች ሕዝቦች ሠርተው በጥረታቸውና በችሎታቸው መበልፀግ እንደማይችሉ የሥነ ልቦና ቀውስ አላብሰዋቸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚሆኑት የአውስትራሊያ አቦርጅኖችና የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ አንድ ጋዜጠኛ በተለይ የብሪታንያ ተገዥዎች በዋናነት ያገኙት ዕውቀት “አይቻልም (Impossible)” እንደሆነ መረር በማለት ተናግሯል፡፡ ይህችም ነገር ወደ እኛም አገር አልተጋባችብንም ወይ? በየመሥሪያ ቤቱ ጎራ ሲባል፣ የሚሰጠው የዕለት ተዕለት መልስ “አይቻልም” ሲሆን መንግሥትም የመልካም አስተዳደር ችግር ብሎ የዳቦ ስም ሸልሞታል፡፡

በአገራችን በ1966 ዓ.ም. የፈነዳውን አብዮት በተረከቡት ተረኞች ወታደራዊ መንግሥት ታውጆ አብዮቱ ሁሉን ዜጋ እኩል ደሃ ከማድረግ በዘለለ፣ የማኅበረሰቡን የደለበ የአስተሳሰብ እሴት በማዛነፍ ይቅር የማይባል ጥፋት ለቀጣይ ትውልድ አስተላልፏል፡፡ ቀጥሎ የመጣውም መንግሥት ለ27 ዓመታት አሻሽሎ ቀጥሎበት ነበር፡፡ የአሁኑም በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹አይቻልም›› አስተሳሰብ በርትቶና ነጥቆ ባለብዙ ብር መሆን የተከበረ አድርጎታል፡፡

በ1950ዎቹ በአገሪቱ እየታዩ የነበሩት ሠርቶ የማሠራትና የማደግ ፍላጎት (እንዲህ ሲባል በወቅቱ ምንም በሕዝብ ላይ የደረሰ ችግር የለም ለማለት አይደለም)፣ በፈነዳው አብዮትና በቀጣይ በመጣው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የግል ስግብግብነት በማንገሥ በጋራ ከማደግ ጋር ኅብረተሰቡን አፋታው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በ2008 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ተከታታይ ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበች ቢሆንም፣ የዓለም ባንክና ብሉምበርግ የሚባል የቢዝነስ ጦማር ኢትዮጵያ በ1958 ዓ.ም. የነበረችበት የዕድገት ደረጃ ላይ ደረሰች ብለው ነው የዘገቡት፡፡ ምን ያህል ለ30 ዓመታት ከዕድገት ርቀን ብሎም ቆሞ ቀር እንደነበርን የሚያሳይ ይሆናል፡፡

በጣም የሚገርመው የፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሠራሁት የግንዛቤ ማዳበሪያ በመበረታታት፣ አጋሮቼ ተሸለሙልኝ ብሎ ነበር፡፡ ግን እውነት በአገሪቱ በማኅበረሰብ ዘንድ ሥነ ምግባር ያለው ሰው እንደ ብርቅ በሚታይበት ዘመን እንዲህ ዓይነት ዜና መስማት ህሊናን አይቆረቁርም? የሽወዳ ፖለቲካ፡፡ ይባስ ተሸላሚዎቹ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ከእነ ሽልማታቸው ከች ማለታቸው፡፡ ነውር የተሸለመባት አገር፡፡ በሽወዳ ፖለቲካ አገር ከድህነት መውጣት ትችል ይሆን?

ድህነት አስተሳሰብ እንጂ ደሃ መሆን አይደለም፡፡ ሰው በድህነት ውስጥ ይወለዳል እንጂ፣ ደህነት በሰው ውስጥ አይወለድም የሚባለው ለዚህም ነው፡፡ የሰው ጥረት በጥበብና በዕውቀት ሲታገዝ ወደ ብልፅግና ያመራል፡፡ በተመሳሳይ አገርም ሆነ ድርጅት በጥበብና በዕውቀት የታገዘ ጥረትን ስንቅ ያደረጉ፣ ብሎም ዘወትር ለመማር ዝግጁ የሆኑ ሰዎች ያለ ምንም ጥርጥር ወደ ብልፅግና ያቀናሉ፡፡

 የአፍሪካ አገሮች ከቀኝ አገዛዝ ነፃ ቢወጡም፣ አብዛኞቹ ከድህነት አስተሳሰብ መውጣት ስላልቻሉ አሁንም ደሃ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ይባስ ብለው የፈረንሣይ ቅኝ ተገዥዎች “የቅኝ ግዛት ግብር” በማለት ለፈረንሣይ በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡ ፈረንሣይም ሆነች ብሪታኒያ በቅኝ በተገዙ የአፍሪካ አገሮች እነሱን ከሚያመልክ መሪ በስተቀር በሥልጣን እንዲቀመጥ አይሹም፡፡ ከድህነት አስተሳሰብ እንዳይላቀቁ፡፡ አንድ ነገር ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አገርም ሆነ ድርጅት የሚያድገውና ወደ ተሻለ ደረጃ መለወጥ የሚችለው በቀና ልብና በጥበብ ሲመራ ብቻ ነው፡፡ ለአገራችን ድህነት ዋናው ምክንያት ምን ይሆን? ዋነኛው ቆሞ ቀሩና በጥላቻ የተተበተበው ፖለቲካችን ቢሆንም፣ የተማረው ዜጋ በአገር ዕውቀት (Soft-Knowledge) በምን ያህል የታነፀ ነው? የሥነ ምግባርና የሞራል ደረጃ ልኩ እንዴት ነው? በዚህ ሁኔታ የምንኖርባት ምድር የመኖር ምንጭ መሆን አትችልም፡፡ መኖር የሚወለደው ከሚኖር ቀና ልብ ነው፡፡ ልባችንን የሚያኖረው እውነተኛነት መሆኑን ልብ በሉ፡፡ መያዝ ብቻ በቂ አይደለም፣ የሚያዝ ያስፈልጋል፡፡ ስኬትን ለመያዝ የማያስይዝህን አጉል ወዳጅ ለእኩይ ጉዳይ እንድትጠመድ የሚያደርግህን ማንኛውንም ሰው መራቅ፣ የሥራና የአዘቦት ወዳጅን መለየት፣ የሥራ ወዳጅ አቅም ነው፡፡

በኢኮኖሚ ለማደግ መራመድ ያስፈልጋል፣ ለመራመድ መንገድና ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በመረዳት መንግሥት በርካታ የመሠረተ ልማቶች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ለመራመድ ከመንገድ ባለፈ ኢነርጂ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ኢነርጂ ዘርፍ ባለሙያዎች አባባል የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ዕድገት ከሌሎች አገራዊ የኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች (ግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት) በአምስት ዓመት ወይም 2.75 በመቶ አገራዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) ቀድሞ መገኘት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያሳየው የኤሌክትሪክ ኢነርጂ ችግር አለመቀረፍ አገራዊ ልማትን ሊያጓትት እንደሚችል ነው፡፡

ከዚህም አኳያ የአገራችን የኤሌክትሪክ ኢነርጂ በተቀመጠው ልክ ከሌሎች የኢኮኖሚ ልማት ቀድሞ ተራምዷል ለማለት ያስችላል ወይ? የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ አቅምን ከማሳደግ አኳያ እጅግ ተስፋ ሰጪ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በማሠራጫ መስመሮች በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እየታየባቸው ቢገኝም፣ ገና በርካታ ግንባታ እንደሚያስፈልጋቸው ያለው ሁኔታ ያሳያል፡፡ የማከፋፈያ መስመር (Distribution Network) ሲታይ በበርካታ ችግሮች እንዳሉበት ብዙ አመላካቾች ይመሰክራሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ገቢን ለማሳደግ የታሪፍ ማስተካከያ ቢደረግም፣ ካሉ የመደበኛ ሥራዎች ወጪና ብድር ከመክፈል አኳያ በቂ ነው ለማለት የሚያስችል አይመስልም፡፡ ሆኖም አገልግሎቱን ቀስፈው ከያዙት ችግሮች አኳያ የታሪፍ ማስተካከያ ማድረግ ብቻውን የሚሰጠው መፍትሔ፣ በውቅያኖስ ላይ ጠብታ ውኃ እንደ ማፍሰስ ያህል ነው ሊያስብል ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ገንዘብ ግለሰብንም፣ ድርጅትንም፣ ብሎም አገርን ሀብታም አያደርግም (የውጤት ስኬታማነትን አያላብስም) ማለፊያ የአስተሳሰብ ቁመና በቅድሚያ የተገነባ አዕምሮ ከተላበሰ ግን ገንዘብ ሀብታም/ውጤታማ ለማድረግ አጋዥ ነው፡፡

ለመሆኑ አገር አሁን ላለችበት ድህነት ምንድነው ምክንያቱ? ለምንስ ከድህነት መውጣት አቃታት? “ችግር እንደ ወራጅ ውኃ ያልፋል፤” ይላሉ የአገራችን ሰዎች፡፡ ግን ለምን አገር የድህነት ወዳጅ ሆነች? “ችግር” አስተሳሰብ እንጂ፣ በገሃዱ ዓለም ችግር የሚባል ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ዕውቀት ከጥበብ ጋር ስትገኝ በዚያ ዘንድ የሚቆም  ወይም የሚገኝ ወይም የሚኖር ችግር የለም፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው ቀዳማዊና ከባዱ ዕውቀት ደግሞ ራስን ብሎም ተቋምን በደንብ ማወቅ ነው፡፡ የአገር ድህነት መንስዔው ገንዘብ ወይስ አስተሳሰብ?

