የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ አዲስ ቀረጥ ለመጣል የቀረበለትን ረቂቅ ደንብ በማፅደቅ ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል። እንዲጣል የተወሰነው ቀረጥ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ከተወሰኑ ዕቃዎች በስተቀር በሁሉም ወደ አገር በሚገቡ ዕቃዎች ተፈጻሚ የሚሆን ነው።
በኢትዮጵያ የተከሰተው ሁሉን አቀፍ የዋጋ ንረት 33 በመቶ በደረሰበትና የዋጋ ንረቱም እየቀጠለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አዲስ ቀረጥ መጣል የዋጋ ንረቱን እንደሚያባብሰው በርካታ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ቢሆንም፣ ቀረጡ የተጣለበት ዓላማን ምክንያት በማድረግ ገቢው ለታለመለት ዓላማ የሚውል ከሆነ መደገፍ የሚገባው እንደሆነ ይከራከራሉ። ‹‹ለመሆኑ አዲስ ቀረጥ መጣል ለምን አስፈለገ?›› የሚለውን ጥያቄና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳውን የዋጋ ንረት መባባስ ሥጋት በተመለከተ በመንግሥት የተሰናዳው ማብራሪያና አመክንዮ የሚከተለው ነው።
አዲስ ቀረጥ መጣል ለምን አስፈለገ?
መንግሥት ለትምህርት፣ ለጤናና ለሌሎችም የማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚያወጣው ወጪ ከአጠቃላይ በጀቱ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ እንደሆነ የደንቡ ማብራሪያ ያመለክታል። ይህ ሆኖ ሳለ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትንና ሌሎችንም የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መልሶ ለመገንባት እነዚህ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች ከኅብረተሰቡ ለሚቀርበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስፈልገው ወጪ የበጀት ፍላጎቱን በከፍተኛ ደረጃ እንዳናረው የደንቡ ማብራሪያ ያመለክታል።
በመሆኑም ይህንን የወጪ ፍላጎት አሁን እየተሰበሰበ ባለው የአገር ውስጥ ገቢ ብቻ ለማሟላት ስለማይቻል፣ በቀላሉና በአስተማማኝ ሁኔታ ገቢ ሊሰበሰብ የሚችል አዲስ የገቢ ምንጭ መፍጠር አስፈላጊ እንዳደረገው ማብራሪያው ያመለክታል፡፡ በመሆኑም ወደ አገር በሚገቡ ምርቶችና ዕቃዎች ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ እንዲጣልና በዚህ ቀረጥ አማካይነት የሚሰበሰበውን ገቢ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚፀድቀው በጀት መሠረት የትምህርት፣ የጤናና የሌሎችንም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወጪ መሸፈኛ እንዲውል መወሰኑን ያመለክታል።
የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ምጣኔና መሠረት
በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው በዚህ ደንብ ነፃ ከተደረጉት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች በስተቀር በሁሉም ዕቃዎች ላይ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የሚጣልና የሚሰበሰብ ይሆናል።
የቀረጡ ማስከፈያ ምጣኔ ሦስት በመቶ ሲሆን፣ ይህ ምጣኔም አነስተኛ የሚባል ከመሆኑ ባሻገር፣ አስመጪዎች ሳይሰማቸው ቀረጡን እንዲከፍሉ የሚያበረታታ እንደሆነ ያስረዳል። በደንቡ የተወሰነው የሦስት በመቶ ቀረጥ የሚጣለውም የዕቃው ዋጋ፣ የኢንሹራንስና የማጓጓዣ ወጪ (ሲአይኤፍ) ተሠልቶ በሚመጣው ድምር የዕቃው ወጪ ላይ እንደሆነ፣ ይህ መሆኑም የቀረጡ መጠን እንዳይንር እንደሚያደርገው የደንቡ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡
ይህንንም ሲያብራራ፣ አብዛኞቹ ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች ላይ የተጣሉ ቀረጥና ታክሶች ከዕቃው ዋጋ፣ የማጓጓዣና የኢንሹራንስ ወጪ በተጨማሪ ቀረጥና ታክስን በመጨመር የሚሰሉ መሆናቸውን ይገልጻል። ይህ በመሆኑም ከማስከፈያ ምጣኔያቸው ጋር ተደምሮ ጫናውን ከፍ የሚያደርጉት ሲሆን፣ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ግን ከዚህ አንፃርም ሲታይ ጫናው ቀለል ያለ እንደሆነና የዋጋ ንረት ተፅዕኖ እንደማያስከትል ያስረዳል፡፡
ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የተደረጉ ዕቃዎች
የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ የዕቃዎች ዋጋ መናርን እንዳያስከተል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ታስቦ ወደ አገር በሚገቡ የተለያዩ ምርቶች፣ እንዲሁም የተወሰኑ አስመጪዎች ከማኅበራዊ ልማት ከቀረጥ ነፃ ተደርገዋል። ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የተደረጉት ምርቶች ሱር ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች መሆናቸውን የፀደቀው ደንብ ይገልጻል።
ሱር ታክስ በሚጥለው ደንብ በተደነገገው መሠረት ወደ አገር የሚገቡ የተወሰኑ ዕቃዎች ላይ አሥር በመቶ ሱር ታክስ የተጣለ መሆኑን ይደነግጋል። ይህ አሥር በመቶ ሱር ታክስ የሚጣለውም ወደ አገር የሚገባው ዕቃ የተገዛበት ዋጋ፣ ዕቃውን ለማጓጓዝ የወጣው የትራንስፖርት ዋጋና የኢንሹራንስ ክፍያ (ሲአይኤፍ)፣ እንዲሁም የጉምሩክ ቀረጥ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስና እንደ ሁኔታው የኤክሳይስ ታክስ ከፍያ ተሠልቶ በሚገኘው ድምር ዋጋ ላይ የሚጣል ነው።
በመሆኑም ሱር ታክስ በሚከፈልባቸው በእነዚህ ዕቃዎች ላይ ተጨማሪ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ መጣል የዕቃዎቹን ዋጋ የሚያንር ብሎም የዋጋ ንረትን የሚያባብስ በመሆኑ ከታክሱ ነፃ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ደንቡ ይገልጻል። ሱር ታክስ ከሚከፈልባቸው ዕቃዎች በተጨማሪ ከማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ነፃ የተደረጉት አስመጪዎች የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው። እነዚህ አካላት ከአዲሱ ቀረጥ ነፃ የተደረጉት ኢትዮጵያ የቪዬና ኮንቬንሽን የተቀበለች አገር በመሆኗና ይህ ኮንቬንሽንም የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ከቀረጥ ክፍያ ነፃ እንዲሆኑ የሚያስገድድ በመሆኑ ነው።
የተጣለው አዲስ ቀረጥ የሚያስገኘው የገቢ መጠን
ከዚህ በላይ እንደተገለጸው የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ በሁሉም ገቢ ዕቃዎች የሚጣል ሲሆን፣ የታክስ መሠረቱ ሲአይኤፍ ይሆናል። ይህም መሠረቱ ሲአይኤፍ በሆነና ምጣኔውም ዝቅተኛ በመሆኑ ጫናው ዝቅተኛ እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሁሉም ዕቃዎች ላይ የሚጣልና ሰፊ መሠረት ያለው ስለሆነ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ይህንንም ለማሳየት ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው የገቢ ዕቃዎች የዋጋ መጠን፣ የማጓጓዣና የኢንሹራንስ ወጪን ጨምሮ ተዘርዝሯል።
በመረጃው መሠረት እ.ኤ.አ. በ2019፣ በ2020 እና በ2021 ወደ አገር የገቡ ዕቃዎች የዋጋ መጠን (የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላት ያስገቧቸው ዕቃዎችን ሳይጨምር) እንደ ቅደም ተከተላቸው 442.5 ቢሊዮን ብር፣ 482.6 ቢሊዮን ብርና 653 ቢሊዮን ብር ነው።
ይህንን መረጃ መሠረት በማድረግ ባለፈው ዓመት (በ2021) ወደ አገር የገቡ ዕቃዎች የዋጋ መጠን ላይ ሦስት በመቶ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ ተጥሎ ቢሠላ መንግሥት እስከ 19.59 ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያገኝ እንደሚችል ይጠቁማል። ወደ አገር የሚገባው የዕቃ መጠን በየዓመቱ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ በእነዚህ የገቢ ዕቃዎች ላይ ሦስት በመቶ የማኅበራዊ ልማት ቀረጥ እንዲጣል መደረጉ መንግሥት ለዜጎች የማኅበራዊ አገልግሎት በስፋትና በጥራት ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ገንዘብ (ፋይናንስ) ለማግኘት እንደሚያስችለው ታሳቢ መደረጉን አዲሱን ቀረጥ ከሚጥለው ደንብ ጋር አባሪ የተደረገው ማብራሪያ ያመለክታል።