ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን በማስመልከት በጉባ የተገኙት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው። ለመላው ኢትዮጵያውያን የ‹‹እንኳን ደስ አለን›› መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በሥራው በመረባረብ ላይ ለሚገኙም የላቀ ምሥጋና አቅርበዋል። አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ በፀና መሠረት ላይ ማቆምና ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑንም አሳስበዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን፣ በዕለቱ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ‹‹ዩኒት ዘጠኝ›› የሚባለው ነው፡፡ ሥራ የጀመረው ይህ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡
(ፎቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ)