Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሽብርተኞችን ሾተል በጋራ ከመመከት ውጪ አማራጭ የለም

በያሲን ባህሩ

       ሽብርተኞች በሃይማኖትም ሆነ በዘውግ ጥላ ይጠለሉ እንጂ፣ የፖለቲካ ጥገኞችና የሌላው የውጭ ጠላት (የእነ ግብፅ ዓይነቶቹ) ፈረሶች ናቸው፡፡ ግብራቸው የሚያስተሳስራቸው ሆኖ፣ በአቋራጭ ሊያተራምሱት በሚሹት አገርና አካባቢ የጥቅም መራኮት ላይ አተኩረውም ይረባረባሉ፡፡

       በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ከሰሜኑና የምዕራቡ ትርምስ የቀጠለው የአልሻባብና የሸሪኮቹ ‹‹የኢትዮጵያ ሙጃህዲን›› የተሰኘ፣ በውስጥ ማንነታችንና ሁለንተናችን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት እንደ ወረራና ግብረ ሽብር የሚቆጠረውም ለዚሁ ነው፡፡ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችንና በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምሳቸውን አግኝተው ኪሳራ ተከናነቡ እንጂ፣ ህልማቸው ይቋረጣል ብሎ መዘናጋት አይገባም፡፡

    ከመሰንበቻው አልሸባብ  የከፈተው  ውጊያ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን አሠላለፍ ወደ ምዕራብና ምሥራቅ ኢትዮጵያ በማዞር፣ የሠራዊታችንን አቅም ለማሳሳት የተሞከረ ግልጽ ቀመር እንደሆነ የሚናገሩ ተንተኞች አሉ።

      ቀመሩ የእነ አልሲሲና የኢትዮጵያዊው ከሃዲ ጁንታ ቡድን ግልጽ ሥሌት ነው። ‹‹ከአልሸባብ ጋርም ቢሆን እንደራደራለን›› በሚል ዓለም አቀፍ አሸባሪውን ቡድን በሹመታቸው ማግሥት በበጎ ዓይን ሊያዩት የከጀሉት የሶማሊያው አዲሱ ፕሬዚዳንትም፣ የቡድኑን ድርጊት ባላየና ባልሰማ በማለፍ ‹‹በእጅ መንሻነት›› ሊጠቀሙበት ስላለመቻላቸው ማረጋገጫ ማቅረብ ያዳግታል ይላሉ የቀጣናው ታዝቢዎች።

     ይሁንና ማንም የፈለገውን ዓይነት የሴራ ትወና ለመፈጸም ቢሞክር፣ ውስጣዊ ጥንካሬያችንና አንድነታችን የኢትዮጵያና የሕዝቧ ዋስትና መሠረት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን እስካለድረስ፣ የካይሮ-መቀሌ-ሞቃዲሾ ከንቱ የትስስር ድር በጀግኖቻችን ኃያል ክንዶች እስከ መጨረሻው ይተረተራል፣ ይከሽፋል የሚል አቋሙን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ክንድ የተሰኘው ማኅበረዊ ድረ ገጽ ነው፡፡

        ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያስረዳም የካይሮ-መቀሌ-ሞቃዲሾ የዱለታና የሴራ ትስስር ድር፣ ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ፈጽሞ ሊሳካ የሚችል አይመስልም በማለት ይጀምራል። አንደኛው አይበገሬው የአገር መከላከያ ሠራዊታችን ለምንምና ለማንም፣ በማንኛውም ጊዜና ቦታ (አቅጣጫ) ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ከምንጊዜውም በላይ የመጠበቅና የመከላከል፣ እንዲሁም የመደምሰስ አስተማማኝ ወታደራዊና ሥነ ልቦናዊ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው (አልሸባብ በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንና በጥምር የፀጥታ ኃይሎች የተደመሰሰበትን ቅፅበት ልብ ይሏል‼)፡፡

       ሁለተኛው ደግሞ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የሚገኘው ሕዝብ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነቷ ከመጡበት፣ ማንኛውንም መስዕዋትነት ለመክፈል የተዘጋጀ  በመሆኑ ነው። አዎ! ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶች ቢኖሩንም፣ በአገራችን ጉዳይ ውስጣዊ አንድነታችን ከብረት የጠነከረ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ አገራችንን በደፈረ ማንኛውም ኃይል ላይ “ሆ!” ብሎ የመዝመት ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን።

      ጥቂት ባንዳዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ ፈጽሞ አይደራደርም፡፡ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ እዚህ ላይ ካሰፈርኩዋቸው ጥቂት ሐሳቦች ብቻ በመነሳት፣ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ አማካይነት ያለችበትን ጊዜያዊ የፈተና ወቅት መገንዘብ አለበት። ራሱን ከጠላቶቻችን አሉባልታና የመከፋፈል እኩይ ሴራ በማራቅ፣ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል ሲል ሐሳቡን አስቀምጧል፡፡

     የአልሸባብና የግብረ አበሮቹ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙ  ኃይሎች፣ የቻሉትን እኩይ ነገር ሁሉ ለመከወን አሁንም ዳገት እየቧጠጡ መሆኑን ማሳያ ነው። ኢትዮጵያን አተራምሶ፣ ዜጎቿን በፅንፈኛ ብሔርተኝነትና በአክራሪ ኃይማኖተኝነት አባልቶና ጨፍጭፎ፣ አገር የመበተን ሴራቸውን ዕውን ለማድረግ ከሰማይ በታች ያሉትን ማናቸውንም እኩይ ድርጊቶች ያለመታከት እየከወኑ ነው ብሏል የኢትዮጵያ ክንድ።

       እነዚህ ተከታታይ የጥፋት ሙከራዎችና የፖለቲካ ሴራዎች ደግሞ ካይሮ ተቀምረው፣ በመቀሌ አልፈው እስከ ሶማሊያ የሚዘሉበት የጥፋት ቁርኝት ሰንሰለት በሁሉም ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ተግባራዊ እየሆነ ነው። የጠላቶቻችን ተወርዋሪ ድንጋይ አልሸባብ፣ ሰሞኑን በድንበር አቅራቢያ ሰርጎ በመግባት አምስት ትንንሽ የጠረፍ ከተማዎቻችን ላይ ወረራ የፈጸመውም፣ የዚሁ የካይሮ-መቀሌ-ሞቃዲሾ ትስስር ውጤት መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም።

      እንደ ውስጥ አዋቂው ማኅበራዊ ድረ ገጽ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሱዳን ጠረፎች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በወለጋና በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር፣ እነዚህ ኃይሎች ተቀናጅተው የሚያዳውሩት ግልጽና ሥውር ደባ ድር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ምንም እንኳን አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከፈለጉት አገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ መብታቸው ቢሆንም ቅሉ፣ በአሁኑ ጊዜ በፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋባዥነት ወደ ካይሮ ማቅናታቸው ‹‹ለምን በዚህ ወቅት?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያጭር አስገንዝቧል።

     ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኢጋድ ስብሰባ ወቅት በኬንያ ናይሮቢ  ከሱዳን የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልቡርሃን (ሌተና ጄኔራል) ጋር ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ውይይት በፈጠሩት ተፅዕኖ ሳቢያ፣ አንዳንድ የሱዳን ባለሥልጣናት (ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሕዝባቸው እየደረሰባቸው ያለውን ውግዘት ለመቋቋም ጭምር) ለዘብተኝነትን በማሳየት፣ ‹ከኢትዮጵያ ጋር በመጋጨታችን ምን እናተርፋለን?› የሚል ጥያቄ እያነሱ መሆናቸው ለእነ አልሲሲ ከባድ የራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

       ይህን ተከትሎም አልሲሲ አዲሱን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ‹‹የሱዳንን ሚና›› እንዲጫወቱ የራሳቸውን አውሮፕላን ሞቃዲሾ ልከው ወደ ካይሮ እንደ ጠሯቸው ተገማች ነው። በጉያዋ ውስጥ አሸባሪውን አልሸባብ የታቀፈችውና ከቡድኑ የሽብር ጥቃት ሕዝቧን እንኳን መከላከል ያልቻለችው ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ራስን በመከላከል መርህ›› (The Principle of Self-Defense) በአልሸባብ ላይ ዕርምጃ ብትወስድ፣ የሞቃዲሾ አስተዳደር በግብፅ በተሰመረለት መንገድ በመሄድ በቅጥፈት ‹ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቴን ጣሰች› የሚል እሪታውን ሊያሰማ፣ አሊያም እንደ ሱዳን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሊያነሳ የማይችልበት ምክንያት እንደማይኖርም ሥጋቱን አስቀምጧል።

