በኢትዮጵያ በዓይነቱና በስፋቱ ትልቁ እንደሚሆን በሚጠበቀውና በአጠቃላይ 24,000 ሔክታር ያካልላል ተብሎ የሚነገርለት የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የማሳያ ምዕራፍ ግንባታ፣ በ301 ሔክታር ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
በ24,000 ሔክታር መሬት ላይ በአምስት ምዕራፍ በ40 ዓመት ውስጥ ዕውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክት፣ በትንሹ አሥር የሚደርሱ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች በሥሩ እንደሚያካትት ተሰምቷል፡፡ ከዚህም ውስጥ የነፃ የንግድ ቀጣና፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የደረቅ ወደብ፣ የአይቲ ፓርክ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና የከተማ ግብርና (ኧርባን ፋርሚንግ)፣ የመኖሪያ ሥፍራዎች፣ የቱሪዝምና የመዝናኛ (ሪክረሽናል) ቀጣናዎች ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
በአዳማና ሞጆ ከተሞች መካከል እንደሚገነባ በሚጠበቀው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ከሚጠበቀው 3,150 ሔክታር መሬት ውስጥ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ አካል የሆነው የ301 ሔክታር መሬት ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን በ3,150 ሔክታር ላይ ለሚተገብረው የልማት ሥራ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ዕውቅና እንደተሰጠው በሐምሌ ወር ተገልጾ ነበር፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከምሥራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ አስተዳደር 301 ሔክታር መሬት ወደ ባለሥልጣኑ የመሬት ባንክ የተላለፈ መሆኑን፣ በዚህም መሬት ላይ የሁለት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የስድስት የኤሌክትሪክ ኃይል ሰብስቴንሽኖች ሥራዎች ስምምነትና ግንባታ ተጀምሯል ተብሏል፡፡
ከ301 ሔክታር መሬት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቀሩት እንዳሉ ሆነው፣ 170 ሔክታር ለሚደርሰው መሬት የካሳ ከፍያ 540 ሚሊዮን ብር ተከፍሏል ተብሏል፡፡ ከ301 ሔክታር መሬት ውስጥ የመንግሥት መሬት ተብለው የተላለፉ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለሥልጣን ከተረከበው መሬት ላይ በአዲሱ ዓመት ለኢንቨስተር የሚያስተላለፈው መሬት እንዳለ የታወቀ ሲሆን፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በቀጥታ ፕሮጀክቶችን የሚሠራ ሳይሆን አልሚዎችን በማምጣት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ለነፃ የንግድ ቀጣናና የሎጀስቲክስ ሃብ የሚሆኑ መሬቶችን እንዲያለሙ እንደሚጋብዝ ተመላክቷል፡፡
በተያዘው የበጀት ዓመት ተቋሙ አንደኛ በውስጥ በጀት በራሱ እንዲችል እየተደረገ የሚቀጥል መሆኑን፣ ከዚህ በሻገር መንግሥትም የማቋቋሚያ ፈንድ እንደመደበለት ተመላክቷል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ዋነኛው ዓላማና አቅጣጫ ተቋሙ ራሱን በገቢ እየቻለ እንዲሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው መሬት መጠንና ስፋት በጥናት ተለይቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም በአንድ ጊዜ የሚጠቃለል እንደማይሆን፣ በፕሮጀክቱ ሰበብ የሚነሱ አርሶ አደሮች በራሱ በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚታቀፉና ተጠቃሚነታቸው ታሳቢ መደረጉ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን የተመለከተ አዋጅ ያልነበራት ቢሆንም፣ ከቀናት በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ ፖሊሲ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ መወሰኑ፣ የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኑን ዕውን ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ የኢንቨስትመንት ቦርድ ከዚህ ቀደም ውሳኔውን ሲያሳልፍ የሰጠው ዕውቅና ፕሮጀክቱን በኢንዱስትሪ ፓርክ ዓይን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም በዚህ ወቅት አዋጁ መፅደቁ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ምሥረታን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ፖሊሲው እንዲወጣም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ግፊት ሲያደርግ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡
በ2050 የመጨረሻው ምዕራፍ ተጠናቆ ዕውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ምሥረታ ‹‹ስታርታፕ›› ከሚባለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አንስቶ በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈለ የነፃ ንግድ፣ የወጪ ንግድ፣ የመዝናኛና የኢንዱስትሪ ከተማ ግንባታ ሥራ እንደሚኖረው ታውቋል፡፡
በዚህ ወቅት በየአሥር ዓመት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች ተለይተው መቀመጣቸውን ሪፖርተር ከምንጮች ያረጋገጠ ሲሆን ለነፃ የንግድ ቀጣናው፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ፣ ለመኖሪያ ጨምሮ የሌሎቹም ፕሮጀክቶች አስፈላጊው ዲዛይን ተሠርቶ ተጠናቋል ተብሏል፡፡