Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግጭት ሰለባዎች

የግጭት ሰለባዎች

ቀን:

በአዲስ አበባ በስተሰሜን በ366 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የራያ ቆቦ ከተማ ወይናደጋ ስትሆን፣ አብዛኛው የቆዳ ስፋቷ የተሸፈነውም በተራሮች ነው፡፡ ይህች በተራሮች የተከበበች ከተማ፣ የምትሰጠው አገልግሎት ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡

ከተማዋ ለድንበር መውጫ ቅርብ ብትሆንም፣ የንግድ ዘርፍ ላይ አልተሠራም ማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም በቅርቡ በፌዴራል መንግሥትና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል በተፈጠረው ግጭት ከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደነበረችበት ቦታ ለመመለስ እያንሰራራች ነው፡፡ ከትግራይ ከአላማጣ በኩል የተፈናቀሉ ዜጎችን እየተቀበለችም ትገኛለች፡፡ ከወለጋ የተፈናቀሉትንም እንዲሁ፡፡

ሪፖርተር በጃራና በሃቡር መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን አነጋግሯል፡፡ ካነጋገራቸውም መካከልም ወ/ሮ ሐሊማ ይገኙበታል፡፡

በወለጋ በጊንቢ ወረዳ ቤተሰብ መሥርተው መኖር ከጀመሩ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ወ/ሮ ሐሊማ ሙሄ፣ በታጣቂዎች ምክንያት ይኖሩበት ከነበረው ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ወ/ሮ ሐሊማ እንደሚሉት፣ በታጣቂዎች ከተከፈተባቸው ተኩስ ለማምለጥ ልጆቻቸውን ጫካ ይዘው ቢገቡም፣ ባለቤታቸውን ግን ታጥቆ በመጣው አሸባሪ ቡድን አጥተዋል፡፡

በወቅቱም ለ30 ዓመታት ያፈሩት ንብረት በታጣቂ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን፣ ልጆቻቸውን ለማዳንና ሕይወታቸውን ለማትረፍ በሚሯሯጡበት ጊዜ ታጣቂ ቡድኑ ሦስት ጊዜ ተኩሶ አካላቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ገልጸዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑም ባልታሰበ ሁኔታ ወረዳው ውስጥ በመግባት የአማራ ተወላጆችን እየመረጠ ጭፍጨፋ ማድረጉን፣ በወቅቱም የእርሻ ሰዓት ስለነበር ባለቤታቸውም ሆኑ እሳቸው እርሻ ላይ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡

የታጠቀው ቡድን ለረዥም ሰዓት ተኩስ መክፈቱን፣ በአካባቢው የሚኖሩ የአብዛኞቹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ንብረት ከመውደም አልፎ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ሊቀጥፍ እንደቻለ አስታውሰዋል፡፡

ታጣቂው ቡድን ሦስት ጊዜ ተኩሶ ሰውነታቸው ላይ ጉዳት ባደረሰባቸው ወቅት ከስምንት አስከሬን መካከል ራሳቸውን እንዳገኙት የሚናገሩት ወ/ሮ ሐሊማ፣ የተጎዱት እግራቸው፣ እጃቸውና ንፍፊታቸው አካባቢ በመሆኑ ሕይወታቸው ሊተርፍ መቻሉን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡  

ጉዳቱ ከደረሰባቸው በኋላ በወቅቱ ከታጣቂ ቡድኑ ተርፈው ወደ ጫካ የሚያመልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይዘዋቸው ወደ ጫካ እንደገቡ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱም የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ብዙ ደም እንደፈሰሳቸው፣ ከብዙ ትግል በኋላ ከደብረ ብርሃን አለፍ ብለው ሃቡር በሚባል የተፈናቃዮች ማዕከል ከልጆቻቸው ጋር ሊጠለሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ከልጆቻቸው ጋር በሚገኙት መጠለያ ማዕከል የደረሰባቸውን ጉዳት ለማስታመም በቂ የሆነ ሕክምና እያገኙ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የደረሰባቸው ጉዳትም ከፍተኛ ስለሆነ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንኳን እንዳልቻሉ፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውም ምን እንደሚሆን ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ማዕከሉም በቂ የሆነ ነገር እንደማያገኙ፣ በተለይም የሰው ልጅ ከሚያስፈልገው መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ የተሟላላቸው ነገር ባለመኖሩ እክል እንደገጠማቸው አስረድተዋል፡፡

ንብረቶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በታጣቂ ቡድን ካጡት መካከል ወ/ሮ ፈቲያ መሐመድ አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ፈቲያ በወለጋ በጊንቢ ወረዳ ከአምስት ልጆቻቸው ጋ ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ በአንድ ጀንበር ንብረታቸውን በማቃጠልና በማውደም ከቀዬአቸው እንዳፈናቀላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ፈቲያ፣ በወለጋ ላይ ለተፈጸመው በደል መንግሥትን  ኮንነዋል፡፡

በብዙ ድካም ያፈሩት ንብረት በአንድ ጀንበር ሙሉ ለሙሉ መውደሙና በተለይም በአካባቢው ላይ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በታጣቂ ቡድኑ መጨፍጨፋቸው አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ በዘር ማንነት ላይ ያተኮረ ጭፍጨፋ ማድረጉን የተናገሩት ወ/ሮ ፈቲያ፣ ጭፍጨፋውን ባካሄደበት ወቅት ልጆቻቸውን ይዘው ጫካ ገብተው ማምለጥ እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ጭፍጨፋው በሚካሄድበት ወቅት ታጣቂ ቡድኑን ለማቆም አንድም የፀጥታ አካል በቦታው አለመምጣቱን፣ በተቃራኒው የዚህ ቡድን ጎራ ሊሆኑ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊትም እንዲህ ዓይነት ጥቃት መፈጸሙን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ማሳደግ እንደከበዳቸው አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታጣቂው ቡድን ባደረገው ጭፍጨፋ አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪ ከሞቀ ጎጇቸው መፈናቀላቸውን፣ እሳቸውም የዚሁ ዕጣ ፈንታ ተቋዳሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ታጣቂ ቡድኑ ባደረሰው ጭፍጨፋም ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እንደወጡና በአሁኑ ወቅትም በሃቡር መጠለያ ልጆቻቸውን ይዘው መቀመጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በመጠለያ ካምፕ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ ችግር እንዳለ፣ በተለይም ሕፃናት ልጆች ለተለያየ በሽታ እየተጋለጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ ነገር እንኳን እንደሚያጡ አስታውሰዋል፡፡

መንግሥት ይህንን ችግር ተረድቶ አፋጣኝ የሆነ ዕርምጃ እንዲወስድና መፍትሔ እንዲያበጅላቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አላማጣ አካባቢ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው የመጡት አቶ ንጉሤ አራርሳ እንደገለጹት፣ ሕወሓት የአላማጣ ሕዝብ ላይ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጭቆናዎችን ፈጽሟል፡፡

‹‹የራያ ሕዝብ በማንነቱ የተነሳ ብዙ ሥቃይ እየደረሰበት ነው፤›› የሚሉት አቶ ንጉሤ፣ ‹‹ሕዝቡ ንብረቱ እየተወሰደ ላልተፈለገ እንግልት እየተዳረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተለይም ብሔር ተኮር የሆነ እንግልት እየደረሰበት መሆኑን፣ በዚህም የተነሳ በርካታ የራያ ተወላጆች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ንጉሤ አምስት ልጆቻቸውን ይዘው ሜዳ ላይ መበተናቸውን፣ የአማራ ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ምንም ዓይነት ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በጃራ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ፣ በመጠለያው ኑሯቸውን ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ የሰው ልጅ የሚያስፈልገው ነገር ተሟልቶላቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡

በመጠለያው አብዛኞቹ ሕፃናት ልጆች እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ንጉሤ፣ ከዚህ በፊት ኑሮን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሕወሓት ቡድን ንብረታቸውን በመዝረፍና ከሞቀ ጎጇቸው እንዲወጡ በማድረግ ቤተሰቦቻቸው ሜዳ ላይ እንዲበተኑ አድርጓል ብለዋል፡፡

‹‹አሁንም ቢሆንም መንግሥት ንብረታችንን ያስመልስ፤›› የሚሉት አቶ ንጉሤ፣ ይህ ካልሆነ ግን የራያ ሕዝብም በአንድነት በመቆም መብቱን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡  

ከአላማጣ ከተማ ከ02 ቀበሌ የመጡት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ አባት እንደተናገሩት፣ ሕወሓት ባደረሰባቸው ጉዳት የተነሳ ከ32 ዓመት በላይ ያፈሩትን ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቤተሰብ አፍርተው የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ የተናገሩት እኚህ አባት፣ በአንድ ውድቅት ሌሊት ንብረታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም መንግሥት ለጉዳዩ ምንም ዓይነት ትኩረት አለመስጠቱ እንዳሳሰባቸው፣ የራያ ሕዝብ አሁንም ቢሆን የማንነት ጥያቄን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየኖሩበት የሚገኘው ቦታ ምቹ አለመሆኑንና መኖር ቀርቶ ለአንድ ደቂቃ ያህል ለመቆም ከባድ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ብለዋል፡፡

በመጠለያውም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የራያ ሕዝቦች መኖራቸውን፣ ተገቢውን ያህል ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ባለመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ሲሉ እኚህ አባት አስረድተዋል፡፡

‹‹ሕፃናት ልጆች፣ ወጣቶችና አረጋውያን የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤›› የሚሉት እኚህ አባት፣ ከዚህ በፊት ይኖሩበት ከነበረው ቦታ ተፈናቅለው ከመጡ ስድስት ወራት ማስቆጠራቸውን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥም የሰው ልጅ በቀን ማግኘት የሚገባውን ነገር እንኳን እያገኙ አለመሆኑን፣ በተለይም ሕፃናት ልጆች ለተለያዩ በሽታ እየተጋለጡ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከአላማጣ ከተማ ከሞቀ ጎጆዋ ተፈናቅላ የምትገኘው አንድ ስሟ እንዳይጠቀስ የምትፈልግ እናት እንደተናገረችው፣ ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሴት ልጆች ተደፍረዋል፡፡

‹‹ሴትና ሕፃናት ልጆችን መርጦ በመድፈርና በማሰቃየት እኩይ ተግባራትን ፈጽሟል፤›› የምትለው እናት እሷም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ መሆኗን አስረድታለች፡፡

በመጠለያው እሷን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በሕወሓት ልዩ ኃይል መደፈራቸውን፣ በዚህም የተነሳ ለተጓዳኝ በሽታ መጋለጣቸውን አስታውሳለች፡፡

የሕወሓት ኃይል ከተደፈረች በኋላ ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ጣቢያ መሄዷንና በቂ ክትትል እንደተደረገላት ተናግራለች፡፡

በአሁኑ ወቅትም በመጠለያው ውስጥ ከገባች አምስት ወራት እንደሆናት፣ የሴት ልጅ ንፅህና መጠበቂያም በአግባቡ እየተሰጠ ባለመሆኑ አብዛኞቹ ሴቶች ከባድ ችግር ውስጥ ገብተዋል ብላለች፡፡

መንግሥት ለችግሩ አፋጣኝ ዕልባት እንዲሰጠውና ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከወለጋ የተፈናቀሉ ዜጎች

ካለፉት ሁለት ወራት በፊት በወለጋ አካባቢ በተከሰተው ጭፍጨፋ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሲፈናቀሉ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በወለጋ የጊንቢ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ ምክንያት ሕይወታቸውን ለማዳን ከአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል ከደብረ ብርሃን በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ አርቡ ከተማ ላይ ከ3,000 በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ዜጎች በቂ የሆነ ምግብ እንደማያገኙና አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በመጠለያው ሕፃናት፣ አረጋውያንና ወጣቶች በጭፍጨፋው ወቅት አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕሙማንም ይገኙበታል፡፡

ከአላማጣ የተፈናቀሉ ዜጎች

ከራያ ቆቦ በቅርብ ርቀት የምትገኝ አላማጣ ከተማ ላይ ከ45 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለው በጃራ መጠለያ አርፈዋል፡፡ ከከተማዋ የተፈናቀሉ ዜጎች በተለያየ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው ከፍ እያለ መምጣቱን እንዲሁም ደግሞ ለተለያየ አደጋ እንደተጋለጡ ይናገራሉ፡፡

ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ ወጣቶችና ነፍሰ ጡሮች የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜም የዕለት ጉርስ እንደሚያጡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አብዛኛው የተፈናቀሉ ዜጎች የራያ ሕዝቦች መሆናቸውን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እንደሚፈልጉና በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሙሉ ለሙሉ እያገኙ ባለመሆኑ ከባድ ችግር ውስጥ እንዳሉ ሪፖርተር በቦታው ሆኖ ለመመልከት ችሏል፡፡

በተለይም አብዛኛው በመማር ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሕፃናት ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተሰናክለዋል፣ ለተለያየ በሽታም ተጋልጠዋል፡፡ ከዚህ አካባቢ የሚፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡  

ሪፖርተርም በጃራና በሃቡር መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ተዘዋውሮ የተመለከተ ሲሆን፣ በእነዚህ መጠለያዎች በቂ የውኃ፣ የምግብና ሌሎች ድጋፎች እያገኙ አለመሆኑን ለመመልከት ችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...