Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአካባቢ ምርጫ ለዜጎች የተሻለ ውክልና ስለሚሰጥ ክልሎች በአንክሮት እንዲሠሩበት ተጠየቀ

የአካባቢ ምርጫ ለዜጎች የተሻለ ውክልና ስለሚሰጥ ክልሎች በአንክሮት እንዲሠሩበት ተጠየቀ

ቀን:

በኢትዮጵያ ከአሥር ዓመት በኋል በቀጣይ 2015 ዓ.ም. ሊካሄድ የታሰበው የአካባቢ አስተዳደር ምርጫ ለዜጎች በተሻለ አማራጭና በቅርበት ለሚገኙ ተወካዮች ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ፣ ክልሎች በተገቢው መንገድ ትኩረት እንዲሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኞ  ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከክልል መንግሥታት ተወካዮች፣ ከፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና መሰል ሌሎች ተቋማት የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት፣ በ2015 ዓ.ም. ሊካሄድ ለታሰበው አካባቢያዊ ምርጫ አስቻይ የሕግ ሥርዓቶች መዘረጋትን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል፡፡

በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ የተለገጸው ይህ የአካባቢ አስተዳደር ምርጫን ለማከናወን በሚደረገው ዝግጅት ላይ፣ የምርጫውን ባህሪና አሠራር አስመልክቶ በተካሄደው ውይይት፣ ምርጫ የወካይና ተወካይን ግንኙነት ማሰሪያና ማጠናከሪያ ውል እንደሆነና ወካዩ ከተወካዩ በበለጠ ከፍተኛ የሆነ ሥልጣን እንዳላው ያብራሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ተወካይ ከወካዩ አጠገብ በራቀ ቁጥር ያንን የወከለውን ባለሥልጣን ተጠቅሞ የማስፈጸምና የመቆጣጠር ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ወካዮች (መራጮች) ከማዕከላዊ መንግሥት ርቀው ስለሚገኙ፣ ሊካሄድ የታሰበው የአካባቢ አስተዳደር ምርጫ ያንን ርቀትና ስፋት የሚያጠብ በመሆኑ፣ ወካዩ ያንን  የወካይነት ሥልጣን በተገቢው ሁኔታ እንዲይዝ እንዲከታተል የሚያደርገው መሆኑ፣ የአካባቢ ምርጫን አስፈላጊነት እጅግ ከፍ እንደሚያደርገው ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት የተሳካ የአካባቢ ምርጫ ተካሂዷል ማለት አይቻልም የሚሉት ሰብሳቢዋ፣ ቀጣዩ ምርጫ ለዜጎች የተሻለ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ፣ ክልሎች የቀበሌ ተወካዮችን ቁጥር እንደ አካባቢው ሁኔታ በማየትና እንደየክልሉ አቅም መወሰን ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ ሊካሄድ የታሰበው የአካባቢ አስተዳድር  ምርጫና የአካባቢ መንግሥት አመሠራረት እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ መምሰል ስለሚኖርበት የተለያዩ አሠራርና የተለያዩ ሒደቶች ሊኖሩት እንደሚችልም አክለው ገልጸዋል፡፡

 የፀጥታ ችግር በሚኖርባቸው አካባቢዎች  ምርጫ እንደማይደረግ የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ምርጫውን ለማካሄድ ብዙ ችግሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉ በመገመት አስፈላጊ የሆኑ የሕግ ዝግጅቶችና አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከባለሙያዎች ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመዳሰስ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ይህ የአካባቢ አስተዳድር ምርጫ በርካታ የወረዳነት፣ የዞንነትና የክልልነት ጥያቄ በተንሰራፋበት ጊዜ በመሆኑ፣ ፓርቲዎች በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸውና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ምርጫው መካሄድ እንዳለበት የገለጹት የቁጫ ሕዝብ ፓርቲ ተወካይ ናቸው፡፡ ተወካዩ በአካባቢ ምርጫ ስም የሕግ ጥሰቶች ሊፈጸሙ ስለሚችሉ ሕጋዊ አሠራሮች ከአሁኑ ሊቀመሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተወካይ አቶ ጄቤሳ ገቢሳ ብዙ ሕዝብ ተፈናቅሎ ባለበትና መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ ችግሮች ባሉበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የአገራዊ ምክክሩ ይቅደም በማለት ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት ብርቱካን ይህን አስመልክተው መልስ ሲሰጡ፣ ስለ አገራዊ ምክክር እየታሰበም ቢሆን ምርጫ የዴሞክራሲዊ ሥርዓት መሠረት በመሆኑ ምርጫ እስከሚሰለች ድረስ ተደግሞና ተደጋግሞ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በምርጫ ሕጉ ውስጥ የአካባቢ ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ በዝርዝር የተቀመጠ አሠራር ባለመኖሩ፣ ምርጫ ቦርድ ክልሎች ግልጽ የሆነ መሥፈርትና የተመራጮችን ቁጥር ለመወሰን የሚያስችል አሠራር እንዲዘረጋ ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበሩት የአካባቢ ምርጫ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫውን ቅቡል አድርጎ ባለማየት፣ ተዓማኒ አይደለም በሚል፣ የፓርቲ አባላትና መሪዎቻችን ይታሰራሉ በሚልና ምርጫውን እንደ ቁም ነገር ባለመውሰድ የማይሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በመጪው 2015 ዓ.ም. ሊካሄድ በታሰበው ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገራዊ ምርጫ ባደረጉት እንቅስቃሴ ልክ፣ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ እንሠራለን ያሉት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...