መቼስ የትኛውም ቤት ምንም ያህል ይተልቅ ቤቱን የሚያህል ቁልፍ እንደማያስፈልገው ሁሉ፣ ትልልቅ ችግሮችም ትልልቅ መልሶች ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ በአገሪቱ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ለፈለቁ ችግሮች በየወቅቱ መልስ ባለተራ አመራሮች መስጠት ባለመቻላቸው፣ አሁን የበረከቱ ችግሮች የአገሪቱን ምኅዳር ወረውታል፡፡ የአሁኑም ባለተራ ባደገበት የባህል ውቅር በወቅቱ መልስ ሰጠ ለማለት አያስችልም፡፡ እንግዲህ የአገር ምድር ፍሬ አልሰጥም ብላ ብትቆልፍ ልንገረም አይገባም፡፡

በአገራችን የእጥረትና አይቻልም አስተሳሰብ ነግሦ ይታያል፡፡ አገሮች ይሁኑ ድርጅቶች አስተማማኝና ዘላቂ ልማት ብሎም ዕድገት የሚያስመዘግቡ ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ በአሁኑ ዘመን በመሠረቱን የሰው ኃይሉ ዕምቅ አቅም እንደሆነ በብዙ አገሮች ታይቷል፡፡ በመሆኑም የዚህ ዓይነት የእጥረትና የአይቻልም አስተሳሰብ መሠረቱ እንዳይስፋፋና በማኮላሸት ዕውቀትንና ጥበብን በጋር አስተሳስሮ ችግርን በመቅረፍ፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት ማምጣት አይቻልምን? የሚቻለው በአገሪቱ አሁን የሚታየውን ኋላቀር ወይም ቆሞ ቀር የአስተሳሰብ ባህልና አሠራር በመቅረፍ፣ ድህነትን መቅረፍ የሚችል አቅም በመገንባት አይመስላችሁም?

በመሆኑም ለምሳሌ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደ ልማት ድርጅትነቱ ከዚህ ቀደም በአገራዊ የኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች የተመራበትንም ሆነ ኤሌክትሪክ ለማግኘት ፍላጎት ያላቸውንና የሚጠባበቁ ዜጎችንና ድርጅቶችን ተጠቃሚ ማድረግ አለበት፡፡ እስካሁን ያልተቻለበትን ውስጣዊ የሥራና የአሠራር ባህል ብሎም ውጪያዊ አላባዎችን በቅጡ መለየት፣ ከዚህም በዘለለ በአገራዊ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማተኮር በቀዳሚነት ለመደገፍ በተናጠልም ሆነ ከሌሎች ጋር በመቀናጀት በትኩረት መለየትና ማቀድ የሚገባበት ወቅት ላይ ይገኛል፡፡ ማንኛውም የድርጅቱ ዕቅድ ሆነ ትልም ከውስጥ ወደ ውጪ የተቃኘ መሆንም ይገባዋል፡፡

በድርጅቱ በውስጡ ያለውን የሰው ኃይል አቅምም ሆነ ወረት በቅጡ በመፈተሽ ብሎም በሙሉ አቅሙ በመጠቀም፣ በእጁ ያለ የተስፋ መክሊት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሰው ኃይሉ እንዴት ገንዘብ ሊፈጥር እንደሚችልም ሆነ ያሉትን ንብረቶች እንዴት ወደ ገንዘብ (ወረት) እንዲቀየሩ/እንዲፈጥሩ ማድረግ፣ እንዲሁም በራስ የመተማመን አቅም መጎልበት ይጠበቃል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱ ክፉ ክስተቶች የሰውን አዕምሮ በማንቃት የላቀ አመለካከት እንዲኖረው፣ ብሎም ችግሮችን የመፍታት ብቃት እንዲያዳብር የማድረግ አቅም አላቸው፡፡ የአሁኑ ሁኔታስ እንዴት ይሆን?

የሰው ልጅ መሆንን መውለድ የሚችል ዕምቅ በውስጡ እያለው፣ ግን ሰው የዓለም ባይተዋር ነው፡፡ ለዘመን የተሰጠ በዘመን የሚስተናገድ፡፡ ሰው በልቡ ያለውን ዘመን መለወጥ የሚችለው አንዳች ሳይሰጠን እንዳይለወጥ የራሳችንን ድርሻ እንወጣ፡፡ ድህነት ሰው ሠራሽ እንጂ የተፈጥሮ በረከት አይደለምና፡፡

ዕድገት በሌሎች ዘንድ ምንም ወይም የማይጠቅም ከሚባሉ ነገሮች የሚጠቅም የማየት አቅም ሲሆን፣ ድርጅትም ማደጉን ለማረጋገጥ አሁን በእጁ ካለው ሀብት በሚያገኘው የስኬት ትርፍ መጠን ነው፡፡ ጤናማ ውጤት ለማግኘት በየድርጅቱ የሚዘረጋው የውስጥ አሠራር ከሰው ተፈጥሮአዊ አሠራር ጋር መስማማቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ጤናማ አሠራር በሌለበት የሚገኙ ጤናማ ሰዎች፣ ንብረቶችም ሆኑ ማናቸውም ነገሮች ይባክናሉ፡፡ ጤናማ አሠራር ማንኛውንም ነገር ወደ ጥቅም ይቀይራል፡፡

በአጠቃላይ ከድህነት ለመውጣት ማለም ብቻ በቂ አይደለም፡፡ አዕምሮን ነገን በሚያማልል መንገድ ብቻ ማየቱ መድረስ አይደለም፡፡ ነፃ የወጣ ቀን የለም፣ የዘመን መንገድም ቀጥ ያለ አይደለም፡፡ አለመለወጥን የሚያስመኝ ማንኛውም ነገር መፈቀድ የለበትም፡፡ አዲሱን አሠራር አዲስ እንዲሆን አሮጌውን ማጥላላትም አያስፈልግም፡፡ የመሻገር አሠራር ትናንትን ሳያጥላላ መዝጋት የሚችል ነው፡፡ ትላንትን በአግባቡ በመዝጋት ነገን በአግባቡ መያዝ ያስችላል፡፡ የሚሠሩ ሥራዎችም ሆኑ የሚዘረጉ አሠራሮች ሁሉ ሰው ተኮር መሆን የድርጅት የራዕይ ዘር ፍሬ አፍርቶ ለነገ ወረት፣ አቅምና በርካታ ዘሮች በማበርከት አትራፊ ያደርጋሉ፡፡ የአሠራር ሥርዓታችን የሰው ኃይሉን ብቃት የምናወጣበት መሆን አለበት፡፡ እርስ በርስ በመማማርና ዕውቀትን ለመጋራት በሚያስችል መንገድ ማዋቀር የሰውን የተፈጥሮ ባህሪ ያማከለ ያደርገዋል፡፡

ትናንትና ዛሬን ማስናቅ የለበትም፡፡ ደንበኞች ትናንናን እያወደሱ ዛሬን እንዲያማርሩ ማድርግ ስህተት ነው፡፡ የድህነት ችግር ካስማጠ ለእሱ መላ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በሕይወት ዘመን ሁለቴና ከዚያ በላይ መክሰርን መልመድ ያመጣል፡፡ ለነገ ከድህነት የተላቀቀ የተሻለ ለውጥ ሲታለም፣ ማንኛውም ሰው በሕይወቱ የምክንያትና የውጤት ትስስር፣ ብሎም የመዝራትና የማጨድ ተዛማጅነት የተፈጥሮ ሕግን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ችግሩን ከመሠረቱ ለመረዳትና ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ፡፡

መድረስ የማድረስ ውጤት ነው፡፡ ለመድረስ ወቅትን ማወቅ አትራፊ ያደርጋል፡፡ በዘመን መገኘት ከዘመን መስተካከል ሲሆን መስተካከል ደግሞ በዘመኑ ማድረግ የሚገባህን ማወቅ ነው፡፡ በዘመን መንገድ ለመቀላቀል የወቅቱን አስተሳሰብ መድረስ ይገባል፡፡ ነገን በተሻለ የተለወጠ ለማድረግ፣ ልክ ነህ እንድትባል መጠበቅ ልክ አይደለም፣ ልክን ወዲያው መጠበቅም ልክ አይደለም፡፡ እናም ግንኙነትህን ቀላል ማድረግና የሐሳብን ዘር ለመዝራት መበርታት ያስፈልጋል፡፡

ቸር እንሰንብት!

 ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባልደረባ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...