Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከድርቁ መንደር

ከድርቁ መንደር

ቀን:

የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በአብዛኞቹ የዝናብ ወቅትን ተንተርሰው የሚዘሩ ናቸው፡፡ የዕለት ተዕለት ጉርሳቸውንም የሚያገኙት በዓመት የዝናብ ወቅት ጠብቀው ከሚያርሱት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይህ ደግሞ በተለይ በቆላማ የአየር ፀባይ ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች በይበልጥ ለድርቅና ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡

መስኖ ወይም ውኃ አቁሮ የመጠቀም ባህል ያልተለመደና የማይዘወተር በመሆኑ፣ ጊዜ እያፈራረቀ የሚከሰት ድርቅና መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እስከመፈናቀል ሲደርሱ ማየትም 40 ዓመታት የታሪካችን አካል ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ችግሩ ሲባባስም የያዙትን ሀብትና ንብረቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ መሸጥ፣ ለጋብቻ ያልደረሱ ሴት ልጆቻቸውን መዳርና ሌሎችም መፍትሔ የሚሉትን ዕርምጃዎች ለመውሰድ ሲገደዱ ይታያል፡፡

ለዚህም ማሳያ በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን  በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸው የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሦስት ክልሎች ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ ለፌዴራልና ለክልል ተቋማት ማድረሱ  ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን፣ እጥረቱ ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ ድርቁ በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

በሶማሌ ክልል በዘጠኝ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዲጋለጡ፣ እንዲራቡና ከብቶቻቸውም እንዲሞቱ አድርጓል፡፡

በባሌ ዞን በቆላና በደጋማ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱ፣ በዘንድሮ ዓመት ብቻ 400 ሺሕ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል፡፡ ድርቁ የተከሰተው በዞኑ በአምስት ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕርዳታ እያቀረቡ ቢሆንም፣ ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ዕገዛ የሚሹ ናቸው፡፡

ከኦሮሚያ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ በተገኘ መረጃ 25 ሺሕ ኩንታል ስንዴ አከፋፍሏል፡፡ የነፍስ አድን ሥራ ላይ የተሰማሩ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ድርቁ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየከፋ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በከብት ዕርባታ  የሚተዳደረው አርብቶ አደሩ እንስሳቱን አጥቷል፡፡ አርሶ አደሩም ለዘር የሚሆን እህል እጁ ላይ የለውም፡፡ ኢንተርናሽናል ሪስኪው ኮሚቴ እንደሚለውም ችግሩ አሥጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

የባሌ ዞን አምስቱ ወረዳዎች ላለፉት አራት ተከታተይ ዓመታት ከፍተኛ የዝናብ እጥረት ከገጠሙ ቦታዎች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን ችግሩም ሥር ሰዷል፡፡  

ከባሌ ዞን ከፍተኛ የቆዳ ስፋት የሚይዘው ቆላማ አካባቢው ሲሆን፣ ቦታዎቹ ዝናብ ካገኙ በቶሎ የሚመለሱና ከፍተኛ ምርት የሚሰበሰብባቸው ናቸው፡፡

በሌላ በኩል ድርቅ ከተከሰተባቸው የኦሮሚያ ዞኖች መካከል ጉጂና ቦረና ይጠቀሳሉ፡፡ በጉጂ ዞን የሰባ ቦሩ ወረዳ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ኃላፊ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደተናገሩት፣ በወረዳው 35,442 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

እነዚህ ዜጎች በድሬሳ በንሳ፣ ደጋላልቻ፣ ሰባሎሌማሞ፣ ኡቱሉ፣ ኦዴና ሐራጌሳ ቀበሌዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታም ያስፈልጋቸዋል፡፡

ለወረዳው አልፎ አልፎ የምግብ ዕርዳታ እንደሚመጣ፣ ነገር ግን ምግብ ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በወረዳዎች በረሃብ ምክንያት የሟቾች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የምግብና መሰል ዕርዳታዎች መቋረጣቸውንና ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጡንም ገልጸዋል፡፡ በወረዳው አስቸኳይ የምግብ እጥረት ቢኖርም፣ ትኩረት ሰጥተው የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን አለመኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በዚህም ረሃቡ ሥር የሰደደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጉጂ ዞን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ኦልኮ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በጉጂ ዞን ቆላማ አካባቢዎች ማለትም አምስት ወረዳዎች ውስጥ ድርቅ ተከስቷል፡፡

እነዚህ ወረዳዎች ከሶማሌ ክልልና ከቦረና ዞን ጋር የሚዋሰኑ ቦታዎች መሆናቸውን በመግለጽ፣ የዝናብ እጥረት ለረዥም ጊዜያት በመኖሩ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ዜጎች ብዙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በአምስቱ ወረዳዎች ውስጥ ከሚመረቱ ምርቶች አንዱ በቆሎ መሆኑን፣ በተያዘው ዓመት የተዘራው አዝዕርት እንዳልበቀለ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በጉሜ ኤልደሎ፣ ሊበን፣ ጎሮ ዶላ፣ ዋደራ፣ ግርጃ፣ ሰባቦሩ ወረዳዎችና አዶላ ሬዴ ቆላማ በሚገኙ ሰባት ቀበሌዎች ላይ ድርቅ መከሰቱንም ገልጸዋል፡፡

የቦረና ዞን ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጃርሶ ቀንጨሮ እንደተናገሩት፣ በዞኑ ለማምረት ከታቀደው 90 በመቶ በላይ ያህሉ ምርት ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ የዚህም ዋነኛው ምክንያት የተጠበቀው ዝናብ ባለመዝነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ሌላው ከፍተኛ ችግር በድርቅ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸው ሲሆን፣ በአብዛኛው አርብቶ አደሮች በመሆናቸው ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

መንግሥትን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርቶች ዕገዛ ቢያደርጉም ከችግሩ ስፋት አኳያ በቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ቦረና ዞን 13 ወረዳዎች፣ ጎጂ ዞን አምስት ወረዳዎች፣ ሶማሌ ክልል 11 ዞኖች በድርቅ የተጎዱ ሲሆን፣ አሁንም አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡

ድርቁ በኦሮሚያ ክልል ባሉ አሥር ዞኖች 3.7 ሚሊዮን ሰዎችን አደጋ ላይ የጣለ ሲሆን፣ የክልሉ አጎራባች አካባቢዎች ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 

በደቡብ ክልል በከንሶ ዞን በተከሰተው ድርቅ ያለፉት ወራት አሥራ ሦስት ሕፃናት መሞታቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ማስፈሩ ይታወቃል፡፡

ዞኑ በድርቅና በፀጥታ ችግር ምክንያት 190 ሺሕ በላይ ዜጎች ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡

ለሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅት ዝናብ ባላገኘው ኮንሶ ዞን፣ በቂ ምርት አልተገኘም፡፡ ከቦረና ዞን የሚጎራበቱ የኮንሶ ቀበሌዎች ድርቅ የተከሰተባቸው ሲሆኑ፣ በዞኑ አምራች የሚባሉ ቀበሌዎች ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል፡፡

በሚቀጥሉ ስድስት ወራት ከ190 ሺሕ በላይ የኮንሶ ነዋሪዎች ዕርዳታ የሚፈልጉ መሆናቸውንም የኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮው ጠቁሟል፡፡ አማሮ አካባቢም በተመሳሳይ በድርቅ ተጎድቷል፡፡

የዞኑ አመራሮችና የአካባቢው ተወላጆች ማኅበረሰቡን ለማገዝ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ዕርዳታ እየሰበሰቡ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 7.2 ሚሊዮን ዜጎች መራባቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሚያዝያ ወር ያወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ድርቅ ከተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከብቶች መሞታቸውንና ድርቁ በ40 ዓመታት ከታየው ሁሉ የከፋ ነው፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ማሳወቁ ይታወሳል።

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ መነሻው ባለፈው ክረምት ወራት ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነቡና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዝናብ አለመዝነቡ ቢሆንም፣ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ባሉት ወራት ውስጥ ዝናቡ አለመዝነቡ ጉዳቱን አባብሶታልም ብሏል።

በኬንያ ብቻ 1.4 ሚሊዮን እንስሳት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ቁጥራቸው በርከት ያሉ እንስሳት መሞታቸው ተገልጿል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...