       በአጭሩ የሞቃዲሾው አዲስ አስተዳደር በካይሮ ሳንባ እየተነፈሰ ሱዳን በተላላኪነት ስትፈጽም የነበረችውን ሁሉ ከመከወን ወደኋላ እንደማይል መገመት ብልህነት ነው፡፡ አልሳካ እያላቸው እንጂ እንደ አይኤስአይኤስ፣ አልቃይዳም ሆኑ አልሸባብን የመሰሉ ሽብርተኞች ዓላማ ከሰው አዕምሮ በላይ የሆኑ እጅግ ዘግናኝና አፀያፊ ዕርምጃዎችን በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ በመውሰድ፣ በሌላው ሕዝብ ልብ ውስጥ ፍርሃትና ሽብርን ማንገሥ ነው፡፡ በሃይማኖት ስም የተሸፈነ ድብቅ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በሕዝብ ላይ መጫን ብቻ ሳይሆን፣ እኛን በመሰሉ የብዝኃነት ማዕከላትም ትርምስን ማንገሥ ነው፡፡

     በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ ፈጽሞ ‹‹ይደረጋል›› ተብሎ የማይታሰብ እኩይ ድርጊት በመፈጸምና በማስፈጸም ለተቀረው ሕዝብ የ‹‹ወዮልህ›› መልዕክት ማስተላለፍና የሕዝብን ወኔ ከወዲሁ በመሰባበር የእነሱን የግፍ አገዛዝ ተንበርክኮ እንዲጠብቅና ጽንፈኞቹ ሲመጡ ጠመንጃውን ጥሎ እጁን ወደ ላይ ሰቅሎ የእነሱ መለያ የሆነውን ምልክት (ባንዲራ) አንጠልጥሎ እያውለበለበ፣ ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ!›› ብሎ ፍርኃት በወለደው ዕልልታ እንዲቀበል ማድረግ ዋነኛ ዓላማቸው ነው (እንደ አቅማቸውም በእኛም አገር ጁንታውና ኦነግ ሸኔ ይህን ሲያደርጉ ታይተዋል)፡፡

        እዚሁ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ውስጥ በቅሎ ቀጣናውን በሽብር የማተራመስ ቅዥት ያለው አልሸባብ የባሰበት ፀረ ሕዝብ ፍጡራን ስብስብ ነው፡፡ ሊዚህ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ቢቻልም በተደጋጋሚ ንፁኃን ሴቶችና ሕፃናትን እየቀላ፣ በአጥፍቶ ጠፊ እያወደመና የአገር ሀብት እያፈራረሰ ተስፋ ቆራጭነቱን በማሳየቱ፣ የሽብርተኝነትን ብቻ ሳይሆን የእነ አልሻባብን ጭካኔ ደረጃ ማሳየት ይቻላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያን ሙስሊም ወገኖችን በጭካኔ በመፍጀት የሚከሰስ ዓላማ ቢስ ስብስብ መሆኑ እየታወቀ ነው፣ መልሶ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ነፃ አወጣለሁ የሚል ድራማ የጀመረ ነው፡፡

       የሚገርመው ነገር ደግሞ አልሸባብን ጨምሮ ‹‹አሸባሪ›› የሚባሉ ድርጅቶች በሙሉ ሳዑዲ ዓረቢያ የምትከተለውን ሃይማኖት ዓይነት (ወሃቢያ) የሚከተሉ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ወሃቢያ›› የሚባለው ደግሞ በቁርአኑና በነብዩ (ሰዐወ) ንግግሮች ሱና/ሃዲስ ጽንፍ በወጣ መንገድ የሚተገብር ነው፡፡ በቁርአኑ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ ሰዎች በወላጆቻቸው፣ ይቅርና በሰው ልጅ ላይ እንዲጨክኑ የሚያስተምር አንቀጽ እንደሌለ ይነገራል፡፡ ቁርአኑ የሚያስተምረው ሰዎች ለፍጡራን ሁሉ እንዲያስቡና እንዲረዳዱ ነው፡፡

    ከኃጢያቶች ሁሉ የከፋ ሃጢያት ነው፡፡ ነውርና ሕገወጥነትም ነው፡፡ አረመኔነት ነው፡፡ ጨካኝነትም፡፡ እንኳንስ በሰዎች ዘንድ በአራዊት ዘንድ የሚደረግ አይደለምና፡፡ ጽንፈኛ አሸባሪዎች ግን ይህን ዓይነት ግፍና ጭካኔን ይፈጽማሉ፡፡ የእምነቱ መሠረት በሆነው በቁርአን ውስጥ ከተጠቀሰው መመርያ ውጪ ለፖለቲካ ዓላማቸው የሚረዳ እስከሆነ ድረስ የሚንቀሳቀሱ ሰው በላዎች ናቸው (እንኳን የሌላ እምነት ተከታይ የራሳቸውን ለዘብተኛና ሚዝናዊ አማኝ ለመግደል እንደማይመለሱም ደጋግመው አሳይተዋል)፡፡

     እንኳንስ የቅርባችን ፅንፈኛው አልሸባብ፣ የተዳከመው ኢስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) የሚባለው ዓለም አቀፍ ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድን ሲወስዳቸው የነበሩት ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ዕርምጃዎች ለእኛ አዲስ አይደሉም፡፡ ከእነ ሕይወቱ የቀበሩት፣ ዶሮ እንደሚጠበስ ዓይነት እግርና እጃቸውን የኋሊት የፊጥኝ አስረውና አንጠልጥለው እያገላበጡ በእሳት ያቃጠሏቸው፣ ውኃ ዳር አጋድመው ያረዷቸው፣ ከፎቅ ላይ ወርውረው የገደሏቸው፣ በጥይትና በአጥፍቶ ጠፊ ፈንጂዎች የፈጇቸው የሰው ልጆች፣ ወዘተ ብዙ የግፍ ድርጊቶች የተፈጸማባቸው መሆኑን እናውቃለን፡፡ ይህን ደግሞ ማን ታግሶ እንዲቀጥል ይፈቅዳል? በፍፁም፡፡

     እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ የአሸባሪዎች ዓላማ ሃይማኖት አለመሆኑ ነው፡፡ የጽንፈኞች ድርጊት በሙሉ ግቡ ሃይማኖት አይደለም፡፡ በየሥፍራው የሚካሄዱ ፀረ ሽብር ትግሎችም ዓላማ እስልምናን ከጽንፈኞች መዳፍ ማላቀቅና ማፅዳት ነው፡፡ የሽብርተኞች ሴራ ሃይማኖታዊ ሽፋን (ቅርፅ) ለማስያዝ በመሞከር እስልምናን ለማፍረስ ነው፡፡ ሽብርተኝነትን መታገል ማለት ደግሞ እስልምናን በቁርአኑና በሱናው መሠረት ንፅህናውን ጠብቆ እንዲዘልቅ ማስቻል ማለት ነው፡፡

      የአሸባሪዎቹ ተግባር ከቁርአኑም ሆነ ከሀዲሱ ያፈነገጠ በመሆኑ የእስልምና አስተምህሮትን የማይከተል ብቻ ሳይሆን የሚጥስ ጭምር ስለሆነ፣ አንድም ኢስላማዊ ጠረን የለውም፡፡ ስለዚህ ሽብርተኝነትን የምንታገለው ለዓለም ሰላም ያለውን አፍራሽ ተልዕኮ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን እስልምናን ራሱን ከመጠበቅ አንፃር ነው፡፡ ስለሆነም አገራችንም ከዚህ ቀደም እንደተንደረገው ጥሪው ‹‹ሽብርተኝነትን በመታገል እስልምናን እንጠብቅ›› የሚል ሊሆን ይገባል፡፡

      የእስልምና ጠላቶች ሌሎች ኃይሎች ሳይሆኑ በእስልምና ስም የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞች ናቸው፡፡ እስካሁን ባሉት የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚታወቀው የሽብርተኞች ተጠቂዎች በአብዛኛው ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ጽንፈኛው አይኤስ በሚንቀሳቀስበት በመካከለኛው ምሥራቅ በሶሪያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 250‚000 ሕዝብ ሕይወቱን አጥቷል፡፡ አሥራ አንድ ሚሊዮን ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አገሮች ተሰደዋል፡፡ በሙሉ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እኛም አገር ለልመና የመጡ ብዙ ናቸው፡፡

     የሺአ ተከታዮች ቢኖሩበትም የሱኒ ተከታዮች የጥቃቱ አብዛኛው ሰለባዎች ናቸው፡፡ ከሱኒዎች ውስጥ ደግሞ የወሃቢ መስመር ተከታዮች ይበዙበታል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ የጽንፈኛ ሽብርተኝነት አራማጅ የሆኑት የአይኤስ ተዋጊዎችም የሱኒ ወሃቢያ መስመር አራማጆች መሆናቸው ነው፡፡

        በአንድ ወቅት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 17 ቀን 2016 እዚያው ሶሪያ ውስጥ ዴር አል ኦዘር በተባለ ሸለቆ ሽብርተኞች ባደረሱት ጥቃት 400 ሰላማዊ ሰዎች ታፍነው ወደ ጽንፈኞች ዋና ከተማ ረቀአ ተወስደው 135 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 85 ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ንፁህና ሰላማዊ ዜጎች ናቸው፡፡ የሞቱትም ሆነ የቆሰሉት በሙሉ ሱኒ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በእኛም አገር በሃይማኖት መልክ አይሁን እንጂ በጉራፈርዳ፣ በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ በቄሌም፣ በቆቦ፣ በሁመራ፣ ወዘተ ብሔርን መሠረት አድርገው በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን እንዲያልቁ የተደረገበት መንገድ፣ በግብረ ሽብር የሚገለጽ የፅንፈኞች ተግባር ሆኖ የሚመዘገብ ነው፡፡

     ሽብርተኝነት ለራሱ አገር ዜጎች፣ ለራሱ ሃይማኖት (እስልምና) ለራሱ የአስተምህሮ መስመር (ሱኒ) ተከታዮች እንኳ ርህራሒ የሌለው ጨካኝና አረመኔ ድርጊት አራማጅ መሆኑን፣ በእነ አልሻባብ ተግባሩ እያስመሰከረ የሚገኝ ነው፡፡ ለሌላ አገር ሰው፣ ለሌላ ሃይማኖት፣ ለሌላ መስመር ተከታይ ጠብታ ርህራሒ ይኖረዋል ተብሎም አይታሰብም፡፡ ሊዚህም ነው ጀግኖቹ ቀደሙት እንጂ የምሥራቁ የአገራችንን ክፍል ሕዝብ  መከራ ደግሰውለት ነበር የሚያስብለው፡፡

     ሁኔታዎች ሁሉ እንደሚያረጋግጡት ከሽብርተኝነት ጋር የሚያደራድር አንድም ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ጉዳይ የለም፡፡ ሰላማዊ ሕዝቦች ያላቸው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ሽብርተኞችን የገቡበት እየገቡ ጠራርጎ ማጥፋትና የዓለምን ሰላም ማረጋገጥ፡፡ ወይም እጅን አጣጥፎ ሽብርተኞች የገባንበት እየገቡ ጠራርገው እስኪደመስሱን መጠበቅ፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ስለዚህ በቁርጠኛ አቋም ከመፋለም ውጪ ሌላ ዕድል የለንም፡፡

      ሽብርተኝነት ባዕድ የሆኑ አስተሳሰቦችን ይዞ የሚያራምድ በመሆኑ ለእስልምና ለራሱ ባዕድ ነው፡፡ ሥራው ሁሉ እስልምና የማያውቀው ነው፡፡ የሽብርተኞች ዓላማ በትክክለኞቹ ሙስሊሞች ዘንድ ዕውቅናም ሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ በአኅጉራችን አልሸባብ፣ ቦኮ ሃራም፣ አልኑስራ፣ ወዘተ የሚባሉ የዋናው ሽብርተኛ የአልቃይዳ ቅርንጫፎች ባተራመሱን ያህል ዳግም እንዳይነሳሱ መትጋት ይኖርብናል፡፡

    አልቃይዳ ደግሞ የአይኤስ ገባር ነው፡፡ ይህ ማለት እነዚህና ሌሎቹም በምሥራቅ፣ በምዕራብና በሰሜን አፍሪካና በየመን ያሉ አሸባሪ ቡድኖች በሙሉ የጽንፈኛው አይኤስ ዓላማ አራማጅና አስፈጻሚዎች ናቸው፡፡ በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውንና በቅርቡ ከግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ አገራችንን ለማጥቃት የሞከረው፣ አል ሸባብን መዋጋት ማለት ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን (አልቃይዳንና አይኤስ ጨምሮ) መዋጋት ማለት ነው፡፡

     የአካባቢያችንን የሽብር ኃይሎች መዋጋት ማለት ለዓለም ሰላም ታላቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊትም ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ኃይል ጋርም ሆነ ለብቻው በአልሸባብ ላይ እየፈፀመች የነበረችው ዘመቻ ዓላማው ሰፊና ጥልቅ መሆን ያለበትም ሊዚሁ ነው፡፡ ሕዝቡም በሙሉ አጋርነት አሸባሪዎችንና ሸሪኮቻቸውን መፋለም ይጠበቅበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles