Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ችግሮች በውይይት የሚፈቱ ስለሆኑ እኛ አድማ አናበረታታም›› ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት

ከ2001 ዓ.ም. አንስቶ ለሦስት ጊዜያት ተመርጠው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ነው፡፡ ለበርካታ መታት በዘለቀው አመራርነታቸው ማኅበሩን ለረዥም ጊዜ የመሩ ፕሬዚዳንት አድርጓቸዋል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በ1984 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ የመምህርነት ሙያን ተቀላቅለዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስተማር የጀመሩት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ከተቀጠሩበት ጊዜ አንስቶ የመምህራን ማኅበር አባል እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም የተቀበሉት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ 1997 ዓ.ም. በትምህርት ዕቅድና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ፣ በ2011 ዓ.ም. ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በትምህርት ፖሊሲና አመራርነት ይዘዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከአንድ ከግል የትምህርት ተቋም በመጀመርያ ዲግሪ በሕግ አጥንተዋል፡፡ ዮሐንስ (ዶ/ር) የሚመሩት ማኅበር በመላው ኢትዮጵያ በሁሉም ደረጃ ያሉ 700 ሺሕ መምህራንን በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 40 ሺሕ ያህሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው ይላሉ፡፡ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ከርመዋል፡፡ ከመንግሥት በኩል ያገኙት ምላሽ የማያረካ ሲሆንባቸው፣ እስከ አድማ መምታት የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስዱ በማኅበሮቻቸው በኩል ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ባስገቡት ደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ የየዩኒቨርሲቲ መምህራን የየራሳቸው ማኅበራት ያሏቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበር ሁሉንም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበራት ያቅፋል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ደግሞ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማኅበርን ጨምሮ ለሁሉም የመምህራን ማኅበራት እናት ነው፡፡ ሳሙኤል ቦጋለ ከእናት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር) ጋር ስለሰሞነኛው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጥያቄና ተያያዥ ጉዳዮች ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን በአንድ ላይ በማኅበሮቻቸው አማካይነት መንግሥት የደመወዝ ጭማሪና የዕርከን ዕድገት እንዲያደርግ፣ ካልሆነ እስከ አድማም መምታት የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል፡፡ መምህራኑ ይህንን ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ያደረሳቸው ችግር ምንድነው? ጥያቄያቸው እዚህ ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ ለምን ምላሽ አልተሰጣቸውም?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ጥያቄ ከዚህ በፊትም የነበረ ነው፡፡ የሚያያዘውም ከሥራ ምዘናና ደረጃ ማስተካከያ (Job Evaluation and Grading-JEG) ጋር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በየመንግሥት መሥሪያ ቤቶቹ ያለው የሥራ ምዘና የተዘበራረቀ፣ በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የደመወዝ ስኬል በጣም የተለያየ ነበር፡፡ መንግሥት ይህንን ሰብሰብ ለማድረግ በሚል ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የማስተካከል ፕሮጀክት ጀምሮ ነበር፡፡ ይኼ ፕሮጀክት ለረዥም ጊዜ ሲሠራ ቆይቶ 65 ገደማ የነበረው በ2011 ዓ.ም. 22 ደረጃ ያለው ምደባ ለመንግሥት ሠራተኞች ተፈቀደ፡፡ እኛ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በአጠቃላይም ሆነ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን በመወከል በዚህ ጉዳይ ላይ በንቃት ስንሳተፍ ቆይተናል፡፡ በ2011 ዓ.ም. ይህ የሥራ ምዘናና ደረጃ ይፋ ሲደረግ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የከፍተኛ ትምህርትና የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን ደረጃ አስተያየት እንዲሰጡበት ለትምህርት ሚኒስቴር ሲልክ፣ ቀድሞ የታየን የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን ደረጃ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደረጃ እኛ ሳናገኘው ወደ ታች ወረደ፡፡ የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን ደረጃ ለትምህርት ሚኒስቴር ሲቀርብለት አስተያየት እንድንሰጥ ተጠየቅን፡፡ ስናየው ግን ጥሩ ስላልነበረ በዚህ ደረጃ መውረድ የለብንም፣ ጥሩ አይደለም የሚል አስተያየት ሰጠን፡፡ ሚኒስቴሩ የእኛን ምላሽ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አቅርቦ፣ ኮሚሽኑ ያለንን አስተያየት እንድንሰጥ ጠየቀን፡፡ ከዚህ በኋላ ሦስት ጊዜ ክለሳ ተደርጎበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ደረጃው በተደጋጋሚ ሲከለስ የተደረገው ዋነኛ ለውጥ ምን ነበር?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- መምህራን እንደ የሥራ ላይ ቆይታቸው፣ የትምህርት ዝግጅታቸውና የሥራ አፈጻጸማቸው እየታየ የሚሰጣቸው የተለያየ ደረጃ አለ፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ጀማሪ መምህር፣ መምህርና ከፍተኛ መምህር እያለ የሚቀጥል ሆኖ በየደረጃው የደመወዝ ጭማሪ አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ላይ ደግሞ ረዳት ምሩቅ፣ ረዳት ሌክቸረርና ተባባሪ ፕሮፌሰር እያለ የሚቀጥል ባለሰባት ደረጃ ነው፡፡ የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን ደረጃ ዘጠኝ የነበረው ማሻሻያው ሲመጣ ዝቅ አደረገው፡፡ እኛ ይህንን ተቃውመን ብዙ ከተከራከርን በኋላ ደረጃውን ዘጠኝ አድርጎ ከመርጋት ይልቅ፣ ሰብሰብ አድርጎ ሰባት ማድረስ ይሻላል ተባለ፡፡ ይህም ደረጃው ዝቅ በመደረጉ ከታች መጨረሻ ላይ የነበሩት ደረጃቸውን ከፍ አድርጓቸዋል፡፡ ከላይ የነበሩት ደግሞ በደረጃ ዝቅ ቢሉም በፊት አሁን ደረጃ ሰባት ላይ ያለው የሚያገኘው ደመወዝ በፊት ደረጃ ዘጠኝ ከነበረው ይበልጣል፡፡ ይህ ደረጃ አሰጣጥ ከላይም ከታችም ያሉትን ይጠቅማል በሚል ተስማምተን ወደ ታች ወረደ፡፡

ይህ ሲሆን ግን ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የተዘጋጀውን ደረጃ ብዙም ምልከታ ሳያገኝ፣ በዚህኛው ላይ ያየነውን ችግር እንደ ያዘ ወደ ታች ወርዶ ሥራ ላይ ዋለ፡፡ በጊዜው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ወዲያው አስተያየት አልሰጡም፡፡ የአጠቃላይ መምህራንን ሲያዩ ነው ምላሻቸው መታየት የጀመረው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ የዲግሪ ምሩቅ መምህራን ደመወዝ ከዩኒቨርሲቲ ሌክቸረሮች ደመወዝ ከፍ ያለ ሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ በወረደው የሥራ ደረጃ 11,305 ብር ነበር የሌክቸረር ደመወዝ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ያለ ባለ ዲግሪ መምህር ደግሞ 12,500 ብር ገደማ ሲሆን፣ ማስተርስ ያላቸው ደግሞ ከ13,000 ብር በላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲ መምህራን ይህንነ ሲመለከቱ የሰጡት ምላሽ ምን ነበር?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- ይህ ልዩነት በዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ ቅሬታ ፈጥሮ በውይይት ላይ ስንገናኝ፣ በግልም እየመጡ ቅሬታቸውን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ይህ ደረጃ በ2012 ዓ.ም. መተግበር ጀምሮ በዓመቱ 2013 ዓ.ም. ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበራት ተፈራርመው 14 የሚሆኑ ጥያቄዎችን የያዘ ደብዳቤ አመጡ፡፡ ከጥያቄዎቹ ውስጥ አንዱ ከደመወዝ ክፍያ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ እኛ ይኼንን ጥያቄ በጊዜው ለነበረው ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርበን በሒደት ላይ እያለ፣ ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፈረሰ፡፡ 2014 ዓ.ም. ሲመጣ የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ በድጋሚ ዘግይቶብናል ብለው መጡ፡፡ በዚህኛው ግን የደረጃ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የትፍር ሰዓት፣ የተማሪዎች ምርምር ማማከርና መምህራን ሌላ ቦታ ሄደው ምርምር ሲያቀርቡ ያሉ የክፍያ ተመኖችና በሚቆረጥባቸው ግብር ላይም ጥያቄ አነሱ። የቤት ድጎማ ክፍያ ላይም አሠራሩ በየዩኒቨርሲቲው የተለያየ ሆኖ አንዱ ዘንድ ግብር ይቆረጥበታል፣ ሌላው ጋ አይቆረጥበትም፡፡ በዚህም ላይ ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መምህራኑ ለቤት ድጎማ ተብሎ ከሚከፈላቸው ባሻገር የቤት ባለቤት ለመሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ይህስ ከምን ደርሷል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በ2008 ዓ.ም. በፌዴራል ደረጃ በፀደቀ መመርያ የአጠቃላይ መምህራን በያሉበት ቦታ ኮንዶሚኒየም ወይም ለቤት ግንባታ የሚሆን መሬት እንዲሰጣቸው ተብሎ ወደ ክልሎችም ወርዶ እየተሠራበት ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በዚህ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ በጊዜው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስንነገጋር የሰጡን ምክንያት የዩኒቨርሲቲ መምህራን የተሻሉ ናቸው የሚል ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ሕንፃ ገንብተው በኪራይ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የመኖሪያ ቤት ድጎማ ክፍያ አላቸው የሚባሉት ነበሩ በምክንያትነት የቀረቡት፡፡ ለጊዜው የአጠቃላይ መምህራኑን እናስቀድምና የዩኒቨርሲቲዎቹን እንመጣበታልን የሚል ነበር ስምምነታችን፡፡ ግን በዚህ አሠራር ላይም ልዩነቶች መታየት ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ በአጠቃላይ ትምህርት ላይ ባልተለመደ ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ ለአጠቃላይ መምህራን የቤት ድጎማ ክፍያ ይፈጽማል፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማ አስተዳደሩ ቤት መስጠት ስላልቻለ ነው ይህንን ክፍያ የሚፈጽመው?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በ2001 ዓ.ም. የማኅበራችን 60ኛ ዓመት ሲከበር ኦሮሚያ ክልል ለመምህራን መሬት የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ ነው የቤት ጥያቄ በይፋ ለመንግሥት የቀረበው፡፡ በጊዜው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹በአዲስ አበባ ይህንን ለማድረግ እንቸገራለን፡፡ ነገር ግን ማኅበሩና ትምህርት ሚኒስቴር ሰነድ አምጥተው ሌሎቹም ክልሎች ላይ መተግበር ይችላል፤›› አሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ደግሞ ይህንን ወስዶ ወዲያው በትምህርት ደረጃ የተከፋፈለ የቤት ድጎማ ክፍያ የሚል አሠራር ዘርግቶ እያሻሻለ በዚያው ቀጠለ፡፡ በ2008 ዓ.ም. በሁሉም ክልሎች መሬት እንዲሰጥ ተፈቀደ፡፡ በአዲስ አበባም በ2009 ዓ.ም. ተፈቅዶ ወደ 5,000 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለመምህራን ተሰጥተዋል፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጉዳይ እንደሚታወቀው ነው፡፡ አንድ ጊዜ ዕጣው ወጥቶ አልቀጠለም፡፡ አሁን ግን በማኅበር ተደራጅቶ ቤት ለመሥራት ከተፈቀደላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱ መምህራን በመሆናቸው በጥሩ ሁኔታ ይሄዳል ብለን እናስባለን፡፡

በየክልሎች ደግሞ ለመምህራን የቤት መሥሪያ መሬት እንዲሰጥ ከተፈቀደ ጊዜ አንስቶ እስከ 2013 ዓ.ም. ባለን ሪፖርት፣ 110 ሺሕ መምህራን በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ አሁን ግን በሒደት ይካተታሉ የተባሉት የዩኒቨርሰቲ መምህራንም ይህንኑ ጥያቄ እያነሱ ነው። አሁንም እየተጠየቁ ካሉት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የመስጠት ሒደቱ አሁን ምን ይመስላል?  

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በሲቪል ሰርቪስ ባለሙያዎች የሥራ መዘርዝር በድጋሚ ታይቶ ሌላ የደረጃ ምዘና ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ረዳት ምሩቅ ሁለት፣ ረዳት ሌክቸረር፣ ሌክቸረር፣ ተባባሪ ፕሮፌሰርና ረዳት ፕሮፌሰር ደረጃዎች ተሻሸለዋል፡፡ የረዳት ምሩቅ አንድና የፕሮፌሰር ግን ከነበረበት ደረጃ አልተሻሻለም፡፡ ለፕሮፌሰር ደረጃ ቀድሞም በ2011 ዓ.ም. ላይ ማሻሻያ ሲደረግ ደመወዝ የተጨመረው 233 ብር ገደማ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን በትምህርት ላይ ያሳለፉ፣ እዚህ ለመድረስ ብዙ ጥናት ያሳተሙና ያማከሩ ናቸው፡፡ ውሳኔዎች ሲተላለፉ የአገር አቅም ከግምት ውስጥ የሚገባ ቢሆንም፣ እነዚህ ሰዎች ከዚህ ሌላ የገቢ ምንጭ የላቸውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ማስተርስ ያላቸው ሆነው በታወቁ ጆርናሎች ላይ ጥናታቸውን ያሳተሙ መምህራን ረዳት ፕሮፌሰር መሆን ይችሉ ነበር፡፡ አሁን በወጣው ደረጃ ግን ረዳት ፕሮፌሰር ለመሆን ሦስተኛ ዲግሪ ስለሚያስፈልግ፣ ማስተርስ ኖሯቸው ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑ መምህራን በአዲሱ ደረጃ የተቀመጠውን የደመወዝ ጭማሪ አያገኙም፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስናነጋግር የሚያነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ሰዎች በማስተርስ ደረጃ ረዳት ፕሮፌሰር የሚሆኑ ከሆነ ዶክትሬት ለመማር አይበረታቱም የሚል ነው፡፡ የትምህርት ዕድል ሲሰጣቸው ባለንበት ረዳት ፕሮፌሰር መሆን እንችላለን የሚሉ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይህንንና የረዳት ምሩቅ አንድና የፕሮፌሰር ደረጃ አለመሻሻሉን ጉዳይ ገና እየተወያየንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያነሷቸው ጥያቄዎች እስከ ነሐሴ ወር ምላሽ ካላገኙ በመስከረም ወር እስከ አድማ መምታት የሚደርስ ዕርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ይህንን እንዴት ያየዋል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- ችግሮች በውይይት የሚፈቱ ስለሆኑ እኛ አድማ አናበረታታም፣ ምክንያቱም ጉዳት አለው፡፡ ያሉንን ጥያቄዎች ሥራችንን እየሠራን በማቅረብ ከመንግሥት በኩል ምክንያታዊና የሚያሳምን ነገር ከመጣ እሱን እንወስዳለን፡፡ መንግሥት አሁን ካለው የኢኮኖሚ አቅምና ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንፃር አንድ ደረጃ ዕድገት ማድረግ ትልቅ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ምንም ምላሽ ካለማግኘት የተወሰነ ነገር ወስዶ ጥያቄ መቀጠል ስለሚሻል እኛም ይህንን ዝቅ አድርገን አናየውም፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎች የተዘበራረቀ የነበረውን የክፍያ ተመን ማስተካከል ጨምሮ የተመለሱ ጥያቄዎችም አሉ፡፡

አሁንም የቤት ድጎማ ክፍያና ሌሎች ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡ አገር መመለስ የምትችለውን እየመለሰች፣ ከአቅም በላይ የሆነው ደግሞ በይደር እየቆየ፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮም እየዳሰስን ምላሾች እንዲመጡ ማድረግ ነው የሚሻለው፡፡ ይህ ካልሆነ እንዲህ አደርጋለው የሚለው ለማንኛውም ወገን ጠቃሚ አይሆንም፡፡ በርካታ የአጠቃላይ ትምህርት፣ የቴክኒክና የሙያ መምህራን ጥያቄዎችን አስመልሰናል፡፡ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤትን በተመለከተ መሬት ውድ ነው፡፡ ሌላ ሰው ሲነሳም ካሳ ተከፍሎ ነው፡፡ ይህ በጣም ውድ ሀብት እንኳን ተፈቅዷል፡፡ በዚህ መንግሥትም መመሥገን አለበት፡፡ አሁን ይህ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን እንዲመለከት ግፊት እያደረግን ነው፡፡ ያለው ምላሽ አዎንታዊ ነው፡፡ ይህ ሲፈታ የታክስ ጉዳይ አለ፣ እሱም ከታክስ አዋጅ ጋር ተያይዞ ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ ለዚህም እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ ይህ ዕቅድ በሚቀጥለው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሮ በሁለት ዓመታት ውስጥ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህንን ዕቅድ እንዴት ታዩታላችሁ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- የራስ ገዝነት ጉዳይ ቀድሞም ቢሆን በአዋጁ ላይ የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ራስ ገዝነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለው ቀድሞ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በመጪው ዓመት በአዲስ አበባ ይጀመራል፡፡ እንቅስቃሴው ጅምር ላይ ስለሆነ ገና መጣራት ያለበት ነገር አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ግን የሚፈልጉት ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ የሚገኙ መምህራን የማስተማር ሙያ ሥልጠና (Post Graduate Diploma in Teaching – PGDT) ሳይወስዱ በሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አባላትስ እነማን ናቸው? ይህንን ሥልጠና ሳይወስዱ የሚያስተምሩ መምህራን አባል መሆን ይችላሉ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- ማኅበሩ አሁን 75 ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ አሁንም ሆነ በፊትም ያለው አቋም ለመምህርነት የሚመጥን የትምህርት ደረጃ፣ ብቃት፣ ክህሎትና የማስተማር ሥነ ዘዴን የሚያውቁ ግለሰቦች ብቻ ማስተማር አለባቸው የሚል ነው፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያለው አሠራር ነው፡፡ አንድ ሰው እንግሊዝኛ ስለቻለ ብቻ እንግሊዝኛ እንዴት ማስተማር እንዳለበት ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ ያንን ዕውቀት ለማስተላለፍ ሥነ ዘዴ (Pedagogical Skill) ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ይህንን ሥልጠና ሳይወስዱ ማስተማር የለባቸውም፡፡ ይህ ችግር ግን በግል ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት ትምህርት ቤቶችም እያጋጠመን ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የመምህራን እጥረት ሲያጋጥም በአፕላይድ ሳይንስ ተመርቀው ቁጭ ያሉ ተወዳድረው ከፍተኛ ነጥብ ያመጡት እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡ የተቀጠሩት ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ሥልጠና መውሰድ ሲኖርባቸው ቀጥታ ማስተማር እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ አሁን ግን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ለረዥም ጊዜ ስንነጋገርበት የነበረው ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ አለ፡፡ ከተመረቁ በኋላ የማስተማር ሙያ ሥልጠና (Post Graduate Diploma in Teaching – PGDT) ያልወሰዱ እንዲወስዱ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ሪፖርተር፡- በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ በእነዚህ ተቋማት ያስተምሩ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ መምህራንም ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ማኅበሩ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ላሉ መምህራን ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርጋል?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለተጎዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ትምህርት ሚኒስቴር መምጣት የሚፈልጉ እንዲያመለክቱ ጠይቆ፣ አመልክተው የተመደቡ አሉ፡፡ ያልመጡ፣ የመውጣት ዕድል የሌላቸው፣ ወይም መምጣት ያልፈለጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ፍላጎት ያላቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ግድ ተመድበው ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው፡፡

የአጠቃላይ መምህራንን በተመለከተ እኛ ዘንድ የመጣ ስም ዝርዝር አለ፡፡ ተፈናቅለው ለመጡ የምናደርገው ትንሽ ለታክሲ የምትሆን ድጋፍ አለ፡፡ ምደባ እንዲያገኙ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸውን ጠይቀናል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር እኔ የማስተዳድረው ትምህርት ቤት የለኝም፣ ትምህርት ቤቶች ያሉት በክልሎች እጅ ነው ብሎናል። ዞሮ ዞሮ በመፈናቀል የመጡ የ43 መምህራንን ስም ዝርዝር ለመንግሥት አቅርበን እንዲመደቡ ክትትል እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በ2010 ዓ.ም. የመንግሥት አመራር ለውጥ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትን ጨምሮ የትምህርት ዘርፍ ላይ ለውጦች እየተደረጉ ነው፡፡ የዘርፉ ባለድርሻ እንደሆነ አንድ አካል የሚደረጉትን ለውጦች እንዴት ትመለከቱታላችሁ?

ዮሐንስ (ዶ/ር)፡- የእነዚህ ለውጦች መነሻ ከ2007 ዓ.ም. ሲጠና የቆየውና በ2011 ዓ.ም. ለሕዝባዊ ውይይት የቀረበው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ከፍተኛ የአገራችን ምሁራንን ጨምሮ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍል በውይይት ተሳትፎበታል፡፡ ለአሥረኛ ክፍል ሲሰጥ የነበረው ብሔራዊ ፈተና መቅረቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ትንሹ የቆይታ ጊዜ አራት ዓመት መሆኑና የመሳሰሉት የዚህ ሪፎርም ውጤት ነው፡፡ ሥርዓተ ትምህርትም ተዘጋጅቶ ሙከራ እየተደረገ ነው፡፡ የመጻሕፍት ኅትመትም በሒደት ላይ ነው፡፡ የመምህራን ሥልጠና ላይም በርካታ ለውጦች አሉ፡፡ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያና የትምህርት ሕግ ማውጣት በሒደት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰነዶች የትምህርት ጥራትንም ለማሳካት አስፈላጊ ናቸው፡፡ እነዚህ ለውጦች መደረግ ያለባቸውና የሚበረታቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በዚህ በኩል ከፍተኛ ድጋፍ አለው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች