Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአገር ኩራት የሆነው አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርት ይጠቀም

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ለመተካት በመንግሥት ደረጃ በተሠራ ሥራ ቢሊዮን የሚገመት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ስለማስቻሉ በቅርቡ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ከውጭ ይመጡ የነበሩ አንዳንድ ምርቶችን እዚሁ በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን በተደረገው ርብርብ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 56 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ምርቶችን እዚሁ ማምረት መቻሉን ይኼው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡  

ከውጭ ይገቡ የነበሩ አንዳንድ ምርቶችን እዚሁ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን ከተቻለባቸው ምርቶች ውስጥ ለአብነት የተጠቀመው የቢራ አምራቾች የሚጠቀሙበት ብቅል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለቢራ ፋብሪካዎች ለምርት ግብዓታቸው የሚጠቀሙበትን ብቅል ከውጭ ያስገቡ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህንን ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች መቋቋማቸው ለቢራ ማምረቻ የሚሆነውን ብቅል ከውጭ ለማስመጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ስለመቻሉ ተነግሯል፡፡ የብቅል ፋብሪካዎቹ ምርት መጠን አገር ውስጥ ፍላጎትን የሚሞላ በመሆኑም ከውጭ የሚገባ ብቅል ቀርቷል፡፡  

የብቅልን ያህል ትርጉም ያለው ለውጥ አይታይ እንጂ የውጭ ምንዛሪ ያስወጡ የነበሩ አንዳንድ ምርቶችንም በአገር ውስጥ ማምረት የተቻለበት ዓመት እንደነበር ይሄው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል፡፡ ደጋግመን እንደምንጠቅሰው ኢትዮጵያ በቀላሉ በአገር ውስጥ ማምረት የምትችላቸው በርካታ ምርቶች እያሉ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የሙጥኝ ማለት ‹‹በቃ!›› ሊባል እንደሚገባ ዛሬም ደግመን ማስታወስ እንወዳለን፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተወሰኑ የምርት ዓይነቶች ከውጭ እንዳይገቡ ለማድረግ ወስጄአለሁ ያላቸው ዕርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁንም ኢትዮጵያ በውጭ ምርቶች የተጥለቀለቀች መሆኑን ግን መካድ አይቻልም። እንደ ብቅሉ ሁሉ ከውጭ ማስመጣት ማቆም የምንችልባቸው ብዙ ምርቶች አሉ፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎቻችንን ደግሞ ለዚህ ማመቻቸት እንችላለን፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ አድርገን የምንጠቅሰው ኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህሉን ለማዳበር የሚያስችል ትልቅ አቅም አላቸው ተብለው ከሚታሰቡ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ 

አየር መንገዱ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገደኞችን በማጓጓዝ የሚታወቅ እንደመሆኑ መጠን፣ ለእነዚህ መንገደኞች የሚያቀርባቸው የተለያዩ ምግቦች፣ መጠጦችና አንዳንድ ቁሳቁሶች በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው ከውጭ ተሸምተው የሚገቡ ናቸው፡፡  

አየር መንገዱ በተወሰነ ደረጃ ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚጠቀማቸው አንዳንድ ምርቶች ቢኖሩም አብዛኞቹን የሚያስገባው ግን ከውጭ ነው፡፡ ለመንገደኞች የሚቀርቡ አንዳንድ ምግቦች ከውጭ የሚመጡ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ለዓለም አቀፍ በረራ ደንበኞቹ የሚቀርቡ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ሳይቀሩ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው መግባት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አፕል፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና የታሸጉ ጭማቂዎች ሳይቀሩ የውጭ ምንዛሪ ተከፍሎባቸው በገፍ የሚገቡ ናቸው፡፡ የታሸገ ቡናና ሻይ ሳይቀር በኢትዮጵያ የተመረቱ ያለመሆናቸው ነገር ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አየር መንገዱ በኢንዱስትሪው ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ እነዚህ የምግብ፣ የመጠጥና የሌሎች ቁሳቁሶችን ለመግዛት ያወጣው ውጭ ምንዛሪ ቢሠላ የትየለሌ ነው፡፡ ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ ደግሞ አብዛኞቹ እዚህ ሊገዙና በአገር ውስጥ ምርት ሊተኩ፣ እንዲሁም ሊዘጋጁ የሚችሉ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ያስቆጫል፡፡

በእርግጥ አየር መንገዳችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ በመሆኑ፣ መስተንግዶውም በዚያው ልክ መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ለደንበኞቹ የሚቀርበው ምግብና መጠጥ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ምግብ ለማዘጋጀት ጥራቱን የጠበቀ ግብዓት የሚያስፈልግ መሆኑም አይጠራጠርም፡፡ ስሙን ለመጠበቅ የሚያደርገው ጥንቃቄም የሚመሠገን ነው፡፡ ነገር ግን በቀላሉ በአገር ምርት የሚተኩ ምርቶችን ሁሉ ከውጭ ማስገባቱ ተገቢ አይሆንም፡፡ አየር መንገዱ የሚፈልጋቸው በርካታ ምርቶች እዚሁ አገር ውስጥ የሚመረቱ ቢያንስ ለመንገደኞቹ የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ ምግብና መጠጦች መግባት የለባቸውም፡፡ አየር መንገዱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ አድርጎ ከሚያስባቸው አንዳንድ ምርቶች የተወሰኑትን እዚሁ በአገር ውስጥ በሚገኝ ምርት ለመተካት ያደረገው ጥረት የለም ባይባልም፣ እየተጠቀመበት ካለው አንፃር አሁንም ብዙ የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደም ለምሳሌ እንደ መቂ ባቲ ያሉ ዩኒየኖች ለአየር መንገዱ አትክትል ለማቅረብ አድርጎት የነበረውን ስምምነት እናስታውሳለን፡፡ እንዲህ ያለው ስምምነት የአየር መንገዱ በአገር የሚመረተውን ምርት ተቀብሎ መጠቀም የሚችል መሆኑን ያሳያል፡፡ ሆኖም ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ፓፓዬ፣ ብርቱካን ሳይቀር አሁንም ከውጭ ይገባል፡፡ የታሸጉ ምግቦችም ከውጭ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በበረራ ወቅት ለመንገደኞች የሚያቀርባቸው ሙቀት ሰጪ አልባሳትን የውጭ ምንዛሪ አውጥቶ ከውጭ ከማስገባት ይልቅ ደረጃውንና ዘመናዊነቱን የጠበቀ ተመሳሳይ ምርት ከአገር ውስጥ መሸመት ይችላል። ይህንን ቢያደርግ ማስቀረት ከሚችለው የውጭ ምንዛሪ ወጪ ባለፈ የኢትዮጵያን የሸማ ጥበብ ኢንዱስትሪውን ያጎለብታል፡፡ የኢትዮጵያን የሸማ ጥበብም ለዓለም በማስተዋወቅ ሌላ ታሪክ መሥራት ይችላል። ስለዚህ አየር መንገዱ ለደንበኞቹ የሚያቀርብውን ምግብና መጠጥ፣ እንዲሁም አልባሳትን በዶላር ከመሸመት መላቀቅ አለበት። ሌሎች ምርቶችንም አሳማኝ ምክንያት ካልኖረው በቀር በውጭ ምንዛሪ በመገፍገፍ መሸመት የለበትም፡፡ ለመንገደኞች የሚሆን ምግብ የሚያዘጋጁ ብዙ ሆቴሎችና ምግብ ማቀነባበሪያዎችም አሉ፡፡ መቼም በውጭ የተመረተ ምግብ ካልሆነ አልመገብም የሚል መንገደኛ የለምና ጉዳዩ ሊታሰብት ይገባል፡፡ አንዳንዴ ነገሩን አስገራሚ የሚያደርገው፣ አየር መንገዱ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚላኩ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በካርጎ ጭኖ እያጓጓዘ፣ እንዳንዶችን ምርቶች መልሶ ከሌላ አገር ማስመጣቱ ነው፡፡ ለማንኛውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎቱ የምንኮራበትን ያህል የአገር አለኝታነቱን ለማስመስከር እንዲህ ያሉ ሥራዎች ላይም አተኩሮ ቢሠራ የበለጠ አለኝታነቱን ያሳይ፡፡ በሌላ በኩል የአገር ምርት የመጠቀም ባህሉን ለማዳበርም ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ለአርሶ አደሮቻችንም ጥሩ ገበያ ይፈጥራል፡፡ ገበያ የሚሹ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎቻችንም አዲስ ገበያ እንዲያገኙ ያግዛል፡፡ የአየር መንገዱ ሠራተኞች አልባሳት ግዥ አሁንም ድረስ ከውጭ የሚገባ መሆኑ ታውቆ ይህም መለወጥ አለበት፡፡ ጥራቱ እስከተጠበቀ ድረስ በአገር ምርት መጠቀም ከተቻለ ትልቅ ለውጥ ያመጣልና አዲሱ የአየር መንገድ አመራር በዚህ ጉዳይ ላይ ዕርምጃ ይወስድ ዘንድ ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት