Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕገወጥ ታጣቂዎች ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችን እየዘረፉ መሆናቸው ተነገረ

ሕገወጥ ታጣቂዎች ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችን እየዘረፉ መሆናቸው ተነገረ

ቀን:

ከጂቡቲ ወደ መሀል አገር ነዳጅ የሚያመላልሱ ቦቴዎች በሕገወጥ  ታጣቂዎች ዝርፊያ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡

ንብረትነቱ የኢስት ዌስት ትራንስፖርት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር  የሆነው 45 ሺሕ ሊትር ናፍጣ የጫነ ቦቴ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መካከል በሚገኘው ሁንዱፎ በሚባል አካባቢ ታግቶ እንደነበር ድርጅቱ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ለሁለት ወራት ያህል አካባቢውን የተቆጣጠሩት ‹‹ኢሳ›› በመባል የሚታወቁት የሶማሌ ጎሳ አባላት ሕገወጥ ታጣቂዎች ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ለቀው ሲሄዱ፣ የአፋር ታጣቂ ኃይሎች ከቦቴው ላይ የነዳጅ ዝርፊያ መፈጸማቸውን ድርጅቱ አክሏል፡፡

ኢስት ዌስት ትራንስፖርት ድርጅት ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ እያስገባ የነበረው አሁን ባለው ግምታዊ ዋጋ ሁለት ሚሊየን ብር የሚያወጣ ነዳጅ ዘረፋ እንደተፈጸመበት፣ አሽከርካሪውም የግል ንብረቱ እንደተዘረፈና አሁንም በታጣቂዎቹ ታግቶ እንደሚገኝ የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓባይነህ ከበደ ተናግረዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ዘረፋ የሚባባስ ከሆነ ለአዲስ አበባና ለክልሎች በሚቀርበው የነዳጅ አቅርቦት ላይ እጥረት መፈጠሩ የማይቀር ነው፤›› ሲሉ አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡

ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ነዳጅ በሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች ላይ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በአፋር ክልል ከሚሌ እስከ ገዋኔ ባለው መስመር፣ ሕገወጥ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት፣ አሽከርካሪዎች ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ጠዋት ሁለት ሰዓት ድረስ ከሚሌ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ፣ የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበር ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መግለጹን አስታውቋል፡፡

በአካባቢው ያሉ ታጣቂዎች የተጠቀሰው ጊዜ በተሽከርካሪዎች ላይ ዘረፋ፣ እንዲሁም በአሽከርካሪዎች ላይ ግድያ እንደሚፈጽሙ ተገልጿል፡፡ ከሐምሌ 15 ቀን በፊት ባሉት ሁለት ወራት ውስጥም አምስት ሾፌሮች ሕይወታቸው ማለፉን፣ ሦስቱ  ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም አሽከርካሪዎቹ ባዶ ቦቴ መኪና ይዘው ሲሄዱ የኢሳ ታጣቂዎች ሁንዱፎ ላይ እንዲቆሙ ተደርገው ውኃ  እንዲያመላልሱ እንደሚደረጉ፣ ጉዟቸውን ሲቀጥሉ ደግሞ የአፋር ታጣቂዎች አስቁመው ውኃ ለምን አመላለሳችሁ በማለት እንደሚደበድቧቸው ማኅበሩ ገልጿል፡፡

የኢስት ዌስት ትራንስፖርት ድርጅት ንብረት የሆነው 45 ሺሕ ሊትር ነዳጅ የጫነ ቦቴ የተዘረፈው፣ ከሁለት ወራት በፊት በአፋር ክልል ሁንዱፎ ከተማ የሰባት ዓመት ሕፃን ልጅ ላይ መጠነኛ ግጭት በማድረሱ ምክንያት የአካባቢው ሰዎች በማስያዣነት ስላስቆሙት እንደሆነ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በተገጨው ሕፃን ምክንያት ተሽከርካሪውን በመያዝ ለድርድር አቅርበውት የነበረ መሆኑን፣ ድርጅቱ የተገጨውን ሕፃን ለማሳከም ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍን የገለጸ ቢሆንም በአካባቢው የሚታወቁ አደራዳሪ (ሽማግሌዎች) አማካይነት  ለሕክምናና ለካሳ በአጠቃላይ አምስት መቶ ሺሕ ብር መክፈል አለባችሁ ተብለው እንደነበር አቶ ዓባይነህ ተናግረዋል፡፡

በድርድሩ ወቅት የተገለጸው የካሳ ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ ድርጅቱ ጉዳዩን ወደ አፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በመውሰድ መፍትሔ ቢጠይቅም፣ የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ሁንዱፎ የሚባለው አካባቢ በእሱ ቁጥጥር ሥር አለመሆኑን ምላሽ በመስጠቱ፣ በፌዴራል ደረጃ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረጋቸውን አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በፌዴራል ደረጃ ጉዳዩ ታይቶ መፍትሔ እንዲሰጠው በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አማካይነት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጣልቃ እንዲገባ በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት፣ ጉዳዩ የተመራበትን ክፍል በተደጋጋሚ ቢጠይቅም መፍትሔ ባለመገኘቱ፣ በመጨረሻ ተሽከርካሪውን ከያዙት የኢሳ ጎሳ ሽማግሌዎች ጋር  በመደራደር 350 ሺሕ ብር ለመክፈል ተስማምተው ገንዘቡን ወደ ገዋኔ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ማስተላለፋቸውን አቶ ዓባይነህ ተናግረዋል።

ገንዘቡን ከማስረከባቸው አስቀድሞ ከተሽከርካሪው ላይ የተፈቱትን ሦስት ጎማዎችና ባትሪ እንዲመልሱ በመስማማት ጎማ በመግጠም ላይ ሳሉ፣ ከተማው በአፋር መደበኛ ያልሆኑ ታጣቂዎች በመከበቡ ኢሳዎቹ ከተማውን ለቀው መውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢስት ዌስት ትራንስፖርት ድርጅት ስለሁኔታው ገዋኔ ለሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ በማሳወቅ ጥበቃ እንዲደረግ ካደረገ በኋላ፣ ሰመራ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ችግር እንደማይኖር ገልጸውላቸው እንደነበር አቶ ዓባይነህ ተናግረዋል።

በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ሪፖርተር አፋር ክልል ለሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አዛዥ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ በመደወልና የአጭር የጽሑፍ መልዕከት በመላክ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

ይሁን እንጂ የአፋር ታጣቂዎች በሶማሌ ታጣቂዎች ተይዞ የነበረውን ከተማ ሲቆጣጠሩ ቦቴውን ከላይም ከታችም በመውረር ነዳጁን ከመዝረፋቸውም በላይ አሽከርካሪውን ደብድበው የተሽከርካሪውን ቁልፉ መውሰዳቸውንና አሽከርካሪው አሁንም በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ አቶ ዓባይነህ ገልጸዋል፡፡

አካባቢው በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት በመሆኑ ጥበቃ የሚያደርግ ባለመኖሩ፣ ለጥበቃ ሠራተኞች በቀን እስከ አምስት ሺሕ ብር ድረስ እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ዝርፊያውን በተመለከተ ለፌዴራል ፖሊስ ማመልከቻ ያስገባ መሆኑን፣ ነዳጅ ጭኖ የነበረው ቦቴ እንዲመለስና ዘራፊዎቹ ተይዘው ነዳጁን እንዲመልሱ ለአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋ አሳመረ በበኩላቸው፣ በነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ላይ ችግር እንዳይፈጠር የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል አካላት፣ በዚህ መስመር ላጋጠመ የፀጥታ ችግር ትኩረት ተሰጥቶት አፋጥኝና ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰሃረላ አብዱላሂን